1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሮና ተሐዋሲ እና የጃፓን ኦሎምፒክ

ሰኞ፣ መጋቢት 14 2012

ጃፓን ውስጥ ሊካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት የዘንድሮው የቶኪዮ ኦሎምፒክ በተያዘለት ቀነ-ገደብ ይካሄድ አይካሄድ ዓለምን እያነጋገረ ነው። አንዳንድ ሃገራት በኮሮና ተሐዋሲ ፍራቻ ከጃፓን ኦሎምፒክ መውጣታቸውን ሲያስታውቊ፤ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ አትሌቶችን በውድድሩ ይሳተፉ አይሳተፉ ብርቱ እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተዋል።

https://p.dw.com/p/3ZvcJ
Japan Tokio Bahnhof Sendai Olympische Flamme
ምስል AFP/P. Fong

የመጋቢት 14 ቀን፤ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ


በዓለም ዙሪያ በርካታ ሃገራት ኮሮና ተሐዋሲ በፈጠረው የጤና ቀውስ የተነሳ የስፖርት ውድድሮችን በብዛት ሰርዘዋል፤ አለያም ደግሞ ጥቂት የሚባሉት በዝግ ስታዲየሞች ውስጥ ለማከናወን ተገደዋል። በዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች በጉጉት ከሚጠበቊት ክንዋኔዎች አንዱ የኾነው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ውድድርም ዘንድሮ የመካሄዱ ነገር ጥላ አጥልቶበታል። ጃፓናውያን ከረዥም ጊዜ አንስቶ ተጨንቀው ተጠበው ሲሰናዱበት የከረሙት የኦሎምፒክ ውድድር እንዲሰረዝ የሚፈልጉ አይመስሉም። አውስትራሊያን ጨምሮ ግን አንዳንድ ሃገራት ከወዲሁ ከውድድሩ ራሳቸውን ማግለላቸውን ይፋ አድርገዋል። ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ጃፓን ውስጥ ውድድሩ ይካሄድ አለያም ለሌላ ጊዜ ይዘዋወር በዚህ ሳምንት ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

ከ7 ዓመት በፊት በመስከረም ወር፦ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የዘንድሮውን የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ውድድር ጃፓን እንድታሰናዳ መመረጧን ይፋ ማድረጉን የጃፓን የቴሌቪዥን ጋዜጠኞች በእምባ ተውጠው ነበር የዘገቡት። ሠናይ ዜናውን የሰሙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ጃፓናውያን ደግሞ ደስታቸውን ለመግለጥ ወደ እየ አደባባዮቹ ለመጉረፍ አፍታም አልፈጀባቸውም ነበር። የውድድር ጊዜው እየተቃረበ ሲመጣ ግን የጃፓናውያኑን ጋዜጠኞች የደስታ እምባ ወደ ሐዘን የቀየረ ብርቱ ባላንጣ ዓለም ላይ ተደቀነ፤ የኮሮና ተሐዋሲ።

በዓለም ዙሪያ በርካታ ሃገራት የእግር ኳስ ጨዋታዎችን፤ የሩጫ ውድድሮችን እና ሌሎች ስፖርታዊ ፉክክሮችን በመሰረዝ ለተለያዩ ጊዜያት አስተላልፈዋል። የጃፓኑ የዘንድሮ ኦሎምፒክ ግን ገና የለየለት አይመስልም። የጃፓን ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል በኮሮና መያዛቸው ቢዘገብም ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ (IOC) ግን አኹንም ድረስ ውድድሮቹን ለማስኬድ ቊርጠኛ ይመስላል። እንደተለመደው ከግሪክ አቴንስ የሚለኮሰው የኦሎምፒክ ችቦ የፊታችን ሐሙስ ያላ ታዳሚዎች ጃፓን ቶኪዮ ይደርሳል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። በእርግጥ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ምን አይነት ለውጥ ሊከሰት እንደሚችል ባይታወቅም ማለት ነው።

