1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመን የጦረኞች ሐገር

ሰኞ፣ መጋቢት 20 2013

የሪያድ ገዢዎች በስድስት ሳምንት ዕድሜ ከየመን ጠራርገዉ ሊያስወጧቸዉ ፎክረዉባቸዉ የነበሩት የሁቲ አማፂያን አሁን ከተራ አማፂ ቡድንነት ወደ አስፈሪ ኃይልነት አድገዋል።የሁቲዎች ደጋፊ የምትባለዉ ኢራንም እንደነበረች አለች።ፕሬዝደንት ሐዲም ዛሬም እንደ 2015 ስደተኛ ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/3rLjf
Kronprinz Mohammed bin Salman und Kronprinz Mohammed bin Zayed
ምስል Eissa Al Hammadi /Ministry of Presidential Affairs/AP/picture alliance

የመን 6 ዓመት ያወደማት ጦርነት ይቆም ይሆን?

የሮማዉ ዕዉቅ የጦር መሪ ኤሊዉስ ጋሉዊስ ከ10 ሺሕ የሚበልጥ ጦሩን አስከትሎ ከግብፅ ወደ ያኔዋ አረቢያ ፌሌክስ የዘመተዉ የሳባዎችን አገዛዝ ደምስሶ ያቺን ስልጡን፣ስልታዊ፣ ለም ሐገር ለመቆጣጠር ነበር።ጦሩ ማሪብ ከተባለችዉ ከዚያች ሐገር የዚያ ዘመን ርዕሰ ከተማ ደርሶ ዉጊያ ገጠመ።አብዛኛዉ ረገፈ።የተረፈዉ ወደ መጣበት ፈረጠጠ።ከክርስቶስ ልደት በፊት በ25ኛዉ ዘመን ነበር። ሙስሊሞች በብልኃት፣ቱርኮች በማባበል፣ ብሪታንያዎች በገንዘብ፣ ሳዑዲ አረቢያዎች በድርድር የተወሰኑ አካባቢዎችን ተቆጣጥረዉባታል።በኃይል ለማስገበር የሞከሯት ግን፣ በዑስማን ቱርኩ የጦር አዛዥ በሐዲም ሱሌይማን ፓሻ አገላለፅ እንደ ጨዉ «ቀልጠዉባታል»።አሁንስ? የመን የሳዑዲዎችና የተከታዮቻቸዉ መቀበሪያ መሆንዋ ይሆን? ያጭር ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ፤ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ። 
የያኔዉ የ32 ዓመት ወጣት መሐመድ ቢን ሰልማን የሳዑዲ አረቢያን ምክትል አልጋወራሽነት ከመከላከያ ሚንስትርነቱ ስልጣን ጋር ደርበዉ በያዙ ማግስት የመንን ለመቆጣጠር ጦር ሲያዘምቱ እንዳያታቸዉ አዋጊ፣ ግዛት አስፋፊ፣ ዉጊያዉ አልሆን ሲል ተደራዳሪ መሆናቸዉን ያስመሰክራሉ ተብሎ ነበር።
ጊዜዉም ተገጣጥሞ ነበር።ንጉስ አብዱል አዚዝ ኢብን ሳዑድ የመንን የወረሩት መጋቢት ወር ነበር።1934 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማንም መጋቢት 26 የመንን ወረሩ።2015።
ኢብን ሳዑድ በሁለት ወር ዉጊያ ጣኢፍንና ሁዴይዳን የመሳሰሉ ትላልቅ ከተሞችን ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ ከዚያ በላይ በዉጊያዉ መቀጠሉ ዉጤቱ ዉርደት መሆኑን ስላወቁ ከየመን ገዢዎች ጋር ይደራደሩ ገቡ።ሁዴይዳን ለየመኖች መልሰዉ ጣኢፍን አስቀሩ።
የልጅ ልጃቸዉ ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን «ወሳኝ ማዕበል» ያሉትን ወረራ ሲያዉጁ የየመን ሁቲዎችን  በ6 ሳምንታት ዉስጥ ጠራርገዉ እንደሚያጠፉ ፎክረዉ ነበር።
በርግጥም የዓለምን ምርጥ የጦር መሳሪያ የታጠቀዉ የራስዋ የሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ የኩዌት፣ የቀጠር፣የባሕሬን፣ የዮርዳኖስ፣ የሞሮኮ፣ የግብፅ፣ የሱዳን ጦር፣ የአሜሪካ ቅጥረኛ ወታደሮች በቀጥታ የሚዋጉበት፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ በተዘዋዋሪ የተካፈሉበት፣አሜሪካና የብሪታንያ የስለላ የስልጠናና ያየር ላይ ነዳጅ ሙሌት ድጋፍ ያልተለየዉ ወረራ የልዑሉን ፉከራ ገቢር ማድረግ ይሳነዋል ብለዉ ያኔ የጠረጠሩ ከነበሩ የዚያችን ጉደኛ ሐገር የጉድ ታሪክ የሚያዉቁ ጥቂቶች ነበሩ።
የቢን ሰልማን «ወሳኝ ማዕበል» አቅጣጫዉን ለዉጦ የራስዋን የሳዑዲ አረቢያንና የተባባሪዎቻቸዉን  ምጣኔ ሐበት በሚያሽመደምድበት በ2019ኝ እንኳን ወጣቱ ልዑል የአያታቸዉን ስም እንጂ የድርድር መፍትሔ የመፈለግን ብልጠት ማወቅ አልቻሉም፤ ወይም አልፈለጉም ነበር።ጦርነቱን ለመቀጠል እዚያዉ ሳዑዲ አረቢያ በስደት ከሚኖሩት ከየመን ፕሬዝደንት አብድ ረቦ መንሱር ሐዲ ጋር አዲስ ስምምነት ተፈራረሙ።አሉም።
                            
