1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢራን፤የአሜሪካና ብሪታንያ ጠብ

ሰኞ፣ ሐምሌ 22 2011

ጠባብ ናት-ከ55-እስከ 95 ኪሎ ሜትር ትሰፋለች።ቀጭን ናት ረጅም።167 ኪሎ ሜትር ትረዝማለች።ግን ዓለም ከሚያነደዉ ነዳጅ ዘይት 20 በመቶዉ፣ ከፈሳሽ ጋሱ አንድ ሰወስተኛዉ ይንቆረቆርባታል።

https://p.dw.com/p/3MvYc
Iran Seemanöver im Persischen Golf Straße von Hormus
ምስል Tasnim

የሆርሙዝ ሰርጥ፣ ኢራን፣ ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ

የብሪታንያ መሪዎች የአዉሮጳ ሕብረት ተስማም አልተስማማ ሐገራቸዉን እስከ ጥቅምት ማብቂያ ድረስ ከትልቁ ማሕበር ለማስወጣት ወስነዋል።የሆርሙዝ ሰርጥን የሚያቋርጡ የብሪታንያ መርከቦችን ከኢራን ጥቃት ለመከላከል ግን «የጠሉትን» ማሕበር አባላት ርዳታ ይጠይቃሉ።የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት በኢራን ላይ ዳግም ማዕቀብ መጣላቸዉን ያልደገፉ የስለላ ኃላፊያቸዉን ሽረዉ ሌላ ሾመዋል።የቴሕራን ፖለቲከኞች የዋሽግተንን «ስምምነት የጣሰ» ርምጃ፣የለንደኖችን ዛቻም ሌሎቹ የአዉሮጳ መንግስታት አለመቃወማቸዉን ይተቻሉ።ግን ከአዉሮጶች ጋር  እንግባባለን ይላሉ።አዉሮጶች የኢራኖችን ቅሬታ እዉነትነት እየመሰከሩ፣የአሜሪካኖችን ርምጃ ችላ እያሉ ዉዝግብ ፍጥጫዉን አፍጥጠዉ ያያሉ።ጦር ያሰለፈዉ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ-ምጣኔ ሐብታዊ ቀዉስ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።

ሰዉ በባሕር ላይ መቅዘፍ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አሳ ያስግር-ይዋኝባት፣ሸቀጥ ይጫን-ባሪያ ያግዝባት፣ ኃይማኖት ሰባኪ ያሳፍር-ነዳጅ ያመላልስባት፣ ሰላይ ይላክ-ጦር ያስፍራባት፣ በየዘመኑ እንደተዋጋ፣ እንደተጋጨ፣ እንደተወዘገበባት፣ እየከበረ እደከሰረባት ነዉ።የሆርሙዝ ሰርጥ።ጠባብ ናት-ከ55-እስከ 95 ኪሎ ሜትር ትሰፋለች።ቀጭን ናት ረጅም።167 ኪሎ ሜትር ትረዝማለች።ግን ዓለም ከሚያነደዉ ነዳጅ ዘይት 20 በመቶዉ፣ ከፈሳሽ ጋሱ አንድ ሰወስተኛዉ ይንቆረቆርባታል።

 በ1973 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የዮምኩፑር ዉጊያ ተብሎ የሚጠራዉ የአረብ እስራኤሎች ጦርነት ሲግም አረቦች የጣሉት የነዳጅ ዘይት ሽያጭ ማዕቀብ የምዕራብ አዉሮጳ በጣሙን የእስራኤልን ዋነኛ ደጋፊ የዩናይትድ ስቴትስን ምጣኔ ሐብት አሽመድምዶት ነበር።የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የሪቻርድ ኒክሰን የሆርሙዝ ሰርጥን «የነፃዉ ዓለም የምጣኔ ሐብት ሕልቅት» የሚል ብሒላቸዉ ገንኖ የተሰማዉም ያኔ ነበር።

