1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመን ጦርነት ምድር

ሰኞ፣ ኅዳር 10 2011

አንዲት ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ከ2009 እስከ 2016 በነበረዉ በኦባማ መስተዳድር ዘመን ለአንዲት ሳዑዲ አረቢያ ብቻ የ115 ቢሊዮን ዶላር ጦር መሳሪያ ለመሸጥ ተስማምታለች።የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያ የዉጪ ጉዞ፤የንግድ ድልም የተመዘገበዉ የ110 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ጦር መሳሪያ ለሳዑዲ አረቢያ ገዢዎች ለመሸጥ ሲስማሙ ነበር።

https://p.dw.com/p/38XhJ
Jemen Krieg Zerstörung Militärcamp
ምስል picture alliance/AA/A. M. Yahya Haydar

የመን፣ የእልቂት አብነት

የ«ዓለም» የሚባሉት ሁለት አስከፊ ጦርነቶች በኋላ ያደረዉን የዓለም ሕዝብ የሠላም ጥማት ለማርካት የተመሠረተዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመቶ ዓመት ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ «ሰብአዊ ድቀት» ይለዋል።የድርጅቱ ዲፕሎማቶች ዛሬም ድርድር ይላሉ።የመኖች ግን መዓልት ወሌት ያልቃሉ።የመጀመሪያዉ እና «የዓለም» የሚባለዉ ጦርነት የቆመበትን መቶኛ ዓመት ለመዘከር ባለፈዉ ሳምንት ፓሪስ-ፈረንሳይ ተሰብስበዉ ለነበሩት ለኃያል ሐብታም መንግሥታት መሪዎች ግን የንግግር ማጣቀሻ ከመሆን ባለፍ እልቂቱን ማስቆም ከልብ የሚጣፍ ዓይደለም።የሪያድ፤የአቡዳቢ፤የካይሮ፣የካርቱም ገዢዎች በገፍ የሚሸምቱት የዩናይትድ ስቴትስ፤የብሪታንያ፤የፈረንሳይ እና የሌሎችም ሐገራት ቦምብ፤ሚሳዬል፤ መድፍ-አዳፍኔ የመንን በእቶን እያነፈረ ወደ ምድረ-ገሐብነት ለዉጧል።ከአረብ ምድር የሚዛቀዉ ሐብት፤አረብን የሚፈጅ፤ የዓረብ ሐገርን የሚያጠፋበት ጦርነት ከተጀመረ አራተኛ ዓመቱን ሊደፍን ወራት ቀሩት።እስካሁን አሸናፊ እና ተሸናፊ ግን አለየም። 

                                            

የሪያድ እና የአቡዳቢ  ነገስታት በሰወስት ወር ዕድሜ ሊያጠናቀቁ ፎክረዉ የተዘፈቁበት ጦርነት፣ የዚያን ቀን፣ ሁለት ዓመት ሊደፍን ሰወስት ወራት ነበር የቀሩት።ጥቅምት 8 2016 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎርያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሰነዓ።የአንድ ትልቅ ጎሳ መሪ መሞታቸዉ ተሰማ።የከተማይቱ ግዙፍ አዳራሽ በሐዘንተኛ ተጨናነነቀ።ያዩ እንዳሉት ለቀስተኛዉ በብዙ ሺሕ ይቆጠራል።የሐዘንተኛዉ ለቅሶ፤ ፀሎት ጩኸት፤ጫጫታ በአስፈሪ ስግምግምታ ተዋጠ።                              

አዉሮፕላን ናት።የተሸከመችዉን አምስት መቶ ፓዉንድ ቦምብ ትልቁ አዳራሽ አናት ላይ ዘረገፈችዉ።ቦምቡም አዉሮፕላኑንም አሜሪካ ሠራሾች ናቸዉ።«ካባቴ ጋር ነበርኩ።ደምፁን እንደሰማሁ ካካባቢዉ ለመብረር ፈልጌ ነበር።-----ሁለተኛ አዉሮፕላን መምጣቱ አይቀርም ነበር።ግን ከዚያ በኋላ የሆነዉን ያወቅሁት ሐኪም ቤት ከገባሁ በኃላ ነዉ።»