ተምሳሌታዊው የኦሎምፒክ ችቦ መለኮስ ስርዓት በጃፓን ፉኩሺማ እንደሚከናወን እየተነገረ ነው። «የችቦ መለኮስ ስርዓቱ መጋቢት 17 ቀን፤ 2012 ዓ.ም ይጀምራል፤ የተቀየረ ዕቅድ የለም» ሲሉ የቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቶሺሮ ሙቶ ዛሬ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ በኮሮና ተሐዋሲ ምክንያት የኦሎምፒክ ውድድሩን ወደሌላ ቀን ስለማዛወር እያሰበበት መኾኑን ያስታወቀው ትናንትና ነበር።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቶሺሮ ሙቶ የኮሮና ተሐዋሲ ሥርጭት በዓለም ዙሪያ በፍጥነት እና በከፋ ኹኔታ እየተሠራጨ መኾኑን እንደሚገነዘቡት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ኾኖም የኦሎምፒክ ውድድሩ ማብሰሪያ ችቦ እንዲለኮስ የተወሰነው ከሳምንት በፊት መኾኑን በአኹኑ ወቅትም የተቀየረ ነገር እንደሌለ ዐስታውቀዋል። ከግሪክ የሚመጣውን የኦሎምፒክ ችቦ የአቀባበል ስርዓቱ አነስ እንዲል መደረጉም «ልብ የሚሰብር» መኾኑን ገልጠዋል። በአቀባበል ስርዓቱ ሰዎች በአንድ ቦታ ሰብሰብ የሚሉበትን አጋጣሚ ለማስወገድ የጃፓን የኦሎምፒክ ጨዋታዎች አዘጋጆች ወስነዋል።

ዓርብ ዕለት ይኖራል ተብሎ በሚጠበቀው ዝግጅት ይኖሩ ነበር የተባሉ 200 ግድም ሕጻናትም በቤታቸው እንዲቆዩ ይደረጋሉ ተብሏል። የኦሎምፒክ ችቦ መቀበል እና መለኮስ ስነስርዓቱ ሐሙስ ዕለት ይጀምራል ተብሎ ዕቅድ የተያዘለት ፉኩሺማ ከሚገኘው ጄ መንደር ከተሰኘው የስፖርት ማደራጃ ስፍራ ነበር። ጄ መንደር ከ9 ዓመት በፊት ጃፓንን ብርቱ ርእደ-መሬት ሲንጣት በተቀሰቀሰው ኃያል መውጅ እና የውቅያኖስ ግዙፍ ማዕበል የኒውክሌር አረር ማብለያው ማዕከል ጥፋት የተፈጸመበት ቦታ ነው።

የጃፓን ቶኪዮ ኦሎምፒክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቶሺሮ ሙቶ «ዋናው የችቦ ማብራት ስነስርዓት እከሚጀምርበት ሐሙስ ድረስ 3 ቀናት አሉን፤ ስለዚህ ለዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ዋና ኃላፊ ቶማስ ባሕ ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደምናደርገው ኹሉ ከእሳቸውም ጋር እንደምንወያይ ነግሬያቸዋለሁ። እሳቸውም ይኽን እንድናደርግ ነግረውናል» በማለት ለውድድሩ ጃፓን ቆርጣ መነሳቷን ተናግረዋል።

የጃፓን ጠቅላይ ሚንሥትር ሺንዞ አቤ በኦሎምፒክ ችቦ መለኮስ ዋናው ስነስርዓት ላይ ለመገኝት ጥርጣሬ እንደገባቸው እንደገለጡላቸው የጠቆሙት የጃፓን ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚደንትም ጠቅላይ ሚንሥትሩ ቆራጥ ውሳኔ እንዲያሳልፉ መናገራቸውን ዐስታውቀዋል። «ጠቅላይ ሚንሥትሩ መምጣት አለያም አለመምጣት አለባቸው ብሎ መናገር የእኛ ፈንታ አይደለም ብያቸዋለሁ። ስለዚህ እባካችሁ እንደ መንግሥት ውሳኔ አሳልፉ» ሲሉም አክለዋል።