Iran Krise l Straße von Hormus
ምስል picture alliance/dpa/NASA/The Visible Earth

ኒክሰን ቃላቸዉን ገቢር ለማድረግ ለእስራኤል ዙሪያ-መለስ ድጋፍ ከመስጠት በተጨማሪ የአረቦችን የነዳጅ ጉርጓዶች የሚቆጣጠር ጦር ለማዝመት ዐቅደዉ ነበር።ይሁንና አሜሪካኖች ቬትናም ላይ የገጠማቸዉ ሽንፈት፣የዎተርጌቱ ቅሌት፣የሶቭየት ሕብረት አፀፋ ያሳደረባቸዉ ሥጋት፣የኢራን ልገሳ ሰበብ ምክንያት ሆኖ ዕቅዱ በዕቅድ ቀረ።

አረቦች በጣሉት ማዕቀብ ሰበብ ነዳጅ ለጠማዉ ምዕራባዊ ቤንዚን ጋዝዋን በገፍ የቸረችዉ ወይም የቸረቸረችዉ የሻሕዋ ኢራን ነበረች።የኢራን እስላማዊ አብዮተኞች በ1979 የቴሕራንን ቤተ-መንግሥት ከተቆጣጠሩ በኋላ ግን የሻሕዋ ኢራንን ሥፍራ-የቢን ሳዑዷ ሪያድ፣የአረቦችን ሥፍራ ኢራን ተረክባለች።በስድስት ዓመት ልዩነት የምዕራባዉያን ወዳጅ የነበረችዉ -ኢራን ጠላት፣ «ጠላት» የነበሩት አረቦች ወዳጅ ሲሆኑ የዋሽግተንን በዉጤቱም የቴልአቪቭ-ለንደን-ፓሪስን ፖለቲካ የሚዘዉሩት ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተር ነበሩ።

የኢራን እስላማዊ አብዮተኞች የቴሕራንን ቤተ-መንግስት በተቆጣጠሩ ማግሥት ካርተር አስጠነቀቁ «የፋርስ ባሕረ ሰላጤን ለመቆጣጠር የሚሞክር ማንኛዉም የዉጪ ኃይል፣በዩናይትድ ስቴትስ መሠረታዊ ጥቅም ላይ ጥቃት እንደከፈተ ይቆጠራል።» አሉ ፕሬዝደንት ካርተር «እንዲሕ ዓይነቱ ጥቃት የጦር ኃይልን ጨምሮ አስፈላጊ በሆነዉ መንገድ ሁሉ አፀፋ ይገጥመዋል።» አከሉ።

Nicaragua - Javad Zarif, der iranische Außenminister
ምስል taghribnews

«የዉጪ ኃይል።»

ከካርተር እስከ ትራምፕ የተፈራረቁት የአሜሪካ መሪዎች ያን የዉጊያ-ዉዝግብ፣የጥፋት-እልቂት ደግሞ በተቃራኒዉ የነዳጅ-የጋስ፣ የወርቅ-ስጋጃ  «ጎተራን» ለመቆጣጠር በቀጥታም፣በተዘዋዋሪም ተዋግተዋል- አዋግተዋል፣ሚሊዮኖችን አጫርሰዋል።ዘንድሮ ተረኛዉ በርግጥ ትራምፕ ናቸዉ።

   «በተደጋጋሚ የተሰጠዉን ማስጠንቅቂያ አልቀበል ብሎ በጣም በቅርብ ርቀት፣ በግምት አንድ ሺሕ ያርድ  ላይ እየበረረ የመርከባችንን ደህንነት ያሰጋ በነበረዉ በኢራን ድሮን ላይ መርከባችን የመከላከያ ርምጃ ወስደዷል።ድሮኑ ወዲያዉ ወድሟል።ይሕ ኢራን በተደጋጋሚ ከወሰደቻቸዉ የጠብ ጫሪነት እርምጃዎች የቅርቡ ነዉ።»

«ጠብ ጫሪነት።»