ይላል ያኔ የአስራ አራት ዓመት ታዳጊ የነበረዉ ወጣት ሁሴይን።የፈራዉ አልቀረም።ሁለተኛ ቦምብ ተደገመ።140 ሰዎች ተገደሉ።ሁሴን አንድ እግሩን አጣ።እንደ ሁሴይን አካላቸዉን ያጡትን ሰዎች ብዛት የቆጠረዉ የለም።የቦምብ ሚሳዬል ድብደባዉ ግን ሽማግሌ-ከሕፃን፤ ወጣት ካዛዉንት፤ ተማሪ ከወታደር ሳይለይ፤ ሰነዓ፤ ታኢዝ፤ ሰዓደ፤ ዛቢድ---- ላይ ሺዎችን ያረግፍ ያዘ።

እስካሁን የሟች ቁስለኞችን ትክክለኛ ቁጥር በዉል የሚያዉቅ የለም።ጦርነቱ የተጀመረበትን ሰወስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፈዉ መጋቢት ባወጣዉ ዘገባ እንዳስታወቀዉ ግን በጦርነቱ በቀጥታ የተገደለዉ ሠላማዊ ሰዉ ቁጥር ከአስር ሺሕ ይበልጣል።ከአርባ ሺሕ በላይ ሰዉ አካሉ ጎድሏል።

ዓለም አቀፉ የሕጻናት መርጃ ድርጅት Save the children እንዳስታወቀዉ ደግሞ በጦርነቱ እና ጦርነቱ ባስከተለዉ በሽታ እና ረሐብ በ2017 ብቻ የሞቱት ሕፃናት ቁጥር ከ50 ሺሕ ይበልጣል። ሰሞኑን ተረኛዋ ሁዴይዳሕ ናት።የጂዳዉ ወኪላችን ነብዩ ሲራክ  ባለፈዉ ሳምንት እንዳለዉ ሁዴዳሕን የሚያወድመዉ ጦርነት ከፍተኛ ዕልቂት ሳያስከል አልቀረም።

 

ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር ለወትሮዉ ከአራት መቶ ሺሕ በላይ ሕዝብ የሚኖርባትን ትልቅ፤ ዘመናይ ዉብ፣ የወደብ ከተማን ከአንሳር አላሕ ወይም ሁቲ ከሚባሉት አማፂያን እጅ ለመማረክ በ2015 መጠነ-ሠፊ ጥቃት ከፍቶ ነበር።አልቻለም።የሪያድ-አቡዳቢ ገዢዎች ለሰወስት ዓመት ከመንፈቅ ያክል አዳዲስ ጦር መሳሪያ ሲያከመቹ፤ወታደር ሲያሰለጥኑ፤ አካባቢዉን ሲያስጠኑ ከርመዉ ባለፈዉ መስከረም አዲስ ጥቃት ከፈቱ።

ሸማቂዎችን ከሰላማዊ ሰዉ፤ የጦር መሳሪያን  ከርዳታ ማከማቻ መጋዘን ያለየዉ ጥቃት በመቶ የሚቆጠር ሰላማዊ ሰዉ ገድሏል።በመቶ ሺሕ የሚቆጠር አሰድዷል።ሰሞኑን ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት UNHCR ቃል አቀባይ ሻቢያ ማንቱ እንደሚሉት ረሐብተኞች መመገቢያ፤ ተፈናቃዮች መሸሺያ አጥተዋል።

                                                

Jemen Demonstration gegen die Regierung in Sanaa alter Mann
ምስል dapd

«ከፍተኛዉ ዉጊያ፤ የአየር ድብደባ እና የከባድ መሳሪያ ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል፣ አቁስሏልም።እስካሁን ድረስ ሑዴይዳሕ ከተማ ዉስጥ ያሉትን ነዋሪዎች ቁጥር ማወቅ አይቻልም።ከተማይቱን ጥለዉ መሸሽ የሚፈልጉ ሰዎች መዉጪያ ማጣታቸዉ ግን በጣም ያሳስበናል።ወታደራዊዉ ዘመቻ አቃርጧቸዋል።መዉጪያ መንገዶችም ተዘግቶባቸዋል።»

