1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት ዘመቻ 

ዓርብ፣ ሚያዝያ 7 2014

« በ2009 ዓ ም ደግሞ ኢትዮጵያ “ከልጅነት ልምሻ ነፃ”ተብላ የምስክር ወረቅት አግኝታ ነበር ሆኖም በ2011 ዓ ም በፖሊዮ ቫይረስ የተጠቃ አንድ የሶማሌላንድ ሰው ወደ ሶማሌ ክልል በመግባቱ ቫይረሱ በቀላሉ በመሰራጨቱ በአማራ፣ኦሮሚያ፣ ድሬዳዋና ሌሎች አካባቢዎች በቀላሉ ተዳርሷል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተጠናከረ ክትትልና ክትባት ሲሰጥ ነበር ።»

https://p.dw.com/p/4A02s
Äthiopien Bahir Dar | Polio Impfkampagne
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት ዘመቻ 

የፀጥታ ችግር በሌለበቸው መላ የአገሪቱ አካባቢዎች ከዛሬ ጀምሮ ለ4 ተከታታይ ቀናት የሚዘልቅ የልጅነት ልምሻ ወይም የ(ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት መሰጠት መጀመሩን የኢትዮጵያ የጤና ተቋማት አስታወቁ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ16 ሚሊዮን በላይ ህፃናት የክትባቱ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ ተብሏል። በአማራ ክልል ደግሞ 2 ሚሊዮን 300ሺህ ህፃናትን ለመከተብ ታቅዷል። ወላጆች ህፃናትን እንዲያስከትቡ የሐይማኖት አባቶች መክረዋል፡፡ዛሬ በበኅርዳር የተጀመረውን የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ዘጋቢያችን አለምነው መኮንን ተመልክቶታል።።

የልጅነት ልምሻ ፖሊዮን ከዓለም ለማጥፋት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ1996 ጀምሮ ከፍተኛ ሥራ ሲሰራ መቆየቱንና ውጤት መመዝገቡን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለ ዓባይነህ ዛሬ ለአራት ቀናት የሚቀጥለውን አገር አቀፍ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በባሕር ዳር ከተማ ሲያስጀምሩ ተናግረዋል፡፡
በተደረገው የተጠናከረ ሥራም በኢትዮጵያ የመጨረሻው የልጅነት ልምሻ ሪፖርት የተደረገው በ2006 ዓም ሲሆን በ2009 ዓ ም ደግሞ ኢትዮጵያ “ከፖሊዮ ነፃ” ተብላ የምስክር ወረቅት አግኝታ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
እንደገና በ2011 ዓ ም በፖሊዮ ቫይረስ የተጠቃ አንድ ከሶማሌ ላንድ የተሸገረ ሰው ወደ ሶማሌ ክልል በመግባቱ ቫይረሱ በቀላሉ በመሰራጨቱ በአማራ፣ኦሮሚያ፣ ድሬዳዋና ሌሎች አካባቢዎች በቀላሉ መዳረሱን ተናግረዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተጠናከረ ክትትልና ክትባት ሲሰጥ እንደነበርም ገልጠዋል፡፡ በጥቅምት 2014 ዓ ም በተደረገ ዘመቻ ትግራይን፣ አፋርንና በወቅቱ በጦርነት ስር የነበሩ የአማራ ክልል አካባቢዎችን ሳይጨምር 16 ሚሊዮን 700ሺህ በላይ ህፃናት መከተባቸውን አስታውሰዋል፡፡
ዛሬ በተጀመረው የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በአማራ ክልል ለ2 ሚሊዮን 300ሺህ ህፃናት ክትባቱን እንደሚሰጥና በሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖችና በዋግኽምራ ብሔረሰብና ደሴ ከተማ አስተዳደር አካባቢዎች ግን በነበረው ጦርነት ምክንያት የመጀመሪያውን ክትባት ያልወሰዱ በመሆናቸው ክትባቱ እንደማይሰጥና ሁለቱም ክትባቶች በሌላ ጊዜ እንደሚሰጡ የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ ናቸው፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት ፕሮግራሞች ዳይሬክተር አቶ ወርቅነህ ማሞ ክትባቱ በጤና ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶችና ቤት ለቤት እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡ በመሆኑም ህብረተሰቡ ወደ ተጠቀሱ ቦታዎች በመሄድ ህፃናቱን እንዲያስከትቡ አሳስበዋል፡፡
ከአማራ ክልል የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተገኙት አቶ ፋሲል ታዬ ክትባት በየትኛውም ሐይማኖት የማይከለከል በመሆኑ ወላጆች ህፃናቱን እንዲያስከትቡ መክረዋል፡፡
ከአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የተገኙት አቶ የሱፍ ማሩም ወላጆች ሳይጠራጠሩ ልጆችን በማስከተብ ከበሽታ ሊጠብቋቸው እንደሚገባ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡
ዛሬ የተጀመረው የፖሊዮ ክትባት እስከፊታችን ሰኞ የሚቀጥል ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ከ16 ሚሊዮን 700ሺህ በላይ ህፃናት ይከተባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዓለምነው መኮንን

Äthiopien Bahir Dar | Polio Impfkampagne
ምስል Alemnew Mekonnen/DW
Äthiopien Bahir Dar | Polio Impfkampagne
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