1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመጋቢት 06 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መጋቢት 6 2013

ዋሊያዎቹ ከነገ በስትያ ባሕር ዳር ውስጥ ነበልባሎቹን ይገጥማሉ። ነገ እና ከነገ በስትያ የጀርመን ሁለት ቡድኖች ለሻምፒዮንስ ሊግ ሁለተኛ ዙር ግጥሚያቸውን ያከናውናሉ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ፉክክር ማንቸስተር ሲቲን የሚያቆመው አልተገኘም። ሆዜ ሞሪኞ በሰሜን ለንደን ደርቢ ግጥሚያ በአርሰናል ለተረታው ቡድናቸው የመሀል ዳኛውን ተጠያቂ አድርገዋል።

https://p.dw.com/p/3qf69
Fußball Bundesliga | Arminia Bielefeld - Bayer Leverkusen
ምስል Ina Fassbender/AFP/Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ዋሊያዎቹ ከነገ በስትያ ባሕር ዳር ውስጥ ነበልባሎቹን ይገጥማሉ። ነገ እና ከነገ በስትያ የጀርመን ሁለት ቡድኖች ለሻምፒዮንስ ሊግ ሁለተኛ ዙር ግጥሚያቸውን ያከናውናሉ። አንደኛው የማለፍ ዕድሉ ጠባብ ነው። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ፉክክር ማንቸስተር ሲቲን የሚያቆመው አልተገኘም። ሆዜ ሞሪኞ በሰሜን ለንደን ደርቢ ግጥሚያ በአርሰናል ለተረታው ቡድናቸው የመሀል ዳኛውን ተጠያቂ አድርገዋል። የኤሪክ ላሜላ ድንቅ ግብ ለቶትንሀም ሆትስፐር ደጋፊዎች ቢሸነፉም ብርቱ ማጽናኚያ ኾኗል። ክርስቲያኖ ሮናልዶ በሳምንቱ መገባደጃ በሠራው ሔትትሪክ አጠቃላይ አጠቃላይ ግቦቹን ከፔሌ ማስበለጥ ችሏል። ፔሌ ክርስቲያኖ ሮናልዶን ለስኬቱ «እንኳን ደስ ያለህ» ብሎታል።

ዋሊያዎቹ ከነበልባሎቹ

ዋሊያዎቹ ከነገ በስትያ ባሕር ዳር ውስጥ ነበልባሎቹን ይገጥማሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ከማላዊ ቡድን (ነበልባሎቹ)ጋር ረቡዕ፤ መጋቢት 8 ቀን፣ 2013ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት የወዳጅነት ጨዋታ ለማከናወን ባሕር ዳር ስታዲየም ውስጥ ተቀጣጥረዋል።  ብሔራዊ ቡድኑ በአፍሪቃ ዋንጫ ከማዳጋስካር እና አይቮሪኮስት ጋር የምድብ ማጣሪያ ወሳኝ ጨዋታዎች ይኖሩታል። የማላዊ ቡድን ተጨዋቾች፦ መጋቢት 6 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተው አንድ ምሽት በአዲስ አበባ ካሳለፉ በኋላ ማክሰኞ መጋቢት 7 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ወደ ባሕር ዳር እንደሚጓዙ ፌዴሬሽኑ ገልጧል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፦ ፎቶ ከማኅደራችን
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፦ ፎቶ ከማኅደራችን ምስል DW/O. Tadele

