1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕገመንግሥት ጉዳይ ጥናት ያስከተለው ውዝግብ

ረቡዕ፣ ግንቦት 16 2015

የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ሕገመንግሥቱን አስመልክቶ ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገውን ጥናት 16 የፖለቲካ ድርጅቶችን የተካተቱበት የተቃዋሚ ፖለቲካ ስብስብ አጣጥሎ ነቅፎታል ። ሕገመንግሥቱ አይነካብን የሚሉ እንዳሉ ሁሉ እንደውም ሙሉ በሙሉ ተቀዶ መጣል አለበት የሚሉም አሉ ። ከሁለቱም በተለየ መሻሻል አለበት የሚሉም ይታያሉ ።

https://p.dw.com/p/4RlaM
Äthiopien Parlament Addis Abeba
ምስል Solomon Muche/DW

ኢትዮጵያ፦ ሕገመንግሥቱ ብዙዎችን እንዳወዛገበ ነው

ኢትዮጵያ ሕገመንግሥቱ ብዙዎችን እንዳወዛገበ ነው ። ሕገመንግስቱ አይነካብን ከሚሉት አንስቶ እንደውም ሙሉ በሙሉ ተቀዶ መጣል አለበት እስከሚሉት ድረስ እንዳጨቃጨቀ ነው ። ከሁለቱም በተለየ መሻሻል አለበት የሚሉም አሉ ። የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ሕገመንግስቱን አስመልክቶ ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው ጥናትም ይህንኑ ያንጸባርቃል ። ጥናቱን ግን 16 የፖለቲካ ድርጅቶችን ያሰባሰበው የተቃዋሚ ፖለቲካ ስብስብ አጣጥሎ ነቅፎታል ። የፓርቲዎቹ ስብስብ እንዳለው ህገመንግስት ሁሉን አካታች በሆነ ሰፊ ውይይት የሚሻሻል እንጂ ውስን ሰዎችን ባነጋገረ ጥናት ሊወሰን አይገባምም ብሏል ።

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ተቋም ሕገመንግሥትን አስመልክቶ ለሁለት ዓመታት ከትግራይ ክልል ውጭ በሁሉም የአገሪቱ አከባቢዎች ያካሄደውን የጥናት ግኝት ውጤት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በዚህም “ህገመንግስት መነካት የለበትም፣ በሙሉ ተቀዶ መጣል አለበት እና መሻሻል አለበት” የሚሉ ሶስት የተለያዩ ሀሳቦች በጥናቱ ላይ አስተያየት በሰጡት ተንፀባርቋል ያለው የጥናቱ ግኝት፤ በዚህ መነሻነትም ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ከመግቢያው አንስቶ አንቀጽ 8 እንዲሁም አንቀጽ 39 ላይ በማተማኮር ባጠናው ጥናት፤ ኅብረተሰቡ አንድ ላይ ከመኖር የተለየ ሃሳብ እንደሌለው መረዳቱን አመለከቶ ነበር።

የዚህ ጥናት ባሁን ወቅት ህገመንግስት ማሻሻያ ሀሳብ ላይ አጠንጥኖ መካሄድ በይሁኝታ አልመለከተውም ያለው 16 የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ያካተተው የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ኮከስ ግን ጥናቱን አጣጥሎ ነቅፎታል፡፡ እንደ ኮከሱ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢኒስቲትዩት ህገመንግስት ላይ ያስጠናው ጥናት፤ “የተወሰኑ አካላት ፍላጎት የተንጸባረቀበት እና አሳሳች” ብሎታል፡፡ 
የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶቹ ኮከስ አስደንቃጭ ነው ያለውን የጥናቱን ውጤት ያለ ሰፊ የህዝብ ውይይት ለመተግበር መመኮር አደገኛ ነው ሲልም አስጠንቅቋል፡፡

ብዙዎችን የሚያጨቃጭቀው ህገ መንግስት በኢትዮጵያ
ብዙዎችን የሚያጨቃጭቀው ህገ መንግስት በኢትዮጵያምስል Solomon Muche/DW

የኮከሱ አባል ከሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ተጠቃሽ ነው፡፡ የፓርቲው ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ በዚሁ ላይ በሰጡን አስተያየትም፤ “ጥናቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ብዙ የተደከመበት የብሔር ብሔረሰቦች ህልውና የሚፈታተን ይመስላል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ 

“ጥናቱ የብሔር ብሔረሰቦች ተሳትፎ እና ድምፅ ለማፈን ብዙ ርቀት ሄዶ የተደከመበት ይመስላል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች አገር በተባለች ኢትዮጵያ ጥናቱ የብሔር ብሔረሰቦች ህልውና የሚያደበዝዝ ይመስላል፡፡ ለዚህ ጥያቄ ከ150 ዓመታት በላይ ትግል ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ይህ ጥናት ያሳሰበን፤ ያስደነገጠንም ለዚሁ ነው” ብለዋል፡፡

አቶ ጥሩነህ አክለውም “ህገመንግስት መሻሻል አለበት እንኳ ቢባል ሰፊ ማህበረሰብ እና የማህበረሰብ ተወካዮች ተወያይተውና ተፋጭተውበት የሚያግባባ ሃሳብ ላይ ተደርሶ እንጂ ለፖለቲካ ጥቅም ባገደለ ፍላጎት መሆን አያሻውም” ሲሉም አስቴየታቸውን አክለዋል፡፡

ሌላው የኮከሱ አባል የሆነውን የአፋር ህዝብ ፓርቲን በሊቀመንበርነት የሚመሩት አቶ ሙሳ አደም ህገመንግስቱን በተመለከተ በኮከሱ አባላት ውስጥ እንኳ ተመሳሳይ አቋም አለመኖሩን ገልጸው፤ የጥናቱ ውጤት አሳሳቢነትን ግን በአስተያየታቸው አኑረዋል፡፡ “አንድ ሺህ ሰዎችን ያውም ጥናቱም እንዳመለከተው በከተሞች ላይ ብቻ በማጠንጠን ውስን ሰው አነጋግረህ የ120 ሚሊየን ህዝብ እጣ ፈንታ መወሰን የማይቻል ነው፡፡ ህገመንግስት ለማሻሻል ማሰብ በራሱ ግን ችግር ነው ብለን አናምንም፡፡ ጥናቱ ግን ከዚህ በፊትም በአገራዊ ምክክር አጃንዳነት ይቅረብ ተብሎ በተጠየቀበት በበርካታ ባለድርሻ አካላት መወያየት ሲገባ አሁን የተረጋገጠ ሰላም እንኳ በሌለበት አጀንዳውን ነጥሎ ማምጣቱ ተገቢነቱ አልታየንም፡፡”

ባለፈው ሳምንት ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የጥናቱ አስተባባሪ ዶ/ር ጥላሁን ተፈራ ጥናቱ የተደረገበት ዋና አላማው መንግሥት ተነስቶ ሕገ መንግሥቱን እቀይራለሁ በሚል ሌላ ርምጃ ውስጥ እንዲገባ ሳይሆን ሕገ መንግሥቱን በሚመለከት በቀጣይ ለሚደረግ ሀገራዊ ውይይትም ሆነ ክርክር ግብአት እንዲሆን ታስቦ መሆኑን በአጽንኦት ማንሳታቸው ይታወሳል።

ሥዩም ጌቱ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