1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሥራ እንቅስቃሴ

ረቡዕ፣ መጋቢት 9 2012

የኢትዮጵያ መንግስት ግዙፍ መዕዋለ ንዋይ በመመደብ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ አከናውኗል። ከሶስት ዓመታት በፊት ተገንብተው ወደ ምርት ተግባር ከተሸጋገሩት መካከል የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በቀዳሚነት ይጠቀሳል ። የዛሬው ከኢኮኖሚው አለም ዝግጅታችንም በዚሁ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የስራ እንቅስቃሴ ላይ ያተኩራል።

https://p.dw.com/p/3Zd2u
Äthiopien Awassa
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሥራ እንቅስቃሴ

ወጣት ወይኒቱ ቦካንሳ ነዋሪነቷ በሲዳማ ዞን ዳራ ወረዳ ነው። ወይኒቱ እንደ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ የገጠር ሴቶች የስራ ጫና ሳይበግራት በትምህርቷ የተወሰነ ደረጃ ለመግፋት ጥረት ማድረጓን ትናገራለች ። ይሁን እንጂ በአስረኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ወደ መሰናዶ ትምህርት ለማለፍ የሚበቃትን ውጤት ለማግኘት እንዳልቻለች የምታስታውሰው ወይኒቱ በዚህም የተነሳ ለዓመታት በቤት ከመዋል ውጪ አማራጭ አልነበረኝም ትላለች ። በኃላ ላይ ግን በሀዋሳ ከተማ የተከፈተው የአንዱስትሪ ፓርክ ለሰራተኝነት ከመለመላቸው ሴቶች መካከል አንዷ ሆና መቀላቀሏን የምትናገረው ወይኒቱ ይህ አጋጣሚ ቤተሰቤን እንድረዳ ፣ ትምህርቴንም እንድቀጥል ምክንያት ሆኖኛል ትላለች ።

በአገሪቱ በቀዳሚነት ከተገነቡት ፓርኮች አንዱ የሆነው የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የምርት አገልግሎቱን የጀመረው ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ነበር። ፓርኩ በእነኝሁ ዓመታት በዜጎች የስራ እድል ፈጠራና በምርት አቅርቦት ረገደ አከናውኗል ያሏቸውን ስራዎች  የፓርኩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም ከተማ ይገልጻል ።

በአሁኑ ወቅት በሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የማምረቻ ቬድ ወስደው በስራ ላይ የሚገኙት ኩባንያዎች በአብዛኛው በጨርቃ ጨርቅ ምርቶች ላይ የተሰማሩ ናቸው። ከእነኝሁ ኩባንያዎች መካከል የካንቤቢ ዳይፐር አምራቹ ኦን ቴክስ ኩባንያ፣ የአሜሪካው ፒቪ ኤች እና የህንዱ ሬይ መንድ ይገኙባቸዋል። ኩባንያዎቹ የግማሽ ምዕተ ዓመት ልምድ ያላቸው ሲሆን በተለይ በአለምአቀፉ የጨርቃጨርቅ ንግድ ዘርፍ የገነነ ስም እንዳላቸው ይነገርላቸዋል። ኩባንያዎቹ በአሁኑወቅት በሙሉና በከፊል የተጠናቀቁ የአልባሳት ምርቶቻቸውን ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረቡ እንደሚገኙ ነው የፓርኩ ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ፍጹም ከተማ የሚናገሩት።

Äthiopien Awassa
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት ያሬድ ሚለታ ከዓመታት በፊት ዛሬ የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በተገነባበት  ቦታ ላይ የነበረውን የእርሻ መሬት በማረስ ይተዳደር እንደነበር ይናገራል። ፓርኩ ሲመሰረት ታዲያ ከመንግስት ከተሰጠው የካሳ ክፍያ በተጨማሪ በፓርኩ ውስጥ በቋሚነት ተቀጥሮ እየሰራ እንደሚገኝ የሚናገረው ወጣት ያሬድ  በተለይም የፓርኩ የስራ ሃላፊዎች በስራው እንዲተጋ ዘውትር እንደሚያበረታቱት ይገልጻል።

