1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመን፣የሚጀመር የማይልቅባት፣የሚያልቅ የማይጀመርባት ሐገር

ሰኞ፣ ኅዳር 20 2014

ሌላዉ ቀርቶ ተፋላሚ ኃይላት የጦር ወንጀል መፈፀም አለመፈፀማቸዉን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ኮሚሽን እንዲያጣራ፣ ለድርጅቱ የሰብአዊ ጉዳይ ምክር ቤት የቀረበዉ ረቂቅ ደንብ እንዳይፀድቅ የዩናይትድ ስቴትሷ-ሳዑዲ አረቢያ፣ በሳዑዲ አረቢያዋ ባሕሬን በኩል ዉድቅ አስደርጋዋለች።

https://p.dw.com/p/43dPi
Saudi-arabischer Luftangriff auf Sanaa
ምስል Hani Al-Ansi/picture alliance/dpa

የየመን ጦርነት ቀጥሏል፣ጦርነቱን ለማስቆም የሚገባዉ ቃል እስካሁን መክኗል

ብሪታኒያዊዉ ዲፕሎማት ማርቲን ግሪፊቲስ የየመን ተፋላሚ ኃይላትን ማግባባት፣የሳዑዲ መራሹን ጦር ጣልቃገብነት ማስቀረት፣ እና  አዉዳሚዉን ጦርነት ማስቆም አይገድም ብለዉ ነበር።ታሕሳስ 2018 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) አንጋፋዉ ዲፕሎማት ለተልዕኳቸዉ ስኬት ከአደን-ሰነዓ፣ ከሪያድ ቴሕራን፣ ከካይሮ-ስቶክሆልም፣ ከጄኔቭ ኒዮርክ ተሽከረከሩ።ሶስት ዓመት።በሶስተኛ ዓመታቸዉ አምና ኃምሌ የመንን በቃሺኝ-በቃሁሽ ብለዉ ከዓለም አቀፉ የሰብአዊ ርዳታ ድርጅት ማስተባባሪያ አናት ላይ ፊጥ አሉ።ከግሪፊቲስ በፊት የሞሮኮዉ ዲፕሎማት ጀማል ቤን ዑመር እና ፣የሞሪታኒያዉ ኢስማኢል ዑሉድ ሼክ አሕመድ ብሪታኒያዊዉ ዲፕሎማት የሞከሩትን ሞክረዉ በበቃኝ ተሰናብተዋል።አሁን ተረኛዉ ሲዊድናዊዉ ሐንስ ግሩንድ በርግ ናቸዉ።ዲፕሎማት ሥልጣን ይለቃል እንጂ ተስፋ አይቆርጥም።የመንም ያልቃል እንጂ ዉጊያ አላቆመም።የየመን ማብቂያ ያጣ ጦርነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁኝ ቆዩ
                                           
የ37 ዓመቱ ጎልማሳ ሙስጠፋ መሐመድ የዋሽግተን-ለንደን ታማኞች-የሪያድ-አቡዳቢ ነገስታት፣ከዋሽግተን ለንደን ጠላቶች ከቴሕራን አያቱላሆች ጋር የሚሻኮቱበትን ሰበብ ምክንያትን በቅጡ አያዉቀዉም።የሚያቅ-የሚያስተነትንበት አቅም፣ዕዉቀት ፍላጎትም የለዉም።የሚያዉቀዉ የሪያድ-አቡዳቢ ነገስታት በቀጥታ፣የቴሕራን፣ ዋሽግተን ለንደን መሪዎች በተዘዋዋሪ የመን ላይ የለኮሱት እሳት ሐገሩን ማዉደም፣ ወገኖቹን መፍጀቱን እሱና ብጤዎቹን መድረሻ ማሳጣቱን ነበር።ተፈናቀለ።ተሰደደም።