ያሁኑ የኢራን የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር መሐመድ ጃባድ ዛሪፍ ካርተር «የዉጪ ኃይል» ያሏቸዉን ወገኖች ባስጠነቀቁበት ወቅት ገና የ19ኛ ዓመት ወጣት ነበር።ለትራምፕ ሰሞናዊ ዛቻ የሰጡት መልስ ግን የ40  ዘመኑ ርቀት የለወጠዉ አካላዊን፣ ሰዉ እንጂ አስተሳሰቡን እንዳልሆነ ጠቋሚ ነዉ።ዛሪፍ ጠያቂያቸዉን ጋዜጠኛ መልሰዉ ጠየቋት።«ማነዉ ጠብ ጫሪዉ?» ብለዉ።

                                 

«ባለን መረጃ መሠረት የተመታብን ድሮን የለም።ሥለዚሕ ከኛ ድሮኖች አንዱን የመቱ አይመስልም።ምናልባት የራሳቸዉን ወይም የሌላ ወገንን ድሮን መትተዉ ይሆናል።ግን፤ ጠብ ጫሪነት? እንዲያዉ የመቱት የኛ ድሮን ቢሆን እንኳ እኛ እዚያዉ እሰፈራችን ነን።የዩኤስ የባሕር ኃይል መርከብ ያለዉ  ከሐገሩ የባሕር ጠረፍ 6ሺሕ ማይል ርቀት ላይ ነዉ።እና እስኪ እኔ ልጠይቅሽ «ጠብ ጫሪዉ ማነዉ?»

ርግጥ ማን ይሆን ጠብ ጫሪዉ? ቀላል ግን ለመመለስ የሚያስፈራ ጥያቄ።ሌላ ጥያቄ፣ እዉነተኛዉስ ማነዉ? ትራምፕ ወይስ ዛሪፍ።አናዉቅም።የሚታወቀዉ ትራምፕ ያሉት እዉነት፣ ዛሪፍ ያሉት ሐሰት ከሆነ ድሮን መትቶ በመጣል ኃያል ፈርጣማ፣ ሐብታሚቱ ትልቅ ሐገር፣ ከትንሺቱ እስላማዊ ሪፐብሊክ ጋር በእግር ኳስ ተቻዋቾች ቋንቋ አንድ ለአንድ ናቸዉ።

እዉነቱ ከተገለበጠ ደግሞ ኢራን ዩናይትድ ስቴትስን አንድ ለዜሮ ትመራለች እንበል።የአያቶላሁቹ ሐገር ከዩናይትድ ስቴትስ የቅርብ ወዳጅ ከብሪታንያ ጋር ደግሞ መርከብ በመያዝ አንድ ለአንድ ሆናለች።ጅብላርተር የሰፈረዉ የብሪታንያ ጦር የኢራንን ነዳጅ ጫኝ መርከብ በያዝ በሁለተኛዉ ሳምንት የኢራን ባሕር ኃይል የኢራንን የባሕር ክልል ጣሳ ያለዉን የብሪታንያ ባንዲራን የሚዉለበልብ መርከብን ከነሠራተኞቹ ማርኳል።

Iran Krise l Straße von Hormus
ምስል picture alliance/dpa/NASA/The Visible Earth

ባለፈዉ ሳምንት ከ10 ዳዉኒንግ ስትሪት ቢሯቸዉን ያስረከቡትም ሆኑ የተረከቡት የብሪታንያ ወግ አጥባቂ ፖለቲከኞች በነባር ፖለቲካዊ አስተሳሰባቸዉ አንድ ናቸዉ።ተሰናባቾቹም ሆኑ አዲሶቹ መሪዎች ባንድ በኩል ዩናይትድ ስቴትሱን ፕሬዝደንት የዶናልድ ትራምን መስተዳድር በማስደሰት፣ በሌላ በኩል በ2015 ከኢራን ጋር የተፈረመዉን የኑክሌር ስምምነት በማክበር ተቃርኖ እየዋዠቁ ነዉ።