ጃፓን የዘንድሮውን ውድድር ለማከናወን በኦሎምፒክ ኮሚቴዋ እና በመንግሥትዋ ውሳኔ መንታ መንገድ ላይ በተገኘችበት በአኹኑ ወቅት አንዳንድ ሃገራት እና አትሌቶች በውድድሩም ኾነ በዝግጅቱ ላይ እንደማይገኙ እየተናገሩ ነው። ነዋሪነቷን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያደረገችው ጃፓናዊት የእግር ኳስ ተጨዋች ናሆሚ ካዋሱሚ ከዚህ ቀደም ያደረግኹት ነገር ኮሮና ተሐዋሲን ለማሰራጨት ከፍተኛ ተጋላጭ ስላደረገኝ በሚል በችቦ መለኮስ ስነስርዓቱ ላይ እንደማትገኝ ዛሬ ዐስታውቃለች።
ይኽ በእንዲህ እንዳለ፦ የጃፓኑ ጠቅላይ ሚንሥትር የኮሮና ተሐዋሲ ግስጋሴ የማይገታ ከኾነ ጃፓን የቶኪዮ ኦሎምፒክን ወደ ሌላ ቀን ስለማዘዋወር ልታጤንበት ይገባል ሲሉ ዛሬ ተናግረዋል። ጃፓን የበጋ ኦሎምፒክን ለማከናወን «በተሟላ ኹኔታ ላይ የማትገኝ ከኾነ» ሀገሪቱ «ውድድሩን ወደ ሌላ ቀን ማዛወሩ ላይ ልታጤንበት ይገባል» ሲሉ በምክር ቤታቸው አጽንዖት ሰጥተዋል። ኾኖም ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴም ስለማይስማማበት ውድድሩን ሙሉ ለሙሉ መሰረዝ የሚለው አጀንዳቸው ውስጥ እንደሌለ ይፋ አድርገዋል። የዓለም ጤና ድርጅት ኮሮና ተሐዋሲ በዓለም ዙሪያ እየተሠራጨ መኾኑን ይፋ ባደረገበት ወቅትም ቢኾን ጃፓን ውድድሮቹን በእቅዷ መሰረት ለማስኬድ ሽር ጉድ ማለቷን ቀጥላበታለች። የቶኪዮ ኦሎምፒክ በተያዘለት ቀጠሮ ሊከናወን የቀረው 4 ወራት ብቻ ነበር። የኦሎምፒክ ውድድሮቹ ሐምሌ 17 ቀን 2012 በይፋ ተጀምረው ይጠናቀቃሉ ተብሎ በእቅድ የተያዘው ለነሐሴ 3 ቀን ነበር።

ከወዲሁ ግን ካናዳ እና አውስትራሊያ ከውድድሩ ራሳቸውን ማግለላቸውን ይፋ አድርገዋል። የካናዳ ኦሎምፒክ ኮሚቴ «በኮቪድ 19 ስጋት የተነሳ» በሚል የሀገሩ አትሌቶችን ወደ ቶኪዮ እንደማይልክ ዛሬ መግለጫ አውጥቷል። የአውስትራሊያ ኦሎምፒክ ኮሚቴም አትሌቶቹ ዘንድሮ መሰብሰብ እንደማይችሉ በመግለጥ ይልቊንስ ከአንድ ዓመት በኋላ ለሚደረግ የኦሎምፒክ ውድድር ተዘጋጁ ብሏል።

