1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የለጋሽ ሀገራት ርዳታ ለማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 10 2009

የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ጊዚያዊ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የርዳታ ድርጅቶች ከብዙ ጊዜ ወዲህ ጥሪ ሲያሰሙ ቆይተዋል። ጥሪውን ተከትሎም የአውሮጳ ህብረት ከሁለት ቀናት በፊት ባለፈው ሀሙስ በብራስልስ ከ80 የሚበልጡ ሀገራት፣ የዓለም ባንክና የተመድን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጭምር የተሳተፉበት የለጋሽ ሀገራት ጉባዔ  አስተናግዶ ነበር።

https://p.dw.com/p/2SvB9
Zentralafrikanische Republik Flüchtlingscamp in Bangui
ምስል picture-alliance/dpa/K. Palitza

zar for cms - MP3-Stereo

 

የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ፕሬዚደንት ፎስተ አርሾንዥ ቱዋዴራ  ሀገራቸው በሚቀጥሉት ዓመታት ግዙፍ ርዳታ እንደሚያስፈልጋት ጉባዔው ሲጀመር ገልጸው ነበር። ከለጋሽ ሀገራት የሚገኘው ገንዘብ በሀገራቸው የሚታየውን ጥቃት ለመታገል እና በብዙ ዓመታት የርስበርስ ወጊያ የተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ እንዳይባባስ እንደሚረዳ ቱዋዴራ አስረድተዋል። የብራስልሱ ጉባዔ ተሳታፊዎች ቀውስ ላመሰቃቀላት እና አስተማማኝ ያልሆነ ሰላም ለሚታይባት ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የፀጥታ ጥበቃ እና የመልሶ ግንባታዋ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት  2,2 ቢልዮን ዩሮ ርዳታ ለመስጠት ቃል ገብተዋል። ከዚህም መካከል የአውሮጳ ህብረት ለማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ እስካሁን የሚሰጠውን ርዳታ በእጥፍ በማሳደግ ከ700 ሚልዮን ዶላር በላይ፣ ማለትም፣  እጎአ ከ2016 እስከ 2020 ድረስ የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን 450 ሚልዮን ዶላር፣ የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት  ደግሞ 328 ሚልዮን ዶላር ርዳታ የአውሮጳ ህብረት አስታውቋል። በተፈጥሮ ሀብት ብትታደልም እጅግ ድሆች ከሚባሉት ሀገራት መደዳ በምትቆጠረው  የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ውስጥ ምንም እንኳን የኃይሉ ተግባር ቢቀንስም እና ባለፈው የካቲት ወር አዲስ ፕሬዚደንት ቢመረጥም፣ በሚሊሺያዎች መካከል ግጭቱ አሁንም አላበቃም። ሆኖም፣ ሀገሪቱ የመልሶ ግንባታውን ለማነቃቃት ዝግጁ መሆኗን እና ለዚህም መሳካት ግዙፍ ርዳታ እንደሚያስፈልጋት የቀረበው ጥሪ ሊደገፍ እንደሚገባው የአውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳዮች ተጠሪ ፌዴሪካ ሞጌሪኒም ገልጸዋል።
« ለጋሽ ሀገራት እና የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የተስማሙበት መርሀግብር ግዙፍ እና የተለጠጠ ነው። ግልጽ በሆነ እቅድ ላይ ነው የተስማማነው። እቅዱ እንዲሳካ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ወሳኝ ሚና መጫወት ይኖርበታል። መልሶ ግንባታውን ለማነቃቃት ብዙ፣ ብሎም ወደ 1,6 ቢልዮን ዶላር ሳያስፈልግ አይቀርም። »
የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ፕሬዚደንት ቱዋዴራ የመልሶ ግንባታውን እውን ለማድረግ መንግሥታቸው ጠንክሮ እንደሚሰራ ለጉባዔው ተሳታፊዎች አረጋግጠዋል።
« በዚሁ ወሳኝ ጉባዔ ላይ በብዛት መገኘታችሁ ራሱ በሀገሬ ማአሬ ላይ ያላችሁን እምነት ያረጋገጠልኝ ማስረጃ ነው። እርግጥ ነው፣ የሀገሬ ጊዚያዊ ሁኔታ እጅግ አዳጋች ነው፣ ግን፣ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም። »
የተመድ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ልዩ ተጠሪ ፓርፌ ኦናንጋ አንያንጋ ለዶይቸ ቬለ እንዳስረዱትም፣ በሀገሪቱ ሰላም ለማውረድ ከጥቂት ጊዜ በፊት በመንግሥት የተነደፈው እቅድ የሚያበረታታ ነው።
« በፕሬዚደንት ቱዋዴራ የሚመራው መንግሥት ከአስር ቀን በፊት የእርቀ ሰላም እቅዱን ያፀደቀበትን ድርጊት ልናሞግስ ይገባል። ሀገሪቱ አሁን ተጨባጭ የእርቀ ሰላም ስልት አላት። ይህ መልካም ዜና ነው፣ በተግባርም መተርጎም ይኖርበታል። ይኸው ዓቢይ ሂደትም መላ የሀገሪቱን ሕዝብ፣ ከታች ጀምሮ ያለውን ሰፊውን ሕዝብ የሚያጠቃልል ይሆናል። ዛሬ ልንል የምንችለው ይህንኑ የእርቀ ሰላም ሂደት ለማሳካት ከፕሬዚደንት ቱዋዴራ አመራር  ቁርጠኛ ተነሳሺነት አለ። ሲቭሉ ማህበረሰብ፣ የወጣት ድርጅቶች፣ የሀይማኖት መድረኮች ተሳታፊዎች ሆነዋል። ስለዚህ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ርዳታ ተጠቃሚ ይሆናል። በዚሁ የጋራ ተነሳሺነት አማካኝነትም በቅርቡ በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ  አንድ የመሻሻል ሂደት ልናይ እንደምንችል አምናለሁ። »
ዓለም አቀፍ ለጋሾች ለማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ለመስጠት ቃል የገቡትን ርዳታ በተለይ በሀገሪቱ የሚፈፀመውን ግዙፍ የመብት ጥሰት ለማብቃት የሚያስችሉትን  ተቋማት ለማጠናከሩ ተግባር ሊጠቀሙበት እንደሚገባ እና ይህen ማድረግ የሚያስችላቸውም ዕድል በወቅቱ እንደተከተላቸው የዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባልደረባ ኢላርያ አሌግሮዚ  ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