ዓላማ፣ ዕቅድ፣ ምኞቱ በዝርዝር አይታወቅም።ግን ያዉ አንደ አብዛኛዉ ስደተኛ ያቺን የጥንታዊ ሥልጣኔ፣ የዘመኑ ስይጣኔ አብነት ሐገሩን ጥሎ መሸሸ፣ ከአዉሮጳ ሐገራት ባንደኛዉ መኖር፣ እራሱን ዉላጅ-ወዳጅ ዘመዱን ከመርዳት ብዙም አይዘልም።አዉሮጳ ገባ-ቤሎሩስ ገሚስ ስኬት።ግን ለዋሽግተን-ለንደን፣ ለሪያድ አቡዳቢ-ቴሕራን ጥቅም፣ስልጣንና ስኬት የምትነድ ሐገሩን ጥሎ የሸሸዉ ጎልማሳ በብራስልስ-ዎርሶ ሚኒስኮች ጠብ ሰበብ ቤሎሩስና-ፖላንድ ድንበር ላይ በብርድ-ረሐብ ሲቋራመድ ለየመን ሰላም «ለፋሁ» የሚሉት የግሪፊቲስ ድርጅት ዳቦ-ብርድ ልብስ አልሰጠዉም። በቀደም ሞተ።የሙስጠፋ መሐመድ ሙርሺድ አል-ራሚ ታሪክ አበቃ።እዚያዉ የመን በጦርቱ ሰበብ በሞትና-በመኖር መሐል የተቃረጡ ተፈናቃይ ወገኖቹ ግን ዛሬም እንደ እስከዛሬዉ ይጮኻሉ።የአምስቶቹ አባት ሐሰን ጀዓፈር ሐሰን አንዱ ነዉ።

Jemen Die gefährlichen Straßen der Stadt Taiz
ምስል Ahmed Al-Basha

«ይዘን የወጣ ነዉ ልብሳችንን ብቻ ነዉ ይዘን የወጣነዉ።በጭነት መኪና እንደ እንሰሳ፣እንደከብት ተጭነን ነዉ እዚሕ የደረስነዉ።ከኛ ሌላ ሌሎች ስምንት ቤተሰቦችም አብረዉን ተሰደዋል።ከሰፈራችን ሌሊት ነዉ የወጣነዉ።ይሕቺን የመሳሰሉና ከስዋም ያነሱ ሕፃናት ይዘናል።እዚሕ በመድረሳችን ፈጣሪን እናሰመሰግናለን።»
ሰሞኑን ጦርነቱ ካየለበት ከማሪብ ግዛት ተሰድደዉ የደረሱበት በመድረሳቸዉ ፈጣሪያቸዉን አመሰገኑ።የእሕል ዉኃ ጥያቄያቸዉ ግን ገና መልስ አላገኝም።ለጊዜዉ የሚረዳቸዉ የብሔራዊ ተቋቁሞ የሰብአዊ ርዳታ ሕዋስ የተባለ የአካባቢዉ ድርጅት ነዉ።ሐሰን ጀዓፈር ሐሰን እንደሚለዉ ድርጅቱ በቂ ርዳታና መጠለያ ማቅረብ አልቻለም።
«እየተሰቃየን ነዉ።ወዳጄ።ገንዘብ የለንም።ገቢ የለንም።የምንቃመሰዉ እነሱ የሚሰጡንን ምግብ ነዉ።የሚሰጡን ምግብ በጣም ትንሽ ነዉ።ተጨማሪ ምግብ ልንጠይቃቸዉ አንችልም። ሕፃናቱ ወተት፣ብስኩት፣ ጭማቂ እና ሌሎች ነገሮች ይጠይቁናል ምን እንስጣቸዉ።ብዙ ነገር ይፈልጋሉ።»

ብዙ ነገር።ከሁሉም በላይ ሰላም ይፈልጋሉ።ሰላም ግን የለም።የሳዑዲ አረቢያ ነገስታት መጋቢት በ2015 የመንን ሲወሩ በሳምንታት ግፋ ቢል በወራት ዕድሜ ሰነዓን ለመቆጣጠር ፎክረዉ ነበር።የዩናይትድ ስቴትስና የብሪታንያ ዘመናይ ጦር መሳሪያ፣ዕዉቅ የጦር አማካሪ፣ በሳል የስለላ መረጃ ማዓለት ወሌት የሚጎርፍላቸዉ የሳዑዲ አረቢያ፣የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣የግብፅ የሌሎች አምስት ሐገራትና የየመን ስደተኛ መንግስት ወታደሮች ያቺን ታሪካዊ፣ዉብ፣የጉጥ-ስርጓጉጥ ሐገር እነሆ ለሰባተኛ ዓመት እያጋዩዋት ነዉ።
ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማንና ተባባሪዎቻቸዉ በወራት እድሜ ከሰነዓ ጠራርገዉ ሊያስወጧቸዉ የዛቱባቸዉ የሁቲ ወይም የአንሳር አላሕ አማፂያን ግን ዛሬም ከግማሽ የሚበልጠዉን የየመን ግዛት እየተቆጣጠሩ ነዉ።በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት አማፂያን ከየመን አልፈዉ የትልቂቱን ሐብታም ሐገር ተቋማት እያጋዩ ነዉ።የሁቲ ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች ባለፈዉ ሳምንት ብቻ 14 የሳዑዲ አረቢያ ተቋማትን ወይም አካባቢዎችን ማጥቃታቸዉን አስታዉቀዋል።
ሰሞኑን ደግሞ የየግንባሩ ዉጊያ፣የአዉሮፕላን ቦምብ ሚሳየሉ ድብደባም ከፍቷል።ፉከራዉም እንደዚያዉ።በሳዑዲ አረቢያ የሚደገፈዉ የስደተኛዉ የአብድ ረቦ መንሱር ሐዲ መንግስት ጦርና ተባባሪዎቹ የሁቲዎችን ሕልቅጥ ለመጥረቅ ተቃርበናል ይላሉ።እሱ ተራ ወታደር ነዉ።ለመዛት መፎከር ግን አላነሰም።