የሀዋሳው ኢንዱስትሪያል ፓርክ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም ከተማ ፓርኩ ባለፉት ሶስት ዓመታት የአካባቢውን ማህበረሰብ የስራ ባህል በመቀየር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዎ ማበርከቱን ይናገራሉ ። በፓርኩ የመጀመሪያ ዓመታት  በቀን ስምንት ሰዓት እንኳን ለመስራት ይቸገሩ ነበር የሚሉት አቶ ፍጹም በሂደት ግን ተጨማሪ ሰዓታትን  በመስራት ተጨማሪ ገቢ ማግኘትን እየለመዱ ይገኛሉ ይላሉ ። በዚህም በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ፓርኩ ከተቀላቀሉ ወዲህ ሰዓትን መቁጠር ብቻ ሳይሆን አንዴት ወደ ገንዘብ መቀየር እንደሚቻልም አንዲረዱ አድርጓቸዋል ይላሉ ።

Äthiopien Fisum Tefera
የፓርኩ ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ፍጹም ከተማምስል DW/S. Wegayehu

የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም ከተማ እንደሚሉት ፓርኩ ባለፉት ሶስት ዓመታት የተጓዘበት መንገድ አልጋ በአልጋ አልነበረም ። በተለይም የምርት ግብዓት እጥረትና የሰራተኞች የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ፓርኩ ካጋጠሙት ፈተናዎች መካከል ዋንኞቹ መሆናቸውን ስራ አስኪያጁ ዘርዝረዋል። በፓርኩ የሚያገለግሉ ሰራተኞች ከደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖችና ከአጎራባች የኦሮሚያ አካባቢዎች የመጡ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ፍጹም ይህም በአሁኑወቅት በሀዋሳ ከተማ በመኖሪያ ቤት ዙሪያ ባለው የፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣም  አገልግሎቱን በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ እንዳይቻል አድርጎታል ብለዋል።

ፓርኩ በቀጣይ ከሰራተኞች መኖሪያ ቤት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት አምራች ኩባንያዎችንና የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ አማራጮችን በመንደፍ ወደ ተግባር መግባቱን ነው ዋና ስራ አስኪያጁ የጠቆሙት ።  

Äthiopien Industriegebiet in Hawassa
ምስል Imago/Xinhua Afrika

በሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በመግባት የምርት ስራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኙት ኩባንያዎች  የአገሪቱን የወጪ ንግድ እድገት በማገዝና የቴክኖሎጂ ሽግግር በመፍጠር ረገድ የየራሳቸውን አስተዋጹዎ እያበረከቱ ይገኛሉ። ይሁንእንጂ አብዛኞቹ ኩባንያዎች የአበርክቷቸውን ያህል ለመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ብዙም ቅርብ አይደሉም  ወይም ከእነካቴው በራቸው ዝግ ነው ማለት ይቻላል። ዶቼ ቨሌን ( DW ) ጨምሮ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት በምርት ስኬቶቻቸውና ባጋጠሟቸው ተግዳሮቶች ዙሪያ ዘገባዎችን ለመስራት የሚቀርቡላቸውን ጥያቄዎች ተቀብለው ለማስተናገድ ሲቸገሩ ይስተዋላሉ።

ያም ሆኖ ግን ዘርፈ ብዙ ገጽታዎች የሚስተዋሉበት የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ከምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታው በመለስ መሻሻል የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች መኖራቸው የሚታወቅ ነው።

በተለይም ከሰራተኞች የጉልበት ክፍያ አለመመጣጠን ፣ ከመደራጀት ነጻነት ጋር በተያያዘ ከአለም አቀፍ ህጎች ጋር ተጻራሪ የሆኑ የመብት ጥሰቶች ይፈጸማሉ ሲሉ  ተቆርቋሪ የሲቪክ ድርጅቶች በየጊዜው በሚያወጧቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ። 

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

እሸቴ በቀለ