1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ኅዳር 12 2012

ሕወሓት በዚሕ አቋሙ ከፀና ኢሕአዴግ የሚዋሐደዉ ከነባር አባሉት አንዱን ቀንሶ፣ አምስት አጋሮቹን ደምሮ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ምርሑን ጥሎ፣ በመደመር አስተሳሰብ የኢትዮጵያን ፖለቲካ-ምጣኔ ሐብት ድጥ-ማጥን ይዘዉራል ወይም ይዘዋራል ማለት ነዉ።

https://p.dw.com/p/3TZEB
Äthiopien |  Abstimmung EPRDF
ምስል EPRDF


ሕወሓት ራሱን ከኢሕአዴግ ዉሕደት ማግለሉ፣ የሲዳማ ሕዝበ ዉሳኔና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መማር አለመማር ሳምንቱን የአብዛኞቹን የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚዘግቡ መገናኛ ዘዴዎችን ትኩረት የሳቡ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ገፆችን ያጨነቃቁ አስተያየቶች የተሰነዘረባቸዉ ርዕሶች ናቸዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ። የጎሉትን ባጫጭሩ እንቃኛለን።

የኢሕአዴግ ሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፈዉ ቅዳሜ ባሳለፈዉ ዉሳኔ እስካሁን በጎሳ ላይ የተመሠረቱ አራት የፖለቲካ ማሕበራትን የሚያስተናብረዉ የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ኢሕአዴግ የግንባርነት ጉዞዉ በቅርቡ ያበቃል።ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴዉ በአብላጫ ድምፅ በወሰነዉ መሰረት ኢሕአዴግ አጋር የሚላቸዉን አምስት የፖለቲካ ማሕበራት ቀይጦ የኢትዮጵያ የብልፅግና ፓርቲ (ኢብፓ) ወደተሰኘ ዉሑድ የፖለቲካ ማሕበር ይለወጣል።
ትናንት የተጀመረዉ የኢሕአዴግ ምክር ቤትም የሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴዉ ያሳለፈዉን ዉሳኔ በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል። ይሁንና የኢሕአዴግ መሥራችና የተቀሩትን አባልና አጋር ድርጅቶች ባምሳያዉ የፈጠረዉ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በቅዳሜዉ የኢሕአዴግ ሥራ-አስፈፃሚ ስብሰባ ዉሕደቱን በመቃዉም ድምፅ ሲሰጥ፣ ትናንት በተጀመረዉ በኢሕአዴግ የምክር ቤት ጉባኤ ደግሞ ጨርሶ እንደማይሳተፍ በደብዳቤ አስታዉቋል።
ሕወሓት በዚሕ አቋሙ ከፀና ኢሕአዴግ የሚዋሐደዉ ከነባር አባሉት አንዱን ቀንሶ፣ አምስት አጋሮቹን ደምሮ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ምርሑን ጥሎ፣ በመደመር አስተሳሰብ የኢትዮጵያን ፖለቲካ-ምጣኔ ሐብት ድጥ-ማጥን ይዘዉራል ወይም ይዘዋራል ማለት ነዉ። የኢሕአዴግ ዉሕደት በተለይም ሕወሓት ዉሕደቱን መቃወሙ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ  አስተያየት ሰጪዎች እያከራከረ ነዉ።ጥቂቱን በወፍ በረር እንቃኝ።
እንደ እንግሊዝኛዉ Peace Save Us  የሚል የፌስ ቡክ መጠሪያ ያላቸዉ አስተያየት ሰጪ የሕወሓትን ያሁን እርምጃ ብቻ ሳይሆን ጥቅል የሕወሓት አቋምን ይተቻሉ። «ጨዉ ለራስሕ ስትል ጣፍጥ ይላላሉ Peace save us «ሕወሓት የሠራችው ግፍ መች ወደ በጎ ይመራታል ።እንኳን ዓለም በመሠከረለት መሪ በአፓርታይድም ተመርተናል። ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ።» 
ብርሐነ ወልደሩፋኤል ግን የሕወሓትን ዉሳኔ «ምርጥ» ብለዉታል። የሱነሕ ወልዴ ግን ዘለግ ባለ አስተያየታቸዉ የሕወሓትን ዉሳኔ ፓርቲዉ ራሱን የሚቀብርበት በማለት ይኮንኑታል።«ይሕን አጋጣሚ በመጠቀም የበደለዉን ሕዝብ ሊክስ ይገባል። አለበለዚያ ግን ሕወሓት እራሱን በራሱ የሚቀብርበት ጊዜ» ይሉና የሱነሕ፣ «ለሌሎች በክልሉ ለሚኖሩ ፓርቲዎች ትልቅ እድል የሚሰጥ እና ከአዲሱና  ካንጋፈዉ  የኢሐዲግ ፓርቲ ጋር በመዋሐድ ሕዝባቸውን በተሻለ መልኩ የሚያገለግሉበት መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ይመስሉኛል።» በማለት አስተያየታቸዉን ይደመድማሉ።

