1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 የሚያዝያ 26 ቀን፤ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 26 2012

የጀርመን ቡንደስሊጋ የእግር ኳስ ውድድር ሊጀመር ዳር ዳር ባለበት በአኹኑ ወቅት የኮሎኝ ቡድን ውስጥ ሦስት ሰዎች በኮሮና ተሐዋሲ መጠቃታቸው መነገሩ ስጋት አጭሮ ነበር። በገለልተኛ ቤተ-ሙከራ ውስጥ ጠቅላላ የቡድኑ አባላት በተደረገላቸው ምርመራ ከሦስቱ በስተቀር ኔጌቲቭ ማለት ነጻ መባላቸው ተጠቅሷል።

https://p.dw.com/p/3blIF
Symbolbild Absage Bundesliga wegen Coronavirus
ምስል picture-alliance/Geisler

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በጀርመን ቡንደስሊጋው  ሊጀመር ዳር ዳር እያለ ነው። የመጨረሻ ውሳኔ ከነጌ በስተያ ይሰጣል ተብሏል። ከወዲሁ ታዲያ አንዳንድ ተጨዋቾች ዳግም ውድድሩ የሚጀምርበት ጊዜ ተፋጠነ ሲሉ ቅሬታ አሰምተዋል። በኮሎኝ ቡድን ውስጥ ሦስት ሰዎች በኮሮና ተሐዋሲ መጠቃታቸውም ቡንደስሊጋው ላይ ሌላ ስጋት ፈጥሯል። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የትኞቹ ስታዲየሞች ውስጥ ይከናወን የሚለው ቡድኖቹን እያወዛገበ  ነው።

የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ማለትም ካፍ አባል ሃገራቱ የሊግ ውድድሮቻቸው ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ እና ስለቀጣይ እጣ ፈንታቸው እንዲያሳውቊ የሰጠው ቀነ ገደብ ነገ ይጠናቀቃል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ ኩባንያ በዚሁ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ለነገ ቀጠሮ ይዘዋል። ቀደም ሲል ስብሰባው በዋዜማው ሊደረግ ነው የሚሉ ዘገባዎች ታይተው ነበር። 

የጀርመን ቡንደስሊጋ የእግር ኳስ ውድድር ሊጀመር ዳር ዳር ባለበት በአኹኑ ወቅት የኮሎኝ ቡድን ውስጥ ሦስት ሰዎች በኮሮና ተሐዋሲ መጠቃታቸው መነገሩ ስጋት አጭሮ ነበር። የኮሎኝ ቡድን ግን ዛሬ ይፋ እንዳደረገው ከኾነ፦ ባለፈው ሳምንት በተሐዋሲው ከተጠቊት ሦስት ሰዎች በስተቀር ሁሉም የቡድኑ አባላት ተመርምረው ነጻ ተብለዋል። በገለልተኛ ቤተ-ሙከራ ውስጥ ጠቅላላ የቡድኑ አባላት በተደረገላቸው ምርመራ ኔጌቲቭ ማለት ነጻ መባላቸው ተጠቅሷል።

Coronavirus - Köln Tageskassen sind am RheinEnergieStadion geschlossen
ምስል picture-alliance/dpa/F. Gambarini

ከነገ በስትያ ረቡዕ የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጀርመን ውስጥ የእንቅስቃሴ ገደብ ይበልጥ ስለሚላላበት ኹኔታ ከሚንሥትሮቻቸው ጋር ይወያያሉ። ምናልባትም ቡንደስሊጋው ዳግም እንዲጀመር ሊፈቀድም ይችላል እየተባለ ነው።

በኮሎኝ ቡድን ውስጥ ባለፈው ሳምንት በኮሮና ተሐዋሲ ተጠቅተዋል የተባሉት ኹለት ተጨዋቾች እና አንድ የቡድኑ ወጌሻ ናቸው። ሦስቱም ሰዎች ካለፈው ዐርብ ጀምሮ ራሳቸውን ለይተው ነው የሚገኙት።