የቶኪዮ ኦሎምፒክ በኢትዮጵያም ውዝግብ ማስነሳቱ ተዘግቧል። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ «ለሁሉም አትሌቶችና አሰልጣኞች» በሚል ርእስ ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ፦ አትሌቶች በተዘጋጀላቸው ሆቴል ገብተው ልምምድ እንዲጀምሩ መወሰኑን ዐስታውቋል። ኦሎምፒክ ኮሚቴው ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው «ቅድመ ኹኔታዎች መሟላታቸውን ካረጋገጠ በኋላ» መኾኑን በመዘርዘር አራት ነጥቦችን አስፍሯል። አትሌቶቹ በተዘጋጀላቸው ሆቴል ካልገቡ «ለተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳይ ከተለያየ ሰው ስለሚገናኙ የመጠቃት ዕድል ከፍ ያለ ነው» ብሏል። ኮሚቴው ከመንግሥት እና ከጤና ጥበቃ ሚንሥትር ጋር በቅርበት እንደሚሠራ በመጥቀስ ያንንም ከግምት ውስጥ ማስገባቱን ጠቅሷል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ የስፖርት ጋዜጠኛው ዖምና ታደለ ዛሬ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ዋና ኃላፊ አቶ ስለሺ ብሥራት አትሌቶች እና አሰልጣኞች ወደ ሆቴል እንደማይገቡ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዚሁ ጉዳይ ላይ ዛሬ ስብሰባ ማድረጉ ተጠቅሷል። አዲስ አበባ ውስጥ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ አመራሮች ከአሰልጣኞች ጋር ባደረጉት የዛሬው ውይይት አትሌቶች እና አሰልጣኞች ለቶኪዮ ኦሎምፒክ ዝግጅት ወደ ሆቴል እንዳይገቡ የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን አቶ ስለሺ ጠቁመዋል፡፡ የኮሮና ተህዋሲ ወረርሽን የመቀነስ አዝማሚያ ካላሳየ እና መንግስት በውሳኔዎቹ ከፀናም አትሌቶቹን ወደ ሆቴል አንደማይልክ አቶ ስለሺ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በገባው ግጭት ምክንያት የወደፊቱ የሁለቱ ተቋማት ግንኙነት ምን ሊመስል ይችላል በሚለው ጉዳይ ላይ ምላሽ አንዲሰጡን ለዋና ፀሃፊው አቶ ዳዊት አስፋው ብንደውልም ስልካቸውን ሊያነሱ አልቻሉም፡፡

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፦ ኬንያ እና ኡጋንዳ ለውድድር ዝግጅት ማድረጋቸው ኢትዮጵያን ወደ ኋላ እንዳስቀራት አሳስቧል። ኮሚቴው አክሎም፦ «የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ቶኪዮ 2020 ዝግጅት በምንም ዓይነት መልኩ የማይሰረዝ ወይንም የማይራዘም መኾኑን በማረጋገጡ» የተነሳ ውሳኔ ማሳለፉን ጠቊሟል።

ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ውድድሩን ለማራዘም ውሳኔ የሚያሳልፍ ከኾነ ጃፓን ዝግጁ መኾኗን እና ያንንም እንደምትቀበል ኪዮዶ የተሰኘ የዜና ወኪል መዘገቡን ሮይተርስ የዜና ምንጭ ዛሬ አትቷል። የዩናይትድ ስቴትስ አትሌቶች በሀገሪቱ የኦሎምፒክ እና ፓራሊምፒክ ኮሚቴ በተዘጋጀው ከርቀት ድምፅ የመስጠት ሒደት በቶኪዮ ኦሎምፒክ በአኹኑ ወቅት የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌላቸው ማሳየታቸውን የሀገሪቱ መገናኛ አውታሮች ትናንት ዘግበዋል።

ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው በትዊተር ገጻቸው፦ የዩናይትድ ስቴትስ ኹነኛ ወዳጅ ሲሉ የጠቀሷቸውን የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ውሳኔ እንደሚቀበሉ ጽፈዋል። ጃፓን ውስጥ የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን ለማሰናዳት ድንቅ ሥራ ሠርተዋል በማለትም፦ «እሳቸው ትክክለኛ ውሳኔ ያሳልፋሉ» በማለት ዛሬ ከሰአታት በፊት ጽፈዋል ዶናልድ ትራምፕ።

