1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ማኅበር ለጠ/ሚኒስትሩ ደብዳቤ ፃፈ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 16 2014

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ማኅበር መንግሥት ለመገናኛ ብዙኀን ችግሮች መፍትሄ እንዲሰጥ ለጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ደብዳቤ ላከ። ማኅበሩ የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ከቤታቸውና ከሥራ ገበታቸው በጸጥታ ኃይሎች መታፈናቸው እንዳሳሰበው፤ ጠ/ሚሩ ይህን ከፍተኛ የሕግ ጥሰት ሰምተው እንዳልሰሙ መሆናቸው እንዳሳዘነዉ ለጠ/ሚሩ ደብዳቤ ፅፎአል።

https://p.dw.com/p/4BoGj
Ethiopian Mass Media Professionals Association
ምስል Ethiopian Mass Media Professionals Association

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ማኅበር መንግሥት ለመገናኛ ብዙኀን ችግሮች መፍትሄ እንዲሰጥ ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ደብዳቤ ላከ ። ማኅበሩ የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ከቤታቸውና ከሥራ ገበታቸው በጸጥታ ኃይሎች መታፈናቸው እንዳሳሰበው ገልጾ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ከፍተኛ የሕግ ጥሰት ሰምተው እንዳልሰሙ መሆናቸው እንዳሳዘነዉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፈዉ ደብዳቤ ጠቅሶአል። መንግሥት ጋዜጠኞችን በሕግ አግባብ ብቻ እንዲጠይቅ እና ጋዜጠኞችን ያፈኑ አካላትም ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቋል። 
በ2010 ዓ.ም. በሀገራችን ከመጣው መንግሥታዊ ለውጥ በፊት በርካታ ጋዜጠኞች በሥራቸው ምክንያት የተለያየ ዛቻና ማስፈራሪያ እና ድብደባ ከፍ ሲል ደግሞ ያለፍርድ ቤት ማዘዣ በሕግ ቁጥጥር ስር መዋልና በእስር ቤቶች ውስጥ ያለምንም ክስ ለወራት ወይም ለዓመታት ታስረው ይለቀቁ እንደነበረዉ ያስታወሰዉ ማኅበሩ፤ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ኢትዮጵያን የመገናኛ ብዙኃን ጠላት እንዲሁም ለጋዜጠኞች የስቃይ ምድር ብሎ እስከመጥራት ደርሶ እንደነበር ገልፆአል። በብዙ ትግልና መስዋዕትነት ወደስልጣን የመጣው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ግን በወቅቱ ባሳየው ከፍተኛ ቁርጠኛ አቋም ምክንያት ለሕዝብ በመወገናቸው ብቻ እንደፖለቲከኛ ተቆጥረው የታሰሩ ጋዜጠኞችን ሁሉ ከእስር በመልቀቁ ሀገራችን አንድም ጋዜጠኛ ያልታሰረባት ሀገር በሚል ስሟ በመታደሱ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለኢትዮጵያ የ2012 ዓ.ም. የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን አዘጋጅ እንድትሆን እድሉን እስከመስጠት አድርሶትም ነበር ሲል ማኅበሩ አስታዉሶአል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በስልጣን ዘመናቸዉ ዕውነተኛ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ካላቸዉ ጽኑ ፍላጎት የተነሳ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በነጻነት ስራቸውን እንዲሰሩ እንደሚያደርጉ እና በጋዜጠኞች ላይ ምንም አይነት እንግልት እንደማይደርስ ቃል በመግባታቸዉ በጋዜጠኛው ላይ ከፍተኛ የሆነ የሞራል (ተነሳሽነት) በየመገናኛ ብዙኃኑ ፈጥሮ እንደነበር ማኅበሩ በላከዉ ደብዳቤ ጠቅሶአል። 
በ2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በተደረገው ሀገራዊ ምርጫ እና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተቀሰቀሰው ጦርነት ላይ የተሳተፉ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ስኬታማ ሥራ ያከናወኑ በመሆናቸዉ ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግላቸዉ  “ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች” የሚል የምስጋና መርሐ ግብሮች አዘጋጅተዉ እንደነበር በደብዳቤዉ ተወስቶአል።  
በዚህም ምክንያት ከጎረቤት ሀገር ኤርትራ ጋር ሰላም እንዲፈጠር ባደረጉት ከፍተኛ ስኬት ጋር ለመገናኛ ብዙኃን የሰጡትን ልዩ ትኩረት እና ነጻነት አንድ ላይ ተደምሮ የኖቤል የሰላም ሽልማት እንዲያገኙ ምክንያት መሆን ማኅበሩ ጠቅሶአል፡፡ የፕሬስ ነጻነትን የሚጋፉ ዝንባሌዎችና ድርጊቶች የባለሙያዎችን የሚዛናዊነትና የገለልተኛነት መብት እንደሚጋፉ፣ ዜጋውንም እንደሚያሸማቅቁ፣ በሀገራችን የዲሞክራሲ ሥርዓት ልምምድ ላይም ጥቁር ጥላ እንደሚያጠላ በመግለጽ ይህ አዝማሚያ በፍጥነት መፍትሔ እንዲበጅለት፤ ካልሆነ ግን ይህ አደገኛ አካሄድ ሀገራችንን ከቀደመው ወደባሰ ብልሹ የመንግስት አስተዳደር ሊመልሳት እንደሚችል ያለውን ስጋት ማሕበራችን ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች ሲገልጽ ቆይቷል ፤ሆኖም ግን ጩኸታችን ሰሚ አግኝቶ መሻሻል ከማሳየት ይልቅ ከድጡ ወደማጡ እየተቀየረ መጥቷል  ሲል ማህበሩ   ለጠ /ሚኒስትር (ዶ/ር)ዐብይ አሕመድ አሳሳቢ ለሆነው የመገናኛ ብዙኃን ችግሮች መፍትሔ እንዲሰጡ በጠየቀበት ረዘም ባለ ደብዳቤ ይፋ አድርጓል።  
 

ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ 

ሸዋዬ ለገሰ