Emblem der Tigray People's Libration Font (TPLF)

ታደሰ ማናዬ፦ በኳስ ግጥሚያ ቃላት የደመደሙትን አስተያየት፣ «ጊዜው አሁን ነው በትግራይ ክልል ላሉ ለትግራይ ህዝብ እንታገላለን ብለው እየተንቀሳቀሱ የሉ ፓርቲዎች -----ምስኪኑን የትግራይን ህዝብ መርዳትና ከጎኑ መቆም ያለባቸዉ ጊዜው አሁን ነው።» ይላሉ። እልፍ ብለዉ፣ ዋው የጫወታው ፊሽካ ተነፋ!!! በትግራይ ክልል ሰም በትግራይ ክልል የሚታወቁት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ፎርፌ ሊያገኙ ነው።» እንደገና « ዋው!!!» አሉ ታደሰ ማናዬ።

አቡዋይሜን አብዱ ደግሞ፦ «ምስኪን ላሉት ለትግራይ ሕዝብ ምክር ብጤ አላቸዉ። የፌስ ቡክ ምክር «በጣም የሚያሳዝነው ነገር ህዋሃት 27 ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያን አውድሞ አጥፊዎችም በህግ ቁጥጥር ስር ሳይውሉ በማን አለብኝነት ባሉበት ሁኔታ አሁን ደግሞ ያ ጥፋት ሳያንሳቸው ይህን ድሃ ህዝብ ወደ ጦርነት ሊያስገቡት ነው፣ምስኪኑ የትግራይ ህዝብ ሆይ የነዚህን መሪዎቻችሁን የተሳሳተ ሃሳብ ተቃዎማችሁ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የመረጠውን ለሃገርና ለህዝብ የሚበጀውን ሃሳብ መደገፍ አለባችሁ።
ብርሃኔ ኃይለ-ሥላሴ ግን የሕወሓትን ዉሳኔ የሚደግፉ ይመስላል፣« ትግላችን ረጂምና መራራ ነዉ፣ድል ማድረጋችን የማይቀር ነዉ !!» ይላሉ በፌስ ቡክ።ድሮ አብዮት-ፀረ አብዮት በሚባልበት በ1960ና 70ዎቹ «ትግላችን መራራ፣ ጉዟችን ረጅም፣ ግባችን ሩቅ፣ ድላችን ግን ጣፋጭ ነዉ» እየተባለ ይፈከር፣ይዘመር ነበር።ያኔ ኢንተርኔት፣ፌስ ቡክ፣ ተንቀሳቃሽ ስልክ አልነበረም።
ወደ ፌስ ቡክ እንመለስ፣ የተስፋዬ ሐጎስ አስተያየት ባጭሩ እንዲሕ ይነበባል። «የትግራይ ህዝብ ከማንም ነፍጠኛ ግንኙነት ሊኖሮው ስለማይችል የትግራይ ህዝብን የወከሎው ህወሓት ከነፍጠኛው ኣብሮ ቁጭ ብሎ ተወያይቶ ውሳኔ መስጠት በትግራይ ህዝብ መቀለድ ስለ ሆነ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብየ ነዉ የምገምተው።»
ዑመር አደም ግን ሕወሓትን «ከግንባርነት ወደ አጋርነት እንኳን በሰላም መጣችሁ።» ይላሉ በፌስ ቡክ ፅሑፋቸዉ ።ብለዉ አላበቁም፣ «ኤርትራ ካናታችን ላይ ስትቀፈፍ ምንም ያላለዉ የኢትዮጲያ ህዝብ እናንተም ብትሞክሩት አይከፍውም።» እያሉ ይቀጥላሉ።

