1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 18 2011

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የስነ ምግባር አዋጅን አፅድቋል። ምክር ቤቱ  በአራተኛ ዓመት የስራ ዘመን፣ ሶስተኛ አስቸኳይ ስብሰባው የቀረበለትን የአዋጅ ረቂቅ በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል።

https://p.dw.com/p/3ORCh
Äthiopien Parlament in Addis Abeba
ምስል DW/Y. G. Egziabher

 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ

ለዕረፍት የተዘጋው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የስነ ምግባር አዋጅን አጸደቀ። ምክር ቤቱ በርካታ አከራካሪ ጥያቄዎችን ያስነሳውን አዋጅ ያጸደቀው በሙሉ ድምጽ ነው። 

በአዋጁ ረቂቅ ላይ በምርጫ ወቅት ሴት እና ወንድ ተወዳዳሪዎች እኩል ድምጽ ቢያገኙ ሴቷ እንደምታሸነፍ መደንገጉ በዛሬው አስቸኳይ ስብሰባ ተቃውሞ ቀርቦበታል። ተቃውሟቸውን ካቀረቡ የምክር ቤት አባላት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ መሐመድ ሀሰን “ውሳኔው ህገ መንግስቱን የሚጻረር ነው” ብለዋል። ለጥያቄው በምክር ቤቱ የህግ፣ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኩል በተሰጠ ምላሽ ይህ ድንጋጌ የተካተተው በህገ መንግስቱም ከተፈቀደው ለሴቶች ከሚሰጥ ልዩ ድጋፍ (affirmative action) አንጻር ታሳቢ ተደርጎ ነው። ሆኖም የምክር ቤቱ አባላት ካካሄዱት ክርክር በኋላ ድንጋጌው ውድቅ ተደርጓል።

Äthiopien Parlament in Addis Abeba
ምስል DW/Y. G. Egziabher

በረቂቅ አዋጁ ውይይት ወቅት አወዛግቦ የነበረው በምርጫ የሚወዳደሩ የመንግስት ሰራተኞች ከስራ እንዲለቅቁ ያስገድድ የነበረው አንቀጽም እንዲሻሻል ተደርጓል። በጸደቀው አዋጅ መሰረት ዕጩ ተወዳዳሪዎች በምርጫ ወቅት ያለ ደሞዝ የዓመት ፍቃድ መውሰድ እንደሚችሉ ተገልጿል። ተወዳዳሪዎቹ በምርጫ ጊዜ የመንግስትን ንብረት እንዳይገለገሉም አዋጁ ከልክሏል። 

በአዋጁ ላይ አዲስ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ለመመስረት 10 ሺህ፣ ለክልል ፓርቲ ደግሞ አራት ሺህ መስራች አባላትን የሚጠይቀው ክፍል በተቃዋሚ ፓርቲዎች ተደጋጋሚ ቅሬታ ቢቀርብበትም ተቃውሞው ተቀባይነት አላገኘም። የተቃዋሚ ፓርቲዎች በአዋጁ 35 አንቀጾች ላይ በአጠቃላይ ቅሬታ ማቅረባቸውን የህግ፣ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታውቋል። ዛሬ የጸደቀው አዋጅ በረቂቅ ደረጃ ከነበረው 149 የቃላት እና ሌሎችም ማሻሻያዎች እንደተደረጉበት ተገልጿል።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።

ዮሃንስ ገብረ እግዚያብሔር / ተስፋለም ወልደየስ 

ልደት አበበ