1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየመን ተፋላሚዎች ድርድር

ረቡዕ፣ ኅዳር 26 2011

የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚያምኑት ያለፈዉ፣ ያሁኑንም ሆነ ምናልባት የወደፊቱን ድርድር የሚወስኑት ከሰነዓ ይልቅ የቴሕራን፤ መሪዎች፣ ከአብድረቦ መንሱር ይበልጥ መሐመድ ቢን ሠልማን ናቸዉ።የሪያድ እና የቴሕራን ገዢዎች ለዲፕሎማሲዉ ወግ ያሕል «ድርድሩ»ን ተገቢ ማለታቸዉ አልቀረም።ለድርድሩ ስኬት እስካሁን ያሉ ያደረጉት ግፊት ግን የለም።

https://p.dw.com/p/39XcV
Jemen Konflikt - Verletzte Huthi-Rebellen in Sanaa
ምስል Getty Images/AFP/M. Huwais

Jemen Verhandlung - MP3-Stereo

የየመን ተፋላሚ ኃይላት ተወካዮች ዛሬ ማምሻቸዉን ወይም ነገ አዲስ ዙር ድርድር ይጀምራሉ ተብለዉ እየተጠበቁ ነዉ።በሳዑዲ አረቢያ የሚደገፈዉ የየመን ስደተኛ መንግሥት ተወካዮች እና በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት የአንሳር አላሕ ወይም ሁቲ አማፂ ቡድን ተጠሪዎች ስቶክሆልም-ስዊድን ገብተዋል።የሁለቱ ወገኖች ተወካዮች ስቶክሆልም ከመግባታቸዉ በፊት በየፊናቸዉ በሰጡት መግለጫ በድርድሩ ሁነኛ ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸዉን አስታዉቀዋል።የፖለቲካ ታዛቢዎች ግን ድርድሩ የተለየ ዉጤት ማምጣቱን ይጠራጠራሉ።

የርዕሠ-ከተማ ሰነዓ ነዋሪዎች ድርድሩ ለአግባቢ ዉጤት እንዲበቃ በፆም-ፀሎት እየተማፀኑ ነዉ።ወጣት መሐመድ አል ቦካሪ አንዱ ነዉ።«ባሁኑ ወቅት ከስዊድን ሠላም ይመጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።እንደ ሌላዉ ዓለም በሰላም እና በፀጥታ መኖር እንድንችል እንፀልያለን።የመን ዉስጥ ሠላም እና ፀጥታ ዳግም ይሰፍናል የሚል ተስፋ አለን።በሰዎች ላይ የሚደርሰዉ ጥፋት በጣም አሳዛኝ ነዉ።የምጣኔ ሐብት ድቀቱም ከፍተኛ ነዉ።ጦርነቱ አብቅቶ እንደ ተቀረዉ ዓለም እንኖራለን የሚል ተስፋ አለን።»

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሹማምንትም እደተራዉ የመናዊ ሁሉ ከተስፋ-ተማፅኖ ባለፍ ተፋላሚዎች ሠላም እንዲያወርዱ ጫና የሚያሳርፉበት «ክርን» ያላቸዉ አይመስልም።የዓለም ምግብ ድርጅት የበላይ ኃላፊ ዴቪድ ቤስሌይ «እንዲያዉ ለየመን ሕፃናት እንኳ ሲባል----» ይላሉ።

«ከሁሉም ወገኖች የተገነዘብኩት መሰላቸት ነዉ።አዕምሯቸዉም፣መንፈሳቸዉም፣ አካላቸዉም ሁሉንም ጦርነቱ ሰልችቷቸዋል።ደክመዋል።ያነጋገርኳቸዉ በሙሉ መፍትሔ ናፍቋቸዋል።ይሕ ነገ ወይ ከነገ ወዲያ የሚጀመረዉ የሠላም ድርድር ለሐገሪቱ ሕፃናት የሠላም ተስፋ ወደ ሚፈነጥቅበት መንገድ ያመራል ብለን ተስፋ እናድርግ።»

Jemen 2016 Kind von Binnenflüchtlingen bei Sanaa
ምስል picture-alliance/AP Photo/H. Mohammed

ጦርነቱ ያደረሰዉ ጥፋት በርግጥም ተነግሮ የሚያልቅ ዓይነት ዓይደለም።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA-በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) እንዳስታወቀዉ የመን ርዳታ በመፈለግ ሰባት አመታት በጦርነት የምትወድመዉ ሶሪያን በልጣለች።24 ሚሊዮን የመናዊ ወይም ካጠቃላይ የሐገሪቱ ሕዝብ ከ75 ከመቶ የሚበልጠዉ የጤና ችግር እና ችጋር እየጠበሰዉ ነዉ።

የተፋላሚ ኃይላትን የሚያደራድሩት በየመን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ማርቲን ግሪፍቲስ ተደራዳሪዎች እልቂት ፍጅቱን ለማስቆም ከሚያስችል ስምምነት እንዲደርሱ «የሚችሉትን ሁሉ» ለማድረግ ቃል ገብተዋል።የሚችሉት እስከምን ድረስ  እንደሁ ግን አይታወቅም።ግሪፍቲስ ባለፈዉ መስከረም የተፋላሚ ኃይላት ተወካዮችን ዤኔቭ ላይ ለማደራደር ሲያግባቡም እንዲሕ እንዳሁኑ ተስፋ አድርገዉ፣ ተስፋ ሰጥተዉ ነበር።ድርድሩ ግን፣ የአንሳር አላሕ ተወካዮች ወደ ዤኔቭ መጓዝ ባለመቻላቸዉ ሳይጀመር አበቃ።

ባሁኑ ድርድር ግን የአንሳር አላሕ ተወካዮች ቀድመዉ ስቶክሆልም ገብተዋል።ከተደራዳሪዎቹ እንዱ ያሉት ደግሞ ተስፋዉ፣ ፍዝም መኖሩን ጠቋሚ ነዉ።

«መሰረታዊ ሥምምነት ላይ ደርሰናል።ድርድሩን ለመጀመር የምናቀርበዉ ቅድመ ግዴታ የለም።መተማመንን ለማስፈን አንዳድ እርምጃዎችን እንወስዳለን።ለምሳሌ የተማረኩ ቁስለኞች ሙስካት ሔደዉ እንዲታከሙ ዉል ተፈራርመናል።የሰነዓ አዉሮፕላን ማረፊያን ለመክፈትም እየሠራን ነዉ።»

Jemen Konflikt - Zerstörungen in der Hauptstadt Sanaa
ምስል Getty Images/AFP/M. Huwais

ይበሉ እንጂ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚያምኑት ያለፈዉ፣ ያሁኑንም ሆነ ምናልባት የወደፊቱን ድርድር የሚወስኑት ከሰነዓ ይልቅ የቴሕራን፤ መሪዎች፣ ከአብድረቦ መንሱር ይበልጥ መሐመድ ቢን ሠልማን ናቸዉ።የሪያድ እና የቴሕራን ገዢዎች ለዲፕሎማሲዉ ወግ ያሕል «ድርድሩ»ን ተገቢ ማለታቸዉ አልቀረም።ለድርድሩ ስኬት እስካሁን ያሉ ያደረጉት ግፊት ግን የለም።

ነጋሽ መሐመድ 

ሸዋዬ ለገሰ