1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመቐለ ነዋሪዎች ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ምን ይጠብቃሉ?

ቅዳሜ፣ መጋቢት 16 2015

ከግዚያዊ አስተዳደሩ ምን ትጠብቃላችሁ በሚል ያነጋገርናቸው የመቐለ ዩኒቨርሰቲ የአስተዳደር ትምህርት ክፍል አስተማሪው ዶክተር ተክላይ ተስፋይ፥ በትግራይ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በመነሳት ቅድሚያ መፈፀም ያለበት፣ በትግራይ ያሉ የውጭ ሃይሎች ማስወጣት እና የተፈናቀለው በሚልዮኖች የሚቆጠር ህዝብ መመለስ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4PF0o
Äthiopien Tigray-Provinz Mekele
ምስል EDUARDO SOTERAS/AFP

የመቀሌ ነዋሪዎች ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ምን ይጠብቃሉ?

በትግራይ ከተቋቋመው የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር ምን ይጠብቃሉ ስንል ምሁራን እና የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች አስተያየታቸው ጠይቀናል።
በፕሪቶሪያው ውል መሰረት በትግራይ የተቋቋመው ግዚያዊ አስተዳደር አጣዳፊ የተባሉ የተለያዩ ስራዎች ሊከውን በህዝቡ ዘንድ እንደሚጠበቅ አስተያየት ሰጪዎች ይገልፃሉ። በዋነኝነት በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሓት እንዲሁም በተለያዩ የፖለቲካ ሀይሎች እና ሲቪል ተቋማት ተሳትፎ የተቋቋመው ይህ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በቅርቡ ካቤኔው ይፋ ያደርጋል ተብሏል። ከግዚያዊ አስተዳደሩ ምን ትጠብቃላችሁ በሚል ያነጋገርናቸው የመቐለ ዩኒቨርሰቲ የማኔጅመንት ትምህርት ክፍለ አስተማሪው ዶክተር ተክላይ ተስፋይ፥ በትግራይ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በመነሳት ቅድሚያ መፈፀም ያለበት፣ በትግራይ ያሉ የውጭ ሃይሎች ማስወጣት እና የተፈናቀለው በሚልዮኖች የሚቆጠር ህዝብ መመለስ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ትግራይ የሁለት ዓመት ጦርነት እንዳለፈች ክልል በርካታ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንደተንሰራፉባት የሚናገሩት ዶክተር ተክላይ ተስፋይ ከ21 ወራት በላይ ደሞዝ ያልተከፈሉ የመንግሰት ሰራተኞች ውዝፍ ክፍያቸው የሚያገኙበት ሁኔታ ማመቻቸት፣ የትግራይ የበጀት ድጎማ ከፌዴራሉ መንግስት ማስለቀቅ፣ የታሰሩ የትግራይ ተወላጅ ፖለቲከኞች፣ ሲቪልና ወታደሮች እንዲፈቱ ጥረት እንዲያደርግ፣ የተቀዛቀዘው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ ማድረግ፣ የወደመ መሰረት ልማት መገንባት እና ሌሎች ስራዎች ከትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እንደሚጠበቅ ምሁሩ ይናገራሉ።
ሌሎች በመቐለ ከተማ ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች እንዲሁ በአቶ ጌታቸው ረዳ ከሚመራ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በርካታ አወንታዊ ለውጦች እንደሚጠብቁ ገልፀውልናል።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ
ፀሀይ ጫኔ