ዋሊያዎቹ ማረፊያቸውን አስቀድመው ባሕር ዳር ከተማ አቫንቲ ሆቴል ውስጥ በማድረግ ዝግጅታቸውን ማጠናከራቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዐስታውቋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገዋል። ለቀጣይ የማጣሪያ ግጥሚያዎቹ ከውጭ ሃገር በብቸኝነት ወደ ብሔራዊ ቡድኑ የተጠራው አማካዩ ሽመልስ በቀለ ይጠበቃል። ለግብጹ ኤል መቃሳ የሚጫወተው ሽመልስ በኤል መቃሳ ቡድን የየካቲት ወር ኮከብ ተጫዋች ሆኖ በመመረጡ፤ አሁን ደግሞ ለብሔራዊ ቡድኑ በመጠራቱ ደስታውን በትዊተር የማኅበራዊ መገናኛ አውታሩ ገልጧል።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ ማንቸስተር ሲቲ በ71 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ሰፍሮ ለብቻው እየገሰገሰ ነው። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንቸስተር ዩናይትድ በ57 ነጥብ ይከተለዋል። ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት ዌስትሀም ዩናይትድን 1 ለ0 አሸንፏል። ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ላይስተር ሲቲ በ5 ግቦች በተንበሸበሸበት የቅዳሜ ዕለት ግጥሚያው ነጥቡን 56 ማድረስ ችሏል። ቸልሲ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቶ ነጥብ ተጋርቷል፤ 51 ነጥብ ይዞ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የአውሮጳ ሊግ ደረጃን የያዘው ዌስት ሀም ኤቨርተንን በ2 ነጥብ በልጦ በ48 ነጥቡ አምስተኛ ደረጃውን አስጠብቋል።  ከቶትንሀም በሦስት ነጥብ ተበልጦ ወደ ስምንተኛ ደረጃ ያሽቆለቆለው ሊቨርፑል ከዎልቭስ ጋር ዛሬ ማታ ይጋጠማል። ካሸነፈ ለጊዜው የኤቨርተንን ቦታ ተረክቦ 6ኛ ደረጃን ይይዛል። ኤቨርተን እና ቶትንሀም ተስተካካይ ጨዋታቸውን ካሸነፉ ሊቨርፑል ወደ ነበረበት ስምንተኛ ይመለሳል።

UK Timo Werner Jubel | Chelsea gegen Souththampton
ምስል Matthew Childs/AFP/Getty Images

በኳስ ቊጥጥር እና አጠቃላይ ይዞታ በመጀመሪያው አጋማሽ ከቶትንሃም ሆትስፐር ልቆ የታየው አርሰናል ትናንት በሜዳው ኤሚሬትስ ስታዲየም 2 ለ1 አሸንፏል። አርጀንቲናዊው አማካይ ኤሪክ ላሜላ በአርሰናል አምስት ተጨዋቾች መካከል ግራ እግሩን በቀኝ ተረከዙ በኩል አዙሮ የመታት እና በድንቅ ኹኔታ ከመረብ ያረፈችው (ራቦና)ግብ ለረዥም ጊዜ የምትታወስ ናት። አርሰናል በ33ኛው ደቂቃ ላይ በተቆጠረበት ግብ ሲመራ ቢቆይም በርካታ ሙከራዎችን አድርጓል።

በሁለተኛው አጋማሽ 44ኛው ደቂቃ ላይ ማርቲን ዴጋርድ አቻ የምታደርገውን ግብ ማስቆጠር ችሏል። ቶትንሀም ጨዋታውን መቆጣጠር በጀመረበት ወቅት 64ኛው ደቂቃ ላይ የተሰጠው ፍጹም ቅጣት ምት ተገቢ እንዳልሆነ የቶትንሀም አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪኝሆ ተናግረዋል። የመሀል ዳኛው የሰጡትን የፍጹም ቅጣት ምትም የተሳተ ውሳኔ ብለውታል። አሌክሳንደር ላካዜት ፍጹም ቅጣት ምቱን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። ቀዳሚዋን ግብ በድንቅ ኹኔታ ያስቆጠረው ኤሪክ ላሜላ 76ኛው ደቂቃ ላይ ባየው ሁለተኛ ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