የጀርመን እግር ኳስ ሊግ (DFL) ባወጣው የንጽህና እና የደኅንነት ደንብ መሠረት ኹሉም የእግር ኳስ ቡድኖች ተጨዋቾች በተከታታይ የኮሮና ተሐዋሲ ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ውድድሮች መካሄድ ያለባቸውም በዝግ ስታዲየሞች ውስጥ ነው። ለኹለት ጊዜያት ተመርምረው ከኮሮና ተሐዋሲ ነጻ የተባሉ ተጨዋቾች ብቻ የእግር ኳስ ልምምድ ማድረግ ይፈቀድላቸዋል። ይኽ ጥብቅ ቊጥጥር እንዲደረግ የተወሰነው ተጨዋቾች እና የቡድኑ አባላት ለኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት ተጋላጭ እንዳይኾኑ ነው።

የኮሎኝ ቡድን ከዛሬ ጀምሮ ወደ ልምምድ እንደሚገባ ቀደም ሲል ዐስታውቋል። የኒው ፓዴርቦን ቡድን የተጨዋቾች ኹለተኛ ዙር የምርመራ ውጤት እንደደረሳቸው ወዲያውኑ ወደ ልምምድ እንደሚገቡ ቡድኑ ዐስታውቋል።

የጀርመን እግር ኳስ ሊግ ኪከር ለተሰኘው በጀርመንኛ ቋንቋ የሚታተም መጽሄት ይፋ እንዳደረገው የእግር ኳስ ቡድኖች የኮሮና ተሐዋሲ ምርመራ ውጤታቸውን ይፋ ማድረግ አይጠበቅባቸውም። ከዚያ ይልቅ በተማከለ መልኩ ውጤቱን ሊጉ ይፋ እንደሚያደርግ ዐስታውቋል። አንዳንድ ቡድኖች ስለውጤታቸው ከወዲሁ ዐስታውቀዋል አለያም ለመገናኛ አውታሮች ገልጠዋል። አውስቡርግ፤ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ እና ኤር ቤ ላይፕሲሽ ውጤታቸውን ይፋ አላደረጉም።

Fußball Bundesliga |  Schalke 04 v RB Leipzig | Tor (0:2)
ምስል picture-alliance/Hufnagel PR/U. Hufnagel

የጀርመን እግር ኳስ ሊግ ቡንደስሊጋው ዳግም እንዲጀመር ባቀረበው ምክረ-ሐሳብ መሠረት ተጨዋቾች በኮሮና ተሐዋሲ ከተጠቊ ውጤቱ ወዲያውኑ ለመገናኛ አውታሮች ይፋ አይደረግም። እስካሁን ድረስ ከቡንደስሊጋው 14 ቡድኖች ውጪ የሌሎቹ ቡድኖች የኮሮና ተሐዋሲ መለያ ምርመራ ውጤታቸውን ዐላሳወቊም።

የጀርመን ፖለቲከኞች ቡንደስሊጋው ዳግም በዝግ እንዲጀምር ረቡዕ እለት በሚያደርጉት ስብሰባ ፈቃዳቸውን ያሳያሉ ተብሎ ይጠበቃል። አኹን ይበልጥ አነጋጋሪ ከኾኑ ጉዳዮች መካከል ጨዋታዎቹ በዝግ የሚካሄዱ ከኾነ እግር ኳስ አፍቃሪያን ግጥሚያዎቹን እንዴት መከታተል ይችላሉ የሚለው ነው።

ጨዋታዎቹን በቴሌቪዥን የማስተላለፍ ፈቃድ ያላቸው እንደ ስካይ ስፖርት ያሉ የግል ጣቢያዎች ከፍለው ለሚከታተሏቸው ደምበኞቻቸው ብቻ የሚያሰራጩ ከኾነ ችግር መፈጠሩ አይቀርም። ያም በመኾኑ የግል ጣቢያዎቹ ጨዋታዎችን ከደምበኞቻቸውም ውጪ በጣቢያቸው ላይ ለኹሉም ሰው በነጻ እንዲያስተላልፉ ይጠበቃል። አለያም ደግሞ ሌሎች ጀርመን ውስጥ የሚገኙ እንደ ARD እና  ZDF  ያሉ ሕዝባዊ ጣቢያዎች ጨዋታዎቹን በየጣቢያዎቻቸው እንዲያሰራጩ የግል ጣቢያዎቹ ፍቃድ መስጠት አለባቸው።