«ወደ ሁለተኛ ሐገራችሁ ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንኳን ደሕና መጣችሁ።የደስታ ቀን ነዉ።የመኖች በተገናኙ ቁጥር ለሳዑዲ አረቢያ የደስታ ቀን ነዉ።ከሳዑዲ አረቢያ መስራች ከንጉስ አብዱል አዚዝ ዘመን ጀምሮ ሳዑዲ አረቢያ ሁል ጊዜ ከየመኖች ጎን እንደቆመች ነዉ።የየመን መረጋጋትና ብልፅግና አስፈላጊ ነዉ።ሕዝቡ የገጠመዉን ፈተና በብልሐት ይወጣዋል።» 
የመን ግን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳለዉ 230 ሺ ዜጎችዋን ለጦርነቱ ገብራ ነበር።4 ሚሊዮን ተፈናቅሎ፣ ከ22 ሚሊዮን የሚበልጠዉ በረሐብና በሽታ ይሰቃይባታል።ከሐገርነት ወደ ትቢያ ተለዉጣለችም።የሪያድ-አቡዳቢ ገዢዎች  የሚከሰክሱት ዶላርም የሁለቱን ሐገራት ምጣኔ ሐብት እያሽመደመደዉ ነዉ።የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን የጦርነቱን ዉጤት «ጥፋት» ይሉታል።
የሪያድ ገዢዎች በስድስት ሳምንት ዕድሜ ከየመን ጠራርገዉ ሊያስወጧቸዉ ፎክረዉባቸዉ የነበሩት የሁቲ አማፂያን አሁን ከተራ አማፂ ቡድንነት ወደ አስፈሪ ኃይልነት አድገዋል።የሁቲዎች ደጋፊ የምትባለዉ ኢራንም እንደነበረች አለች።ፕሬዝደንት ሐዲም ዛሬም እንደ 2015 ስደተኛ ናቸዉ።እንደገና ዩሱፍ ያሲን።
 ሮሞች የመንን ለመቆጣጠር በከፈቱት ጦርነት መሸነፋቸዉን ሲያዉቁ ወደመጡበት የተመለሱት በ60 ቀናት ዉስጥ ነበር።የኦቶማን ቱርኮች በጦርነቱ መሸነፋቸዉን የተቀበሉት በ3ኛዉ ዓመት ነበር።ሻምበል ስታፎርድ ቤትስወርዝ ሐይነስ የሚያዙት ብሪታንያ ቅኝ ገዢ ጦር በ1839 አደንን ለመያዝ በከፈተዉ ዉጊያ ብዙ ሺሕ የመኖችን ቢፈጅም፣ በጦርነቱ ሙሉ በሙሉ ድል ማድረግ እንደማይችል ተረድቶ ድርድር የጀመረዉ በወራት ዕድሜ ነበር።በድርድሩ ለአካባቢዉን ባላባቶች በዓመት 6ሺሕ ሪያል ለመክፈል ተስማምቶ ጦሩን አደላድሎ አሠፈረ።
በ1934 የመንን የወረሩት የሳዑዲ አረቢያ መስራች ንጉስ ቢን ሳዑድ የወረራዉ ዉጤት እንዳጀማመሩ እንደማይቀጥል ተረድተዉ ከጠላቶቻቸዉ ከየመኖች ጋር የተደራደሩት ዉጊያ በገጠሙ ሁለተኛ ወሩ ነበሩ።በ1962 የየመንን አብዮታዉያን የሚደግፍ ጦር ያዘመቱት የያኔዉ የግብፅ ፕሬዝደንት ገማል አብድናስር፣  ከጦርነቱ ሽንፈት እንጂ ድል እንደማይገኝ የተረዱት 3ኛ ዓመታቸዉ ነበር።
በናስር የመንፈስ ልጅ በጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ሲሲና በመሰሎቻቸዉ አይዞሕ ባይነት በየመኑ ጦርነት የተዘፈቁት ኢብን ሳዑድ የልጅ ልጅ ዘንድሮ በ6ኛ ዓመታቸዉም አዉዳሚዉን ጦርነት አላቆሙም።የዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉ ልዑል ፈይሰል ቢን ፈርሐን አል ሳዑድ ግን ባለፈዉ ሳምንት ተኩስ አቁም አሉ።
                   
