1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሔልሙት ኮል ሥንብት

እሑድ፣ ሰኔ 25 2009

በርካታ የዓለም መሪዎች በተገኙበት ቅዳሜ ሰኔ 24 ቀን፣ 2009 ዓ.ም. በአውሮጳ ምክር ቤት ለሔልሙት ኮል የስንብት ሥነ-ስርአት ተከናወነ። በስንብት መርሐ-ግብሩ የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል «ድልድይ ገንቢ» ሲሉ ሔልሙት ኮልን አሞካሽተዋል።

https://p.dw.com/p/2fl3w
Speyer Dom Trauerfeierlichkeiten für Altkanzler Kohl
ምስል Reuters/A. Dedert

የቀድሞው የጀርመን መራሔ- መንግሥት ሔልሙት ኮል ርዓተ-ቀብር እና ስንብት አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኙ እና የቀድሞ የዓለም መሪዎች  በተገኙበት በፈረንሳይ ሽትራስቡርግ ከተማ  ተከናወነ። የጀርመኗ መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል በፈረንሳይ የሽትራስቡርግ ከተማ በሚገኘው የአውሮጳ ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፦ ሔልሙት ኮል ባይኖሩ ኖሮ ሕይወቴ የተለየ በሆነ ነበር ሲሉ ተደምጠዋል። መራኂተ-መንግስቷ ጀርመንን ለ16 ዓመታት የመሩትን ሔልሙት ኮል «ድልድይ ገንቢ» ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል። በ87 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ኮል በአውሮጳ ፓርላማ ኦፊሴላዊ ሥንብት የተደረገላቸው የመጀመሪያው ሰው ናቸው።

የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዣን ክላውድ ጁንከር መርሐ-ግብሩ «የጀርመን እና የአውሮጳ ጀግና» ሲሉ ባሞካሿቸው ሔልሙት ኮል ምርጫ መካሔዱን ተናግረዋል። ከጎርጎሮሳዊው 1982-1998 ዓ.ም. በዘለቀው የመራሔ-መንግሥትነት ሥልጣናቸው ኮል የጀርመንን ውኅደትን በበላይነት አሳክተዋል። የአውሮጳ ኅብረት የዩሮ የመገበያያ ገንዘብን በጋራ እንዲጠቀሙ ማድረግም ችለዋል።

በሥንብት መርሐ-ግብሩ የተሳተፉት የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን «ሔልሙት ኮል ከግል ፍላጎታችን በላቀ ዓላማ እንድንሳተፍ እድል ሰጥተውናል» ሲሉ አመስግነዋቸዋል። ክሊንተን በቁልፍ ታሪካዊ ወቅቶች ከአገራት ብሔራዊ ጥቅም ይልቅ ዓለም አቀፍ ትብብርን በማስቀደም ያሳዩትን ፈቃደኝነት በምሳሌነት ጠቅሰዋል። በመርሐ-ግብሩ ላይ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኤማኑዌል ማክሮ እና የሩሲያው ጠቅላይ ሚንሥትር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭም ነበሩ።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