አብዱ ሰዒድ ጥያቄ ብጤ ነዉ አስተያየታቸዉ። «አዛውንቱና እብሪተኛው ህወሓት አብዮታዊ ድሞክራሲ ላይ ድርቅ ብሎ መቅረቱ አይገርምም?» መልስም አላቸዉ፣ «ይህ የዘራፊዎችና ያምባገነኖች ስብስብ ለውጥ አይናፍቀውም፡፡ ህዝብን እያሸበረና እያባላ መቀጠል ነው ፍላጎቱ፡፡» እያለ ጥቂት መስመሮች የሚያክል መልስ።
የኢሕአዴግ ዉደትን እና የሕወሓትን እንቢተኝነት በተመለከተ የተሰጠና የሚሰጠዉ አስተያየት፣ ትችት፣ አንዳዴ ስድብ ርግማኑ ብዙ ነዉ።በጉዳዩ ላይ ሥርዓት የጠበቀዉ ዉይይት መቀጠሉ አይከፋም።ስድብ ዘለፋዉ ግን???? ለማንኛዉም እኛ ለዛሬዉ አበቃን።
ሁለተኛዉን  ርዕስ እንቃኝ። የሲዳማ ሕዝበ ዉሳኔ። ሲዳማ የራስ ገዝ አስተዳደር እንዲኖራት ሲዳማዎች ከ40 ዓመት በፊት ጀምሮ በነፍጥ ዉጊያ፣ በአደባባይ ሰልፍ፣ በዉይይት ክርክር መድረክም ሲጠይቁ ነበር።
ጥያቄዉ በተደጋጋሚ ወደ ኃይል ርምጃና ግጭት እየተለወጠ የብዙዎች ሕይወት ጠፍቷል። በብዙ ቢሊዮን የሚገመት ሐብትና ንብረት ወድሟል፤ ብዙዎችን አፈናቅሏል። እስካሁን የመጨረሻዉ ግጭት የተደረገዉ ባለፈዉ ኃምሌ አጋማሽ ነበር። የዞኑ ባለስልጣናት ያኔ እንዳስታወቁት በግጭቱ በትንሽ ግምት ከ50 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። የጠፋዉን ሐብትና ንብረት በዉል የገመተዉ የለም።
ሲዳማ እስካሁን እንደነበረዉ የደቡብ ብሔራዊ መስተዳድር አካል ሆኖ ይቀጥል ወይም 10ኛዉ የኢትዮጵያ ክልል ይሁን በሚሉ ሁለት ሐሳቦች ላይ ባለፈዉ ሮብ የተደረገዉ ሕዝበ ዉሳኔ ዓመታት ያስቆጠረዉ ዉዝግብ፣ ግጭት፣ ግድያና ጥፋትን ለማስቆም ይጠቅማል የሚል ተስፋ አሳድሯል።
ለጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ግን ተስፋዉ ሥጋትም የተለየዉ አልመሰለም። ጠቅላይ ሚንስትሩ ባለፈዉ ሮብ ድምፅ መሰጠት እንደተጀመረ በፌስ ቡክ ባስተላለፉት መልዕክት ፀጥታ እንዳይታወክ አደራ ብለዋል።
«የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ኢትዮጵያ እየሄደችበት ያለውን የዴሞክራሲ ጎዳና አመላካች ነው» ይላሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ « ዜጎች ድምጽ ለመስጠት በሚወጡበት በዛሬው ዕለት ሁሉም ተሳታፊዎች ለሂደቱ ሰላማዊነትና ዴሞክራሲያዊነት እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አቀርባለሁ።» አከሉ።
ፍሬሕይወት ፍሬeይ የተባሉ የፌስቡክ አስተያየት ሰጪ፦ ለሲዳማዎች መልካም ምኞታቸዉን፣ ለኢትዮጵያ ሠላምና ፍቅርን ተመኝተዋል። «መልካም የምርጫ ጊዜ ይሁንላቸው።በዚህ ምርጫ የወደፊቱ ብሔራዊ ምርጫ ፍትሐዊ መሆኑን የምናይበት ይሆናል። ሰላምና ፍቅር ለሀገራችን።» ብለዉ አበቁ።

