1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የልዩ ኃይል ጉዳይ በአማራ ክልል ያስከተለው ሕዝባዊ ቁጣ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 2 2015

የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና ለማደራጀት በሚል የተወሰነው ውሳኔ በአማራ ክልል ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቷል፤ ሕዝባዊ ቁጣም ቀስቅሷል ። በክልሉ በርካታ አካባቢዎች በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉባቸው ብርቱ የአደባባይ የተቃውሞ ሰልፎች ላለፉት ጥቂት ቀናት በተከታታይ ቀጥለዋል ። በታጠቁ ኃይሎች መካከልም የተኩስ ልውውጥ መደረጉ ተገልጧል ።

https://p.dw.com/p/4Ps6s
Äthiopien Bahir Dar | Friedlicher Protest gegen Premierminister Abiy
ምስል Alemenew Mekonnen/DW

በመከላከያና የታጠቁ ኃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጥ ነበር ተብሏል

የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና ለማደራጀት በሚል የተወሰነው ውሳኔ በአማራ ክልል ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቷል፤ ሕዝባዊ ቁጣም ቀስቅሷል ። በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉባቸው ብርቱ የአደባባይ የተቃውሞ ሰልፎች ካለፉት ጥቂት ቀናት አንስቶ በተከታታይ ቀጥለዋል ። በታጠቁ ኃይሎች መካከልም የተኩስ ልውውጥ የተደረገባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ነዋሪዎች ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ። በብዙ አካባቢዎች የመጓጓዣ አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን፤ የንግድ እንቅስቃሴ የታጎለባቸው አካባቢዎች መኖራቸውም ተገልጧል ። የክልሉ መንግሥት እና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራር በተለያዩ መግለጫዎቻቸው፦ «የአማራ ልዩ ኃይልን በተለየ መንገድ የሚጎዳ ውሳኔ አልተወሰነም» እያሉ ነው ። ነዋሪዎች በበኩላቸው፦ ኅብረተሰቡ ላይ ላለፉት ጊዜያት በተደጋጋሚ የጅምላ ግድያና መፈናቀል የፈጠሩ የተለያዩ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ሳይፈቱ አማራን ለጥቃት ለማጋለጥ የተሸረበ ሴራ ነው በሚል ተቃውሟቸውን ቀጥለዋል ። 

ውሳኔውን ተከትሎ ያልተጠናቀቁ የማንነት ጥያቄዎች፣ የወሰን ጉዳዮችና ሌሎችም ችግሮች በይደር እያሉ የአማራን ልዩ ኃይል እንደገና ማደራጀቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል በሚል በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ቅሬታዎችና አለመረጋጋቶች ተፈጥረዋል፣ አለፍ ሲልም በታጠቁ ኃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጥ የተደረገባቸው አካባቢዎች መኖራቸው እየተነገረ ነው ፡፡

ግጭት ከተነሳባቸው አካባቢዎች አንዱ የሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ አካባቢ ሲሆን በከተማዋ ውስጥ የትራንስፖርትና የገበያ አገልግሎቶች እንደሌሉ አንድ የዓይን እማኝ አመልክተዋል፣ ግን ከረፋድ ጀምሮ ወደ መቀሌና አላማጣ የሚያልፉ መኪናዎችን ማየታቸውን አስረድተዋል ፡፡ አስተያየት ሰጪው እንደሚሉት ግጭቱ በመከላከያ ሰራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ነው ፡፡ በአካባቢው የፋኖ ታጣቂና አመራር እንደሆኑ የገለፁልን አስተያየት ሰጪ በአካባቢው ግጭት መኖሩን ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል፣ ለግጭቱ መነሻም በርካታ ያልተጠናቀቁና ለአማራ ሥጋት የሆኑ ሥራዎች ሳይጠናቀቁ ልዩ ኃሉን ትጥቅ ማስፈታት ተገቢ ባለመሆኑ ነው ብለዋል፣ አሁን ፍጭቱ በፋኖ ታጣቂዎችና በመከላያ ሰራዊት መካከል እንደሆነም ገልፀዋል፣ በሌለኛው ወገን በኩል ያለውን ጉዳት ማወቅ ባችሉም በእነርሱ በኩል መስዋዕት የሆኑ እንዳሉም አመልክተዋል ፡፡ 

በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር መካከል በምትገኘው አላላ አካባቢ በአማራና በኦሮሞ ታጣቂዎች መካከል ግጭት ከጠዋት ጀምሮ መኖሩን የሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማ ነዋሪው አቶ እሸቱ ጌትነትና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰንበቴ ከተማ ነዋሪው አብደላ ያሲን ተናግረዋል ፡፡  በደሴ ከተማ ዛሬ ጠዋት ላይ የተቃዉሞ ሰልፍ እንደነበር አንድ ነዋሪ የገለፁ ሲሆን የትራንስፖርት አገልግሎትና የንግድ እንቅስቃሴ የለም ፡፡ 

ከአንድ ሳምንት በፊትም ተቃውሞ በአማራ ክልል ነበር ፦ ፎቶ ከማኅደር
ከአንድ ሳምንት በፊትም ተቃውሞ በአማራ ክልል ነበር ፦ ፎቶ ከማኅደርምስል Alemenew Mekonnen/DW

በባሕር ዳር ከተማ በተለምዶ ዓባይ ማዶ በተባለው አካባቢ ትናንት ምሽት 2 ሰዓት አካባቢ ወደ አንድ መጠጥ ቤት በተወረወረ ቦምብ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መሞታቸውንና መቁሰላቸውን አንድ የአካባቢው የዓይን እማኝ አመልክተዋል፡፡ ከተማዋን ዛሬ ከሰዓት በፊት ተዘዋውረን እንደተመለከትነውም አብዛኛዎቹ የንግድ ሱቆች ዝግ ናቸው፣ የከተማ ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ቢኖርም፣ ከባህርዳር የሚወጡም ሆነ ወደ ከተማዋ የሚገቡ የህዝብ ትራንስፖርት ሰጪ ተሸከርካሪዎች አይታዩም ። ትናንት በጎንደር ከተማ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተሳተፉት የጠለምት አማራ ፋኖ ብርጌድ አዛዥ መምህር ፀጋዬ እሸቱ በሰልፉ ላይ ከተላለፉ መልዕክቶች መካከል ሁሉም የክልል ልዩ ኃይሎች ትጥቅ መፍታት አለባቸው፣ የአማራ ልዩ ኃይል ተነጥሎ ትጥቅ አይፈታም የሚሉ ይገኙበታል ብለዋል፣ አያይዘውም መንግስት ያለውይይት ጉዳዩን በግብታዊነት የሄደበት በመሆኑ አሁንም ጉዳዩን ከህዝብና ከፀጥታ ኃይሉ ጋር እንዲወያይበት ጠይቀዋል፡፡ 
አንድ ጠንካራ የመከላከያ ሰራዊት እንዲገነባ ፍላጎት እንዳላቸው የሚገልፁት መምህር ፀጋዬ ሆኖም ከዚያ በፊት የሚከናወኑ የቤት ሥራዎች እንዳሉ ያምናሉ ፡፡ 

የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ ሰሞኑን ለብዙሀን መገናኛ በሰጡት ማብራሪያ፣ የሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች በአዲሱ አደረጃጀት ውስጥ ይገባሉ፡፡ “ኮሚቴ ተቋቁሞ እኩል በጋራ ነው እተፈፀመ ያለው፣ አሁን እኮ ከክላንሽኮቭ የተሻለ ብረት ነው ታጠቅ እያልነው ያለነው፣ እንጂ ትጥቅ ፍታ እልነው ኤደለም እያልነው ያለነው፣ ከእኛ ጋር ነው የሞተውና ወደ ህጋዊ መስመር እናስገባው እንጂ እንበትነው አላልንም፣ አንደኛውን ክልል ኃይል እንዲኖረው፣ ሌላውን ክልል ግን ኃል እንዳኖረው ግን አናደርግም፣ ክልሎች ሊይዙት የሚችሉት የፀጥታ ኃይል አንድ ብቻ ነው እሱም መደበኛፖሊስ” ብለዋል ፡፡ 

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ በሰጡት መግለጫ ፕሮግራሙ በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጠዋል፣ ሆኖም ግን የአማራ ልዩ ኃይል በተናጠል ሊበተን ነው፣ ልዩ ኃይሉ ትጥቅ ሊፈታ ነው የሚል ቅስቀሳ በመደረጉ ውይይቱ ከመጠናቀቁ በፊት አንዳንድ የልዩ ኃይል አባላት ከካምፕ እየወጡ መሄዳቸውን ተናግረዋል ፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ሰሞኑን ባስተላለፉት መልዕክት፣ አደረጃጀቱ ሳይገባቸው የሚቃወሙትን ለማስረዳትና ለማሳመን ጥረት እንደሚደረግ፣ ሆን ብለው የአፍራሽነት ሚና በሚጫወቱት ላይ ደግሞ ተገቢው የሕግ ማስከበር ርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል ፡፡ 

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