ፉልሃም፣ ዌስትብሮሚች እና ሼፊልድ ዩናይትድ 26፣ 18 እና 14 ነጥብ ይዘው ከ18ኛ እስከ 20ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባየር ሙይንሽን ከነገ በስትያ ለሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታውን ያከናውናል። በመጀመሪያው ግጥሚያ ባየርን ሙይንሽን የጣሊያኑ ላትሲዮን 4 ለ1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ድል አድርጓል። በቡንደስሊጋው ቅዳሜ ዕለት ቬርደር ብሬመንን 3 ለ1 በማሸነፍ ነጥቡን 58 አድርሷል። በ3 ነጥብ ልዩነት የሚከተለው ላይፕትሲሽ ትናንት ከአይትራኅት ፍራንክፉርት ጋር አንድ እኩል በመለያየት  ከባየር ሙይንሽን ጋር ይኖረው የነበረውን የ2 ነጥብ ልዩነት ወደ አራት ከፍ አድርጎታል። ላይፕትሲሽ ከሻምፒዮንስ ሊጉ ባሳለፍነው ሳምንት በሊቨርፑል ደርሶ መልስ ግጥሚያ 4 ለ0 ተሸንፎ ተሰናብቷል።  

Bundesliga - RB Leipzig v Eintracht Frankfurt
ምስል Ronny Hartmann/REUTERS

ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዘንድሮ ከሻምፒዮንስ ሊግ ፉክክር ይልቅ በቡንደስሊጋው እስከ አራተኛ ደረጃ ጨርሶ ለቀጣይ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነት ላይ እንሚያተኩር የቡድኑ ኃላፊዎች ገልጠዋል። በቡንደስሊጋው 42 ነጥብ ይዞ የአምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዶርትሙንድ በአይንትራኅት ፍራንክፉርት በ2 ነጥብ ይበለጣል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቡንደስሊጋው ላይ ከማተኮሩም ባሻገር ዋና አጥቂው የ20 ዓመቱ ወጣት ኧርሊንግ ኦላንድ ወደ ሌላ ቡድን እንዳይኼድበት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግም ዐስታውቋል። አይንትራኅት ፍራንክፉርት 44 ነጥብ ይዞ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከቮልፍስቡርግ በ4 ነጥብ ይበለጣል።

በሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ በመጀመሪያው ዙር በማንቸስተር ሲቲ 2 ለ0 የተሸነፈው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ የመልሱን ጨዋታ ነገ ማታ ያከናውናል። በቡንደስሊጋው ውጤት ርቆት 33 ነጥብ ብቻ ይዞ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ዐርብ ዕለትም በአውግስቡርግ የ3 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል። ሔርታ ቤርሊን እና ማይንትስ በተመሳሳይ 21 ነጥብ ግን በግብ ክፍያ ልዩነት 16ኛ እና 17ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ዘንድሮ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን መሰናበቱን ከወዲሁ ያረጋገጠው ሻልከ 10 ነጥብ ብቻ ይዞ ደረጃው 18ኛ ነው። ቅዳሜ ዕለት በቮልፍስቡርግ የ5 ለ0 ውርጅብኝ ገጥሞታል።

ሮናልዶ ያገባቸው ግቦች ከፔሌ በለጡ

ብራዚላዊው የኳስ ንጉሥ ፔሌ በጨዋታ ዘመኑ ካገባቸው ግቦች ፖርቹጋላዊው አጥቂ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በ3 በመብለጡ «እንኳን ደስ ያለህ» ሲል መልእክት ልኮለታል። ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ቡድኑ ጁቬንቱስ ካግሊያሪን 3 ለ1 ባሸነፈበት የቅዳሜ ዕለቱ ግጥሚያ ሦስቱንም ከመረብ በማሳረፍ ሔትትሪክ ሠርቷል። በዚህም አጠቃላይ ከመረብ ያረፉ ኳሶቹን 770 ማድረስ ችሏል። ፔሌ 767 ግቦች አሉት።

Fußball UEFA Champions League Ajax Amsterdam - Juventus FC
ምስል Imago Images/Beautiful Sports