Äthiopien Yirgalem Sidama Referendum
ምስል DW/S. Wegayehu

ባለፈዉ ሮብ ድምፅ ሰጪዉ ሕዝብ በተለይ የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ ድምፁን ለመስጠት ከማለዳዉ ጀምሮ በየድምፅ መስጪያ ጣቢያዉ መሰለፉት ከዶቸ ቬለ ዘገባ ያደመጡት ገደፋዉ አምሳሉ ጥጋቡ፣ «ምርጫ 97ን አስታወሰኝ።» ይላሉ የሕዝቡ ጉጉት በፌስ ቡክ። «የማይነጋ መስሏቸው ፈርተው እኮ ነው። ምርጫ 97ን አስታወሰኝ።» ቀጠሉ ገደፋዉ። « ያኔ ኢህአዴግን ለመጣል አብዛኛው ህዝብ ሌሊት ነበር ወደየምርጫ ጣቢያዎች የጎረፈው። እመጫቶችም አልቀሩም ነበር። ሌሊት 8 እና 9 ሠዓት የመሄዱ ሚስጥር ሲዳማ ክልል ሆና ለማየት ከመጣ ጉጉት ነው።»
ይሕን ዝግጅት እስካጠናቀርንበት እስከ ትናንት አመሻሽ ድረስ የሕዝበ ዉሳኔዉ አጠቃላይ ዉጤት በይፋ አልተነገረም። በየድምፅ መስጪያ ጣቢያዎች የወጡ ዉጤቶችንና የድምፅ ሰጪዉን አጠቃላይ ስሜት የገመገሙ ታዛቢዎች እንደሚሉት ግን ሲዳማ የክልልነት አስተዳደር ይኑራት የሚለዉ አማራጭ በአብላጫ ድምፅ መፅደቁን አይጠራጠሩም።
የዉጤቱን እንዴትነት አስቀድመዉ ያወቁ የሚመስሉት አብረሐ ይሻቅ በፌስ ቡክ የሰጡት አጭር አስተያየት በሦስት ጥያቄዎች ያሳርጋሉ። ጥያቄ አንድ፣- «በቀድሞ መንግሥታት ክፍለ ሀገር የነበረው ሲዳማ አሁን ድንበሩ የት ድረስ ሊሆን ነው? በኦሮሞ ስለተወሰዱት ግዛቶችስ ምን ያስባል? ሻሸመኔስ የማን ልትሆን ነው? እኔ የምለው  ሻሸመኔ የሚለው ቃል ኦሮምኛ ነው ወይስ ሲዳምኛ? ትርጉሙስ ምን ማለት ይሆን? ጥያቄ ሁለት መሆኑ ነዉ። 3፣ በአዲሱ የሲዳማ ክልል የሲዳማ ድንበሩስ የት ድረስ ነው የሚሆነው? ሻሻማኔ፣ ጥቁር ውኃ፣ ወንዶገነት? ጥያቄ ሦስት።
ለአብረሐ ይሻቅ ጥያቄ ዝርዝር መልስ የሚሆን አስተያየት የሰጠ እስካሁን የለም። የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ሌዳሞ ባለፈዉ ሮብ ድምፅ ከሰጡ በኋላ ያሉትን በመደበኛዉም በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎችም አሰራጭተነዉ ነበር። ምናልባት ጥቅል መልስ ከሆነ በድጋሚ ስሙት።
                        
የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዘር-ጎሳ ለይተዉ እዚሕም እዚያም መደባደብ፣ መጋጭት፣ መጋደላቸዉ ባገባደድነዉ ሳምንትም የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ርዕስ ሆኖ ነዉ የሰነበተዉ። ከዚሕ ቀደም ተማሪዎች በመጋጨት መጋደላላቸዉና በመሸሻቸዉ ሰበብ ትምሕርት አቋርጠዉ የነበሩ የወልዲያ፣ የጎንደር (በከፊል) እና የወሎ (ደሴ) ዩኒቨርስቲዎች አቋርጠዉት የነበረዉን ትምሕርት መጀመራቸዉን ዘግበናል። የዘገባጭን ምንጮች የየዩኒቨርስቲዉ ባለስልጣናት ናቸዉ።
ጂግሳ ኒሞና ግን በተለይ የወልዲያ ዩኒቨርስቲ ትምሕርት መጀመሩን ማስታወቁን አይቀበሉትም። እንዲያዉም ይጠይቃሉ።«ምን ትምህርት ይጀመራል።» ብለዉ። መልስም አላቸዉ። ተማሪዎች በራሳቸው መንገድ አየተመለሱ አይደለም እንዴ? ከወልድያ ዩኒቨርሲቲ በራሳቸው መንገድ አዲስ አበባ ገብተዋል።» ብለዉ ለራሳቸዉ ጥያቄ እራሳቸዉ መለሱ።
የወልዲያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዳግም ትምሕርት የጀመሩት በሃይማኖት መሪዎች፣ በሐገር ሽማግሌዎችና በመንግስት ባለስልጣናት ጥረትና ምክር እንደሆነ የዩኒቨርስቲዉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ባለፈዉ ሮብ ለዶቼ ቬለ አስታዉቀዉ ነበር።
ኢዶሳ ተፈራ ግን በፊስ ቡክ «ለመሆኑ የምትሉት እዉነት ነዉ?» ይላሉ እኛን ይሁን የዩኒቨርስቲ ባለስልጣናቱን አለዩም። ብቻ ቀጠሉ። «ሃይማኖት፣ ሽማግሌ እና መንግስት አሉ እንዴ?»
መልካም የሳምንት መጨረሻ።

Äthiopien Sidama Referendum vorläufige Ergebnisse
ምስል DW/S. Muchie

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