«ይሕ (የተኩስ አቁም) ሐሳብ ተግባር ላይ እንዲዉል ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ፣ ከሸሪኮቻችን፣ ከየመን መንግስት ጋር ተባብረን እንሰራለን።ሁቲዎች ሐሳቡን እንዲቀበሉ፣ ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንደሚጡ ትጥቃቸዉን እንዲፈቱም አስፈላጊዉን ግፊት ሁሉ እንዳረጋለን።ምክንያቱም ዉጊያዉን አቆሞ መደራደር ብቸኛዉ አማራጭ ነዉ ብለን እናምናለንና።»
«ተኩስ አቁም፣ ድርድ ግን ትጥቅ ማስፈታት።» ብሎ አባባል ለሁቲዎች ግራ አጋቢ ነዉ የሆነዉ።የሁቲ ዋና ተደራዳሪ መሐመድ አብዱሰላም የሪያዶች ጥሪ ከዚሕ ቀደም ሁቲዎች «እጅ እንዲሰጡ» ከጠየቁበት አዋጅ የተለየ አይደለም በማለት ጥሪዉን ዉድቅ አድርገዉታል።ይሁንና ቡድናቸዉ ለዉይይት ምንጊዜም ዝግጁ መሆኑን አስታዉቀዋል።
የየመኑ ጦርነት እንዲቆም ከፍተኛ ግፊት የሚያደረገዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የጆ ባይደን መስተዳድር፣የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአዉሮጳ መንግስታትም የሪያዶችን ጥሪ ደግፈዉታል።
አጥኚዎች እንደሚገምቱት ለጦርነቱ አንዲት ሳዑዲ አረቢያ ብቻ ወደ4 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ  አዉጥታለች።ከ4 ሺሕ በላይ ዜጎችዋ ተገድለዋል።አራምኮ የተባለዉ ግዙፍ የነዳጅ ማምረቻና ማከማቻ ኩባንያዋ፣ የነዳጅ መርከቦቿ፣ አዉሮፕላን ማረፊያዎችዋ ሳይቀሩ በድሮን ሚሳዬል እና ቦምብ ጋይተዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ጨምሮ መሐመድ ቢን ሰልማንን ከበዉ «ሲያጫፍሩ» የነበሩት የስምንት ሐገራት ገዢዎችም ከጦርነቱ ቀስ በቀስ ራሳቸዉን አግልለዋል።አሜሪካኖችም በገፍ ይቸበችቡት  የነበረዉን ቦምብ-ሚሳዬል እንደሚያቅቡ አስጠንቅቀዋል። 
የሪያዶች ተኩስ አቁም ለሁቲዎች ግራ አጋቢ፣ ለተጠራጣሪዎች የይስሙሉ ቢመስልም የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት የሪያዱ አልጋወራሽ ከእንግዲሕ በጦርነቱ ለመቀጠል «መፈናፈኛ» የላቸዉም።
ጦርነቱ ቆመም ቀጠለ ያቺ ደሐ ግን ስልታዊ፣ ለምዕራባዉያን ኋላ ቀር ግን ጥንታዊ ሐገር በብዙ ሺሕ ዘመን ታሪኳ እንዳደረገችዉ ሁሉ የወራሪዎችዋ መቀበሪያ እንጂ መፈንጫ እንዳልሆነች አስመስካራለች።
ራሱን ለቻለዉ ዉይይት፣ መወያየት የሚሻ ይወያይበት።የመን ግን የዕልቂት ፍጅት፣ የጥፋት ዉድመት ግን የጦረኞች ጉደኛ ምድር ናት።

Jemen Huthi Sprecher Mohammed Abdelsalam
ምስል picture-alliance/dpa/Y. Arhab
Arabischer Frühling in Jemen - 10 Jahre seit der Revolution
ምስል Mohammed Al-Wafi/Xinhua/picture alliance
Arabischer Frühling in Jemen - 10 Jahre seit der Revolution
ምስል Mohammed Al-Wafi/Xinhua/picture alliance
Jemen Sanaa | Rauchwolke nach Luftangriff
ምስል Khaled Abdullah/REUTERS

ነጋሽ መሐመድ 

ሸዋዬ ለገሰ