በዓለም የእግር ኳስ ታሪክ ቀድሞ ለኦስትሪያ እና ቼኮዝላቫኪያ ይጫወት የነበረው አጥቂ ጆሴፍ ቢቻን ላይ የሚደርስ አልተገኘም። ጆሴፍ ቢቻን በጨዋታ ዘመኑ 805 ግቦችን ማስቆጠር የቻለ አስደናቂ ተጨዋች ነው። በአማተር ተጫዋችነት ዘመኑ እና ፕሮፌሽናል ሳይሆን ባከናወናቸው 27 ግጥሚያዎች ያስቆጠራቸው ግቦቹ ሲቀነሱ ግን አጠቃላይ ከመረብ ያሳረፋቸው ኳሶች 759 ናቸው። ከፔሌ እና ከክሪስቲያኖ ሮናልዶ የሚያንሰውም በትንሹ ነው።

በሻምፒዮንስ ሊጉ ግጥሚያ በፖርቱ ለጥቂት የተሰናበተው ጁቬንቱስ በሴሪ ኣው ተሳክቶለት የሦስተኛ ደረጃውን አስጠብቋል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ከመሪው ኢንተር ሚላን የሚበለጠው በ10 ነጥብ ነው። 56 ነጥብ ካለው ኤሲ ሚላን ደግሞ በአንድ ነጥብ ብቻ ይበለጣል። የፊታችን እሁድ ከቤኔቬንቶ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ካሸነፈ በ58 ነጥብ የሴሪኣውን የሁለተኛ ደረጃን ይረከባል። ቤኔቬንቶ 26 ነጥብ ይዞ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ የቀረው ቶሪኖ በ20 ነጥብ፤ ፓርማ በ19 እንዲሁም ክሮቶኔ በ15 ነጥብ ከ18ኛ እስከ 20ኛ ደረጃ ይዘዋል። አታላንታ እና አንድ ተስተካካይ ግጥሚያ የሚቀረው ናፖሊ በ52 እና 50 ነጥብ በ4ኛ እና 5ኛ ደረጃ ላይ ሰፍረዋል።

Champions League I Liverpool v RB Leipzig
ምስል Bernadett Szabo/REUTERS

ባርሴሎና የማንቸስተር ሲቲው አጥቂ የ32 ዓመቱ ሠርጂዮ አጉዌሮን ለማስፈረም ጫፍ መድረሱን ኖይስትሮስ ሶሺዮስ ዘግቧል። የባርሴሎና ተመራጭ ፕሬዚደንት ዮዋን ላፖርታ አጥቂውን በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ወደ ካምፕ ኑ ስታዲየም ለማስመጣት ስምምነት እየተጠናቀቀ መሆንን ዐስታውቀዋል። ሠርጂዮ አጉዌሮ ወደ ባርሴሎና የሚመጣው በነጻ ዝውውር መሆኑም ተጠቅሷል። ስምምነቱ የሚጠናቀቀው ግን የባርሴሎና ተመራጭ ፕሬዚደንት ሥልጣናቸውን ሲረከቡ ብቻ መሆኑን ተገልጧል። የቡድኑ ፕሬዚደንት በሌሉበት በአሁኑ ወቅት ባርሴሎናን በጊዜያዊ ፕሬዚደንትነት የሚመሩት ቻርሌስ ቱስኩዌትስ ናቸው። የባርሴሎና ተመራጭ ፕሬዚደንት ዮዋን ላፖርታ ሠርጂዮ አጉዌሮን ማስፈረማቸው የቦሩስያ ዶርትሙንዱ አጥቂ ኧርሊንግ ኦላንድን ለማስመጣት የጀመሩት እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ እንደሌለው ተናግረዋል። ሠርጂዮ አጉዌሮ ከሰባት ዓመታት በፊትም ወደ ባርሴሎና ሊዛወር ጫፍ ደርሶ በወቅቱ ቡድኑ ሉዊስ ሱዋሬዝን በማስመጣቱ ሳይሳካ ቀርቷል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