Jemen Huthis in Sanaa
ምስል Hani Al-Ansi/dpa/picture alliance

«ከሞቅባና በስተሰሜን፣ ከሰቅም ፊትለፊት የሚገኙትን ተራሮች ነፃ አዉጥተናል።ወደፊት እየገፋን ነዉ።ሁቲዎች እየሸሹ ነዉ።ሰዓዳ ግዛት ከሚገኘዉ ጠንካራ ምሽጋቸዉ ማራን ተራራ እስኪደርሱ ድርስ እየተከተልናቸዉ ነዉ።»
ባለፈዉ ሳምንት ሰኞ ርዕሠ-ከተማ ሰነዓ ዉስጥ አደባባይ የወጣዉን ሕዝብ ያስተባበሩት የሁቲ ባለስልጣናት ግን ጉዳይችን ከአብድ ረቦ ሐዲ፣ከመሐመድ ቢን ሰልማንም አይደለም ዓይነት ይላሉ።ከአሜሪካ እንጂ።በመቶ ሺሕ ለተገመተዉ ለሰልፈኛ ንግግር ያደረጉት የሁቲዎች የፀጥታ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሜጄር ጄኔራል ያሕያ አል መሕዲ የየመን ሕዝብ የዩናይትድ ስቴትስ አገልጋይ አይሆንም አሉ።
«እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ የየመን ሕዝብ ይሕን የመሰለ ሕዝባዊ መልዕክት አንግቦ ዛሬ በአደባባይ የተሰለፈዉ በዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ የተከፈተና የተባባሰዉን ጦርነት፣ የምጣኔ ሐብት ማዕቀብና የቀጠለዉን ወረራ ለማዉገዝ  ነዉ።ጆ ባይደን ስልጣን ሲይዙ የመን ዉስጥ የሚደረገዉን ጦርነት ለማስቆም የገቡትን ቃል የሚያክብሩ፣ የሰነዓን አዉሮፕላን መረፊያ የሚያስከፍቱ መስሎን ነበር።ያ ሁሉ ወሬ በሙሉ ዉሸት መሆኑ አሁን ተረጋግጧል።የአሜሪካ መርሕ አንድና በእስራኤል ደጋፊዎች ቁጥጥር ስር መሆኑ ታዉቋል።»
አጥኚዎች እንደሚሉት በየመኑ ጦርነት 16 ሐገራት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ይካፈላሉ።አብዛኛዉን የዉጪ ኃይል የምትመራና የምታስተባብረዉ አንዲት ሳዑዲ አረቢያ ብቻ ለጦር መሳሪያና ለቅጥረኛ ወታደሮች ብቻ በየቀኑ 200 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ትከሰክሳለች።
ሳዑዲ አረቢያ ከ2015 እስከ 2019 በነበሩት ሶስት ዓመታት ከመንፈቅ ብቻ ለጦርነቱና ለደጋፊዎችዋ 60 ቢሊዮን ዶላር አዉጥታለች።አብዛኛዉ ቦምብ፣ ጥይት፣ሚሳዬል የሚሸመተዉ፣ ስልጠና፣ መረጃ፣ፕሮፓጋንዳ የሚገኘዉ ከዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያን ከመሳሰሉ ተባባሪዎችዋ ነዉ።
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ባለፈዉ የካቲት የየመንን ጦርነት ለማስቆም በርግጥ ቃል ገብተዉ ነበር።እንዲያዉም ጦርነቱን የሰብአዊ ድቀትና የስልት ዉድቀት ብለዉትም ነበር።
                                            