የፈረንሳይ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቶኪዮ ኦሎምፒክ ውድድር መራዘሙ የማይቀር ነው ብሏል። በዚህም አለ በዚያ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ውሳኔውን በቅርቡ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

እግር ኳስ

በጀርመን የእግር ኳስ ውድድሮች ለጊዜው በተራዘሙበት በአኹኑ ወቅት ስለ እግር ኳስ እና ስርዓት አልባ ደጋፊዎች ትችቶች ተጽፈዋል። በተለይ የሆፈንሃይም እግር ኳስ ባለሐብት ዲትማር ሆፕ ላይ ያነጣጠሩ የግለሰብ መብትን የሚጥሱ የእግር ኳስ ታዳሚዎች መረን የለቀቊ ተቃውሞዎች ትችት ተሰንዝሮባቸዋል። በጀርመን የእግር ኳስ ቡድኖች ደጋፊዎች ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ክፍል ኃላፊ ሚሻኤል ጋብሪኤል፦ በጀርመን የደጋፊዎች ስርዓት የጣሱ ተቃውሞዎች ቀደም ሲሉም የነበሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። በተለይ ከ40 ዓመታት በፊት ይንጸባረቊ የነበሩት የደጋፊዎች ልማድ «እጅግ በዓመጽ የተሞሉ ብቻ ሳይኾኑ በዘረኝነት የተቃኙ ነበሩ» ብለዋል። ያ ኹኔታ አኹን መሻሻል ያሳየ ቢኾንም በግለሰቦች ላይ የሚሰነዘረው ተቃውሞ ግን መስመሩን እየሳተ መኾኑን ጠቊመዋል።

«በሻልከ ቡድን እንደታየው አይነት ዘረኛ ስድቦች የሚሰነዘሩት ከደጋፊዎች በኩል ሳይኾን ከስታዲየሙ ሌላኛው አቅጣጫ ነው። ስለዚህ ዘረኝነት በጽንፈኞች ብቻ የሚፈጸም ሳይኾን ከማኅበረሰቡ መሀልም የሚገኝ ነው።»

የእግር ኳስ ደጋፊዎች የስነምግባር ጥሰት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲበጅለት በተደጋጋሚ ሲጠየቅ ቆይቷል።

ከእግር ኳስ ዜና ሳንወጣ፦ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ ኩባንያ ዛሬ አዲስ አበባ የፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ውስጥ በሰጡት የጋራ መግለጫ በኮሮና ተሐዋሲ የተነሳ የእግር ኳስ ቡድኖች በአጠቃላይ ልምምዳቸውን በአፋጣኝ እንዲያቆሙ ወስኗል። ለሁለት ሳምንት ተራዝሞ የነበረው የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግም ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ተጠቅሷል።

የኮሮና ተሐዋሲ በአፍሪቃም በርካታ የእግር ኳስ እና ሌሎች የስፖርት ውድድሮች ብሎም ስብሰባዎች ወደሌላ ቀናት እንዲዛወሩ አስገድዷል። ካሜሩን ጥር እና የካቲት ወር ላይ ልታካሂድ የነበረው የአፍሪቃ ዋንጫ ለኹለት ጊዜያት ተሸጋሽጓል። ወደ የካቲት ተዘዋውሮ የነበረው ውድድር ካሜሩን ውስጥ በኮሮና ተሐዋሲ የተያዙ 10 ሰዎች መኖራቸው በመነገሩ በድጋሚ ውድድሩ ለሌላ ጊዜ ተዛውሯል።

KOS - Michael Gabriel
ምስል picture-alliance/dpa/F. Rumpenhorst
Kanada Olympia
ምስል picture-alliance/empics/T. Martin
Japan Tokio Bahnhof Sendai Olympische Flamme
ምስል Reuters/Kyodo
Athen Entzündung der Olympischen Flamme
ምስል AFP/A. Messinis

 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