በዚህም አለ በዚያ ጨዋታዎቹ እንዴት የእግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ መድረስ እንደሚችሉ ስምምነት ላይ ለመድረስ የፖለቲከኞቹ ውሳኔ ወሳኝ መኾኑን ጨዋታዎቹን በበላይነት የማሰራጨት መብት ያለው ስካይ ስፖርት ዐስታውቋል።

Borussia Dortmund Signal-Iduna-Park
ምስል picture-alliance/Digitalfoto Matthias

ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ በጀርመን እና እንግሊዝ የሚገኙ አንዳንድ ተጨዋቾች ከኮሮና ስጋት ባልተላቀቅንበት በአኹኑ ወቅት ዳግም የእግር ኳስ ግጥሚያው የሚጀምርበት ጊዜ በጣም ተጣድፏል ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። «ጤና ከእግር ኳስ ይቀድማል» ሲል ቅሬታውን የገለጠው የኮሎኝ አማካኝ ተጨዋች ቢርገር ፈርሽትራይቴ ነው። እግር ኳስ በዓለማችን ከፍተኛ ገንዘብ የሚሽከረከርበት፤ በማኅበረሰቡ ዘንድ ጠቀሜታ ያለው ብርቱ ስፖርት ቢኾንም የሚጫወቱት ግን ሰዎች መኾናቸውን መዘንጋት እንደማይገባም አክሏል።

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዳግም ሊጀምር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በአኹኑ ወቅት ውድድሮች እንዴት እና የት ይካሄዱ የሚለው ግርታን ፈጥሯል። እግር ኳስ ውድድሮቹ በዝግ ስታዲየሞች ሲከናወኑ እግር ኳስ አፍቃሪያን በስታዲየሞቹ ዙሪያ እንዳይሰባሰቡ ለመከላከል ከመኖሪያ ቤቶች ራቅ ያሉ ስታዲየሞችን መምረጥ ያስፈልጋል ተብሏል። ለዚያም ፕሬሚየር ሊጉ ከ8-10 ስታዲየሞችን ለመምረጥ በዝግጅት ላይ ነው። እነዚህ የተመረጡ ስታዲየሞች የፕሬሚየር ሊጉ ቀሪ 92 ግጥሚያዎች የሚካሄዱባቸው ናቸው።

Fußball UK Burnley vs. Manchester City
ምስል Getty Images/A. Livesey

ከመኖሪያ ቤቶች ካላቸው ርቀር አንጻር የአርሰናሉ ኤሚሬት ስታዲየም ወይንም የማንቸስተር ሲቲው ኤቲሃድ ስታዲየም የበለጠ ተመራጮች ሳይኾኑ አይቀሩም።  እነዚህ ስታዲየሞች የሚገኙባቸው ኹኔታ ፖሊስ አካባቢውን በሚገባ ለመቆጣጠር አመቺ ናቸው። ኾኖም ትናንት በወጡ ዘገባዎች መሠረት በፕሬሚየር ሊጉ ወራጅ ቃጣና ውስጥ እና ከታች እስከ ስድስተኛ ደረጃ የሚገኙ ቡድኖች በዚህ ሐሳብ ቅሬታ እንደገባቸው ዐሳውቀዋል። ቅሬታቸውን ያሰሙት ቡድኖች፦ ብራይተን፣ ዌስትሐም፣ ቦርመስ፣ ዋትፎርድ፣ ኖርዊች እና አስቶን ቪላ ናቸው።

እነዚህ ቡድኖች ላለመውረድ ቀሪ ጨዋታዎችን ሲያደርጉ በስታዲየሞቻቸው በሜዳቸው ሲጫወቱ የሚኖረውን ጠቀሜታ የሚያሳጣ ነው በሚል ነው የተቃወሙት። በተመረጡ ስታዲየሞች ጨዋታው ይካሄድ የሚለው ሐሳብ ተግባራዊ የሚኾነው ግን ከ31ዱ ቡድኖች 20ው ይኹንታ ከሰጡት ብቻ ነው። የመውረድ ስጋት ካጠላባቸው ከስድስቱ ቡድኖች የአንደኛው ኃላፊ እንደተናገሩት ቡድኖቹ በተመረጡ ስታዲየሞች ውድድሮቹ ይከናወኑ የሚለውን ሐሳብ የሚደግፉት ዘንድሮ ወደታችኛው ዲቪዚዮን መውረድ የሚባል ነገር ከቀረ ነው ብለዋል።