«የመን ዉስጥ የሚደረገዉን ጦርነት ለማስቆምም ዲፕሎማሲያዊ ጥረታችንን እናጠናክራለን።ሰብአዊና ስልታዊ ድቀት ያስከተለዉን ጦርነት።ተኩስ አቁም እንዲደረግ፣የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦቶች እንዲከፈቱ እና ለዘላቂ ሰላም የሚደረግ ድርድር እንዲጀመር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚደርገዉን ጥረት መደገፋችንን እንዲያረጋግጥ የመካከለኛዉ ምስራቅ ቡድኔን ጠይቄያለሁ።»
የሁቲዉ ጄኔራል በቀደም ያሉት ሐሰት ሊሆን ይችላል።የባይደን ቃል በተሰማበት ወቅት ግን ከጦርነቱ ጠቀም ያለ ገንዘብ የሚዝቁት የአሜሪካ ኩባንዮችና ድርጅቶች ቃሉ ገቢር እንዲሆን መፍቅደቻቸዉን አንዳድ ተንታኞች ተጠራጥረዉ ነበር።ቃሉ ቢያንስ እስካሁን ገቢር አለመሆኑም ሐቅ ነዉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ከ2011 ወዲሕ አራተኛዉን ዲፕሎማት ሾሞ፣ ቀን፣አስከሬን-ቁስለኛ፣ተፈናቃይ ስደተኛ ከመቁጠር ባለፍ ጦርነቱን ለማስቆም እስካሁን  የተከረዉ የለም።

Jemen Marib Provinz | Angriff von Huthi-Rebellen
ምስል AFP

ሌላዉ ቀርቶ ተፋላሚ ኃይላት የጦር ወንጀል መፈፀም አለመፈፀማቸዉን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ኮሚሽን እንዲያጣራ፣ ለድርጅቱ የሰብአዊ ጉዳይ ምክር ቤት የቀረበዉ ረቂቅ ደንብ እንዳይፀድቅ የዩናይትድ ስቴትሷ-ሳዑዲ አረቢያ፣ በሳዑዲ አረቢያዋ ባሕሬን በኩል ዉድቅ አስደርጋዋለች።
ዓለም አቀፉ ድርጅት ዲፕሎማቶችን መሾም-መሻሩ እንዳልገደደዉ ሁሉ በጣም በሚታወቅበት «በጣም አሳስቦናል» በምትል ዓረፍተ ነገሩ የደመቀች ምክር ማስጠንቀቂያዉን ከመስጠትም አልቦዘነም።
ባለፈዉ ሳምንት ሮብ ተረኛዋ የድርጅቱ የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽነር (UNHCR) ቃል አቀባይ ሻቢያ ማንቶ ነበሩ።
«የመን ማሪብ አገረ-ግዛት የሚኖሩ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ተፈናቃዮችና ያጠቃላይ ሰላማዊ ሰዎች ጉዳይ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ መርጃ ድርጅትን በጣም አሳስቦታል።የዉጊያዉ አዉድ በርካታ ሕዝብ ወደሚኖርበት አካባቢ በመቃረቡ ሕወታቸዉ ለአደጋ ተጋልጧል።የሰብአዊ ርዳታ ማቀበልም ሲበዛ ከባድ ነዉ።»
ርዕሠ-መንበሩን ጄኔቭ ያደረገዉ የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሸነር የመን የሚኖሩ ተፈናቃዮች ሁኔታ እጅግ በጣም እንዳሳሰበዉ ባስታወቀበት ሳምንት፣ ሙስጠፋ መሐመድ እና ብጤዎቹ ፖላንድ ድንበር ላይ ብርድና ረሐብ ፈድፍዶ ሲገላቸዉ አልሰማ ይሆን?
ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር የመንን ከወረረ ከመጋቢት 2015 ወዲሕ አንድም በቀጥታ በሚደረገዉ ዉጊያ፣ በጦር ጄቶች ድብደባ፣ ሁለትም በምግብ እጥረት፣ በበሽታና ስደት ከ230 ሺሕ በላይ ሕዝብ አልቋል።ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል።ከ21 ሚሊዮን የሚበልጥ የመናዊ ርዳታ ፈላጊ ነዉ።ጦርነት እልቂት፣ፍጅት፣ስደት መፈናቃሉ  ዛሬም ቀጥሏል።የመን የተጀመረ የማያልቅባት፤ የሚያልቅ የማይጀመርባት ሐገር።

Jemen |  Bildung in Jemen
ምስል Sanaa Safia Mahdi/DW

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