Belgien Brüssel - Federica Mogherini bei Pressekonferenz
ምስል picture-alliance/abaca/D. Aydemir

« ጉባዔው ለዓለም አቀፍ ለጋሽ ሀገራትና ድርጅቶች በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ውስጥ በተለያዩ ፣በተለይም፣ በፍትሑ አውታር ዘርፎች ላይ  ለመስራት የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ይሰማናል። ምክንያቱም፣ በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ውስጥ ጥፋተኞች ካለቅጣት የሚታለፉበት አሰራር ነው የተስፋፋው። በሀገሪቱ  የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች አባላት እጅግ ዘግናኝ የመብት ጥሰት ፣ እንዲሁም፣ በስብዕና አንፃር በዓለም አቀፍ ሕጎች መሰረት የሚያስቀጡ ከፍተኛ ወንጀሎችን  ፈጽመውም በመላይቱ ሀገር በነፃ ሲዘዋወሩ እና አሁንም ሁከትና ግጭትን ሲቀሰቅሱ ይታያሉ። »
እጎአ በ1960 ዓም ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነፃነቷን ካገኘች ወዲህ የተደጋጋሚ የመፈንቅለ መንግሥት ሰለባ የሆነችው በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የመጨረሻው መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደው፣ በብዛት ሙስሊሞች የሚጠቃለሉበት የሴሌካ ዓማፅያን ቡድን እጎአ በ2013 ዓም ክርስትያኑን የቀድሞው ፕሬዚደንት ፍራንስዋ ቦዚዜን ባስወገዱበት ጊዜ ነበር።   

Karte Zentralafrikanische Republik Deutsch
ምስል DW

መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎም በሴሌካ ዓማፅያን እና በአንፃራቸው በተነሱት ክርስትያኖቹ ፀረ ባላካ ሚሊሺያዎች መካከል የኃይሉ ተግባር ቀጥሎ፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል፣ እጅግ ብዙዎችም ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለዋል፣ ሌሎችም ወደ ሌሎች ሀገራት ተሰደዋል። ከመጋቢት 2013 ዓም መፈንቅለ መንግሥት በኋላ በሀገሪቱ ደም መፋሰስን ለማስቆም የፈረንሳይ ወታደሮች ፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላም 12,000 ወታደሮች ያጠቃለለ የተመድ ተልዕኮ፣ ሚኑስካ» መሰማራቱ ይታወሳል።   የፈረንሳይ ወታደሮች ባለፈው ወር ሀገሪቱ ከሞላ ጎደል ተረጋጋታለች በሚል  ለቀው ቢወጡም፣ «ሚኑስካ» እንዳስታወቀው፣ ከሁለት ሳምንት በፊት የሴሌካ አባላት ባካሄዱት ጥቃት ቢያንስ 36 ሰዎች ተገድለዋል።  እንደ ፖለቲካ ታዛቢዎች ግምት፣ ፕሬዚደንት ቱዋዴራ የሚመሩት መንግሥትም ከባንጊ እና በደቡቡ የሀገሪቱ ከፊል ካሉ አንዳንድ ከተሞች በስተቀር ሙሉ ቁጥጥር የሌለው ሲሆን፣ የሴሌካ ዓማፅያን በቅርቡ በመዲናይቱ ባንጊ አዲስ ጥቃት ሊጀምሩ የሚችሉበት ስጋት ተደቅኖዋል።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