Fußball RB Leipzig Timo Werner mit hochgestülptem Kragen
ምስል picture-alliance/dpa/U. Anspach

የኤር ቤ ላይፕሲሹ ቲሞ ቬርነር በቡንደስሊጋው ለባየር ሙይንሽን ቡድን ከመጫወት ወደ ውጭ ሃገር ሄዶ መጫወት ምርጫው እንደኾነ ተናግሯል። ጀርመናዊው  አጥቂ  በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ከሊቨርፑል እና ቸልሲ ጋር ግንኙነት እንዳለው እየተነገረ ነው። የ24 ዓመቱ አጥቂን ከሌሎች የጀርመን የእግር ኳስ ተጨዋቾች በተለየ የውጭ ሃገራት ቡድኖች ዐይናቸውን ጥለውበታል። እሱም ቢኾን ወደ ውጭ ሃገር ሄዶ መጫወት እንደሚሻ ተናግሯል። በተለይ ቲሞ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ ባለድሉ እና የዘንድሮ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫ ለመውሰድ ጫፍ ወደ ደረሰው ሊቨርፑል የመሄዱ ነገር ርግጥ ነው እየተባለ ነው። ሊቨርፑል ከቲሞ ቬርነር ጋር ያደረገው ንግግር አመርቂ መኾኑም ተገልጧል። ምናልባትም ሊቨርፑል የአምስት ዓመት ውል  ለቲሞ ቬርነር ለማቅረብ መዘጋጀቱም ተዘግቧል። በውሉ መሠረት ቲሞ በአምስት ዓመት ቆይታው በየጨዋታ ዘመኑ 10 ሚሊዮን ዩሮ ይከፈለዋል ነው የተባለው። በአጠቃላይ ሊቨርፑል ቲሞ ቬርነርን ለማስመጣት ለላይፕሲሽ እስከ 60 ሚሊዮን ዩሮ መድቧል።

የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ እጣ ፈንታን ለመወሰን ነገ ቀጠሮ መያዙ ተገልጧል። የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ማለትም ካፍ አባል ሃገራቱ ስለሊግ ውድድሮቻቸው ያሉበት ደረጀ እና የወደፊት እጣ ፈንታቸው ላይ የደረሱበትን ውሳኔ እስከ ነገ ሚያዝያ 27 ድረስ እንዲያሳውቊ ማሳሰቡ ይታወሳል። የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ ኩባንያ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ  ፌዴሬሽን  ነገ ያደርጉታል በተባለው የጋራ ስብሰባ ውሳኔያቸውን ለካፍ በነገው እለት ያሳውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።  

BdTD Neujahrs-Grand-Sumo-Turnier
ምስል imago images/Kyodo News

በጃፓን የኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት በሀገሪቱ ተወዳጅ የኾነው የሱሞ ስፖርት እንዲሰረዝ አድርጓል። በጃፓን የትግል ስፖርት ማለትም የሱሞ ማኅበር በቅርቡ ሊካሄድ የነበረውን ፍልሚያ በመሰረዝ በቀጣይ ውድድሮች ታዳሚያን በሌሉበት እንዲከናወን ወስኗል። ቀጣይ ውድድር ይካሄዳል ተብሎ ቀጠሮ ተይዞ የነበረው ከ20 ቀን በኋላ ነበር። የሀገሪቱ ጥንታዊ የትግል ፍልሚያ ስፖርት ሱሞ ውድድር  በቅድሚያ ለኹለት ሳምንት እንዲራዘም ተወሰኗል።

ውድድሩ መራዘሙ የተነገረው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሺንዞ አቤ በጃፓን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለሚቀጥሉት አራት ሳምንታት ማራዘማቸው ይፋ ከኾነ በኋላ ነው። የሱሞ ስፖርት ጃፓን ውስጥ ከ9 ዓመታት በፊት ከተሰረዘ በኋላ የአኹኑ የመጀመሪያው ነው። እንደጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2011 የሱሞ ስፖርት ጃፓን ውስጥ ተሰርዞ የነበረው ተጋጣሚዎችን መደልደሉ ላይ በተከሰተ ቅሌት ነበር።

ማንተጋፍቶት ስለሺ