የዓለም አቀፉ የሕፃናት መርጃ ድርጅት UNICEF ቃል አቀባይ ክርስቶፍ ቦልየራ እንደሚሉት ደግሞ ቁስለኞችም ሐኪም ቤት የሚደርሱበት መንገድ የለም።

                                 

«አንድ ሐኪም እንደነገርን (ዉጊያዉ እንደተጀመረ) በቀን ከ2000 እስከ 2500 የሚደርሱ በሽተኞች ወደ ሆስፒታል ይሔዱ ነበር።አሁን ስንት በሽተኞች እንደሚሔዱ በግልፅ አልነገረንም።ይሁንና (ዉጊያዉ በመባሱ) አል-ሳዉራ ወደተባለዉ ሆስፒታል አሁን የሚሔዱት በሽተኞች ቁጥር በጅጉ መቀነሱን ነግሮኛል።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደጋግሞ እንዳስታወቀዉ የየመን ሕዝብ እልቂት፤ረሐብ፤ በሽታ ስደት የመጀመሪያዉ «የዓለም» ከሚባለዉ ጦርነት ወዲሕ ታይቶ የማይታወቅ ዓይነት ነዉ።የዓለም መሪዎች ሚሊዮኖች ያለቁ፤ ብዙ ሚሊዮኖች የተሰደዱ፤ ቢሊዮነ-ቢሊዮናት ዶላር የሚገመት ሐብት ንብረት ያጠፋበት ጦርነት የቆመበትን መቶኛ ዓመት ባለፈዉ ሳምንት ፓሪስ ፈረንሳይ ዉስጥ ባደረጉት ጉባኤ ዘከሩ።ጉባኤተኞች ሥላለፈዉ ጦርነት ጥፋት እያነሱ ሲጥሉ የየመኑን እልቂት ከንግግር ማጣቀሻነት ባለፍ ሥለሚቆምበት ብልሐት ያሉት የለም።

በርግጥም የዋሽግተን-ለንደን፣ የፓሪስ-ሞስኮ መሪዎችን የሚያሳስበዉ ለሪያድ፤ ለአቡዳቢ፣ ወይም ለካይሮ ገዢዎች ከሚያስታቅፉት ጦር መሳሪያ የሚጋብሱት ገንዘብ እንጂ የየመን ሕዝብ እልቂት ወይም የኻሾጂ መገደል አይደለም።

አንዲት ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ከ2009 እስከ 2016 በነበረዉ በኦባማ መስተዳድር ዘመን ለአንዲት ሳዑዲ አረቢያ ብቻ የ115 ቢሊዮን ዶላር ጦር መሳሪያ ለመሸጥ ተስማምታለች።የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያ የዉጪ ጉዞ፤የንግድ ድልም የተመዘገበዉ የ110 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ጦር መሳሪያ ለሳዑዲ አረቢያ ገዢዎች ለመሸጥ ሲስማሙ ነበር።

የመንን ለሚደበድቡት ሐገራት ከፍተኛዉ ጦር መሳሪያ በመሸጥ ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥሎ ብሪታንያ፤ፈረንሳይ ፣ ጀርመን እና ሩሲያ ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ያለዉን ሥፍራ ይይዛሉ።

ከጀርመን በስተቀር ሁሉም የዓለምን  ሠላም ለማክበር ቆሟል የሚባለዉ  የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ አባላት ናቸዉ።ድምፅን በድምፅ የመሻር የድርጅቱን መርሕ የመዘወር ሥልጣን ያላቸዉ ናቸዉ።

የመንን የሚያጠፉት መንግስታት፣ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከብሪታንያ በሚደረግላቸዉ የስለላ፤የማማከር እና ወታደራዊ ስልጠና እየታገዙ በሚደርጉት ዉጊያ ሥለተቀዳጁት ድል ከመለፈፍ በስተቀር ጥፋቱን ለማስቆም አይደለም በጦራቸዉ ላይ ሥለሚደርሰዉም ጉዳት ለመናገር የሚጨነቁበት ምክንያት የለም።