ኢራን ወይም ደጋፊዎችዋ በሆርሙዝ ሰርጥ ወይም ባካባቢዉ የሚቀዝፉ ተጨማሪ የብሪታንያ መርከቦችን እንዳይተናኮሉ ለመከላከል ከኢራን ጋር ከመደራደር፣የኢራንን መርከብ እንደማይነኩ ቃል ከመግባት፣ ወይም የጋራ ሕግ ከማርቀቅ ይልቅ እስካሁን መፍትሔ ያሉት መርከቦቻቸዉን በባሕር ኃይል ማስጠበቅ ነዉ።መርከቦቹን በባሕር ኃይል ለማስጠበቅ ደግሞ የብሪታንያ ንጉሳዊ ባሕር ኃይል ብቻዉን ወጪዉን አትችለዉም።

በስልጣን ላይ ያለዉ የብሪታንያ ወግ አጥባቂ ፓርቲ የቀድሞ መሪ ኢያን ስሚዝ በቀደም እንዳሉት የለንደኖችን ችግር የተረዳዉ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ለብሪታንያ ርዳታ ለመስጠት ጠይቆ ነበር።«ታማኝ ከሆኑ ምንጮች እንደተረዳሁት፣ የብሪታንያ የመርከብ ጉዞን ለመርዳት፣ብሪታንያ የአሜሪካንን ኃይል እንደትጠቀም ዋሽግተን ፈቅዳ ነበር።እነሱ (የብሪታንያ ባለስልጣናት) አልተቀበለዉም።»

ሐበሻ እንደሚለዉ «እንግሊዝ ብልጥ» ነዉ።አብዛኛዉ ዓለም ፈርቶ እንጂ ፈቅዶ ካልተቀበለዉ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር በተናጥል ያዉም በይፋ በጦር መተባበሩን ለጊዜዉም ቢሆን አልፈቀደም።ለንደኖች ሲቸገሩ የተፉትን የሚዉጡ፣ ሲመቻቸዉ የዋጡትን የሚተፉ ናቸዉ።ሐገራቸዉን ከአዉሮጳ ሕብረት አባልነት ለማስወጣት ሌት ተቀን እየባተሉ ጭንቁ ሲመጣ አሜሪካኖችን ገሸሽ አድርገዉ ከአዉሮጶች እንደሚለጠፉ አስታወቁ።

እሳከለፈዉ ሳምንት ድረስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት ጄርሚ ሐንት ይሕን አረጋግጠዋል።«በዚሕ በጣም አስፈላጊ አካባቢ የሚደረግ የመርከብን የሰራተኞቻቸዉን ጉዞ ለመጠበቅ፣አዉሮጳ መራሽ የባሕር መከላከያ ተልዕኮ እንዲመሰረት እንጥራለን።»

የአዉሮጳ ሕብረትም ሆነ አባል ሐገራቱ ቢዘገይ ጥቅምት ማብቂያ ላይ ሕብረታቸዉን ጥላ የምትወጣዉ ብሪታንያ ላቀረበችዉ ጥያቄ እስካሁን በይፋ የሰጡት መልስ የለም።ወትሮም ግጭት ጦርነት ያልተለየዉን የፋርስ ባሕረ ሰላጤን በሌላ ጦርነት ለማዉደም የሚደረገዉ ዝግጅት፣ፉከራና ኃይል መፈታተሽ እንዲቆም ግን ሕብረቱ ካንጀትም ሆነ ካንገት ማሳሰቡ አልቀረም።

የድሮን መመታት፤የመርከብ መያያዝ፣ የጦር ፍጥጫም ያስከተለዉ ዩናይትድ ስቴትስ ከ2015ቱ የኑክሌር ስምምነት በተናጥል በመዉጣትዋ ምክንያት መሆኑ አላከራከረም።ዩናይትድ ስቴትስ ስምምነቱን በተናጥል አፍርሳ በኢራን ላይ ዳግም ማዕቀብ መጣልዋንም የአዉሮጳ ሕብረት፣ሩሲያና ቻይና እኩል ተቃዉመዉታል።ቤጂንግና ሞስኮ አዉግዘዉታልም።