Jemen Zerstörte Schule in der Stadt Taiz
ምስል DW/M. Alhaidary

በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት የአንሳር አላሕ ወይም የሁቲ አማፂን አፀፋም «ድል የኛ ነዉ« ዓይነት ነዉ።ከሰነዓ ወደ ሁዴድያሕ ለመዝመት የተዘጋጀ በርካታ ተዋጊን የሚመሩት ሸምሳን አቡ ናሽታን ትናንት እንዳስታወቁት ጦራቸዉ ከድል በመለስ የሚገታዉ የለም።

«የተከበሩት የየመን ጎሳ መሪዎች ተዋጊዎቻቸዉን፤የጦር መሳሪያ እና ገንዘባቸዉን  ወደ ጦር ግንባር እንደሚያዘምቱ አረጋግጠዋል።በፈጣሪ ፍቃድ  የየመንን ነገዶችን ድል ከማድረግ የሚያግዳቸዉ ነገር አይኖርም።»

በየመን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ማርቲን ግሪፍቲ እንደሚሉት ግን የተፋላሚ ኃይላት ዛቻ ፉከራ፤የኃያላኑ መንግሥታት ወገንተኝነትም ሆነ ዝምታ ተፋላሚዎችን ለመሸምገል የሚያደርጉትን ጥረት አላገደም።ልዩ መልዕክተኛዉ  ባለፈዉ አርብ እንዳስታወቁት ተፋላሚዎች የምክክር በተባለ ድርድር ላይ ለመካፈል ፈቃደኞች ናቸዉ።

  «ይሕ ለየመን ወሳኝ ጊዜ ነዉ።ከየመን ተፋላሚ ኃይላት መሪዎች ማለትም ከየመን መንግሥት እና ከአንሳር አላሕ፣ በዚሕ ምክክር ላይ ለመገኘት ፈቃደኛ መሆናቸዉን ማረጋገጪያ አግኝቻለሁ።»

ስዊድን ይደረጋል በተባለዉ ምክክር ሁለቱም ወገኖች እንደሚገኙ በየፊናቸዉ አረጋግጠዋል።ይሁንና ዋነኞቹ የጦርነቱ አዋጊዎች የሪያድ ገዢዎች እና ተባባሪዎቻቸዉ ስለድርድሩ ያላቸዉን አቋም በግልፅ አላስታወቁም።ጦራቸዉ ሑዴይዳሕ ከተማን መደብደቡን እንደሚያቆም ካስታወቁ ከጥቂት ቀናት በኋላም ድብደባዉ ቀጥሏል።ድርድር በተባለ ማግስት-ጦርነት፤ ጦርነት በፋማ ማግስት ድርድር ሲባል እነሆ አራት ዓመት ሊደፍኑ ወራት ቀራቸዉ።

Yemen - al-Hudaida
ምስል picture-alliance/AP Photo/N. El-Mofty

የፖለቲካ ተንታኝ መሐመድ ሸምሳን እንደሚሉት አሁንም ከጦር ግንባሩ ፍልሚያ ዉጪ ከድርድሩ የተለየ ነገር አይጠበቅም።

«የየመን ተፋላሚ ኃይላት ዉጊያ አቁመዉ እንዲደራደሩ ሁሉም ወገን ሲጠይቅ ነበር።ይሁንና ወታደራዊዉ ግጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ ነዉ።የዚሕ ምክንያቱ ተፋላሚ ኃይላት ወደፊት ይደረጋል ብለዉ በሚያስቡት ድርድር ወታደራዊ የበላይነት ይዘዉ ለመደራደር ሥለሚፈልጉ ነዉ።ይሕ ማለት የፖለቲካ አጀንዳ እና የበላይነት ለማግኘት ወሳኙ ወታደራዊ ዘመቻዉ መሆኑን አመልካች ነዉ።»

«አል ሐቅ ፎቀል ቅዋ» ይላል አሉ-አረብ።ፍትሕ በጉልበት ላይ ነዉ-እንደማለት።ግን እስከ መቼ?  

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