ከመቃወም ምናልባት ዉግዘት ባለፍ ግን በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የፀደቀዉ ስምምነት በመጣሱ በትራምፕ አስተዳደር ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ለመዉሰድ አይደለም ለማሰብም እስካሁን የሞከረ አንድም መሪ የለም።

Iran Beschlagnahmung Öltanker Stena Impero
ምስል picture-alliance/dpa/H. Shirvani

ኢራንም አሜሪካን እያወገዘች፣ ሌሎቹን እያባበለች የሚመጣዉን ለመቀበል እየተዘጋጀት ጊዜ ለመግፋት ያሰበች ትመስላለች።ትናንት ቪየና-ኦስትሪያ ዉስጥ ከስምምነቱ ተፈራራሚ ሐገራት ተወካዮች ጋር የተነጋገሩት የኢራን ምክትል ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰይድ አባስ  አራጋቺም ሌላ አላሉም።«ኢራን በ JCPOA መሠረት የነዳጅ ዘይት የመሸጥ መብት አላት።ኢራን ነዳጅ ዘይት እንዳትሸጥ ለማገድ የሚደረግ ማኝኛዉም ሙከራ JCPOA እና የፀጥታዉ ምክር ቤት ዉሳኔ ቁጥር 2231ን መቃረን ነዉ።ስለዚሕ ኢራን ነዳጅ ዘይት እንዳትሸጥ ዩናይትድ ስቴትስማከላከሏ የፀጥታ ጥበቃዉን ምክር ቤት ዉሳኔ የሚጥስ ነዉ።»

ከዩናይትድ ስቴትስ ለሌላ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትን ስምምነትና ዉሳኔ የማስከበር ስልጣን ያላቸዉ አራት ሐገራት አሉ።ብሪታንያ፣ፈረንሳይ፣ሩሲያና ቻይና።አራቱ ሐገራት፣ ጀርመን አምስተኛ ተጨምራ JCPOA የተባለዉን የኢራን የኑክሌር አጋጅ ስምምነትን ተፈራርመዋል።የአምስቱን ሐገራት ባለስልጣናት ትናንት ከኢራኑ ምክትል ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የሰሙትን ከአምና ግንቦት ጀምሮ በቀጥታ ሲሰሙት፣ ሲያሰላስሉት፣ባለሙያዎች ሲተነትኑት ዓመት ከሁለት ወራት አስቆጥረዋል።ሰሙ።አስተነተኑ።በቃ።ለነገሩ የዋሽግኑ ጠንካራ መሪ ዶናልድ ትራምፕ የዓለምን የንግድ ስምምነት፤ የተፈጥሮ ጥበቃን ስምምነት፣ የእየሩሳሌምን፤ የጎላን ኮረብታን ባለቤትነት መነቃቅረዉ ሲጥሉት ማን ምን አደረገ? ትራምፕ ከዉጪ አይደለም ከቅርብ አማካሪዎቻችም ከሳቸዉ ሐሳብ የተለየ አስተያየት ያለዉን አይቀበሉም።

ከኢራን ጋር የተደገዉን ስምምነት እንዳያፈርሱ የጠየቁ ሹሞቻቸዉን ተራ በተራ እያባረሩ ነዉ።እስካሁን የመጨረሻዉ የብሔራዊ የስለላ የበላይ ኃላፊ ዳን ኮትስ ናቸዉ።የአሜሪካ መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት ከ2017 ጀምሮ የዓለምን ግዙፍ የስለላ መስሪያ ቤት የመሩት ኮትስ ኢራን ስምምነቱን ስላከበረች ተጨማሪዉ ማዕቀብ ይቅር አሉ። ተባረሩ።  

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