1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የህክምና ባለሙያዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 4 2011

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲጎለብት የሚፈለግ መልካም ተግባር ነው። በውጪው ዓለም በከፍተኛ የህክምና ሙያ ተሠማርተው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያ ዶክተሮች ወደ ሀገራቸው ጎራ እያሉ በተካኑበት የህክምና ዘርፍ ህሙማንን ሲረዱ መመልከት ብዙዎች ይመኛሉ።

https://p.dw.com/p/3KBhL
Äthiopien Dr. Wubtaye Duressa Tekle bei einer orthopädischen Operation
ምስል Dr. Wubtaye Duressa Tekle

የአጥንት ቀዶ ጥገናው

ዶክተር ውብታዬ ዱሬሳ ተክሌ በተለያዩ ጊዜያት በተካኑበት የህክምና ዘርፍ ላይ ሙያዊ ማብራሪዎችን በመስጠት የሚተባበሩ ቤተኛችን ናቸው። ከወራት በፊትም የዲስክ መንሸራተት ምንድነው ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ ስለጀርባ እና የወገብ ህመም በቂ ግንዛቤ የሚሰጥ ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወስ ይሆናል። በሙያቸው ሀገር ቤት ለሚገኙ ታማሚ ወገኖች በነጻ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ማቀዳቸውን በማወቃችን በቅርበት ስንከታተላቸው ቆየን እና ከሰሞኑ ደርሰው መመለሳቸውን ገለፁልን።

ዶክተር ውብታዬ ወደ አዲስ አበባ በራሳቸው ወጪ የሄዱት እጅግ ውድ ክፍያ የሚጠየቅበትን የታፋ መገናኛ አካባቢ ህመም የሚገላግል የቀዶ ህክምና ርዳታ ለታማሚዎቹ ለማድረግ ነበር። ለሕክምናው የሚያስፈልገው ቁሳቁስ እሳቸው እንደገለፁት በሰዓቱ ባለመድረሱ ጥቂት ታማሚዎችን ብቻ ለማከም ነው የቻሉት። ታማሚዎቹ አቅም ኖሯቸው ገንዘብ ቢከፍሉ ለህክምናው ከ200,000 የኢትዮጵያ ብር በላይ ያስወጣል።

ዶክተር ውብታዬ አስበው የሄዱት በሳምንት ውስጥ ቢያንስ 20 በዚህ ህመም የሚሰቃዩ ሰዎችን አክመው ለመመለስ ነበር። ህክምናው የሚያስፈልጋቸው እና ያንን ለማግኘት አቅሙ የሌላቸው ወገኖች ተመርጠው ተዘጋጅተው ቢጠብቁም የተባለው አስፈላጊ የህክምና ቁሳቁስ በጊዜው ባለመድረሱ ሳይሳካላቸው በመቅረቱ ቢያዝኑም በሙያው ዘርፍ የተሰማሩ ሀኪሞች እና ተማሪ ሃኪሞች በተገኙበት የተከናወነው ሁሉ ደግሞ መንፈሳቸውን አነቃቅቶታል።

Äthiopien Dr. Wubtaye Duressa Tekle bei einer orthopädischen Operation
ምስል Dr. Wubtaye Duressa Tekle

በወቅቱ ተገኝተው በከፍተኛ የአጥንት ሀኪም ቀዶ ህክምናው ሲደረግ ከተከታተሉ አንዱ ዶክተር ፀጋዬ ማሞ ነበሩ። በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የመጨረሻ የህክምና የትምህርት ዓመት የአጥንት ህክምና ተማሪ እና ባለሙያው ዶክተር ፀጋዬ በሆስፒታሉ እጅግ በርካታ ታማሚዎች ቢኖሩም እንዲህ ያለው ህክምና ተፈላጊው ቁሳቁስ ሲገኝ በዘመቻ መልክ የሚሠራ እንደነበር ነው የገለፁልን። ዶክተር ፀጋዬ ምንም እንኳ መገጣጠሚያ ላይ በዕድሜ አንዳንዴም በአደጋ፤ አልፎ አልፎም በተፈጥሮ ስቃይ የሚያስከትለው ህመም ብዙዎችን ቢያጋጥምም ህክምናው ውድ በመሆኑ አቅም ያላቸው ብቻ መታከም እንደሚችሉ አስተውለዋል። በአሁኑ ጊዜም ጥቁር አንበሳ ውስጥ ብቻ እንኳን ከ400 እና 500 የሚበልጡ ታማሚዎች እንደሚገኙም አመልክተዋል። እሳቸውም ሆኑ ሌሎች የሙያ ባልደረቦቻቸው ተመርቀው ሲወጡ ብዙዎችን የማከም አቅሙ ቢኖራቸውም አስፈላጊው የህክምና ቁሳቁስ ግን ሀገር ውስጥ የለም።

Äthiopien Dr. Wubtaye Duressa Tekle bei einer orthopädischen Operation
ምስል Dr. Wubtaye Duressa Tekle

ከጀርመን ሀገር ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወደ ትውልድ ሀገራቸው ሄደው የተመለሱት የአጥንት ከፍተኛው ሀኪም ዶክተር ውብታዬ ፤ ለቀዶ ህክምናው የሚያስፈልጓቸው ቁሳቁሶች አዲስ አበባ ደርሰው በጊዜው ስላልተለቀቁላቸው ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ባገኙትዝ አራት ሰዎችን ብቻ ነው ያከሙት። አቤት ሆስፒታል በበኩሉ ከ14 እስከ 20 የሚደርሱ ለህክምናው መክፈል የማይችሉ ታማሚዎችን አዘጋጅቶ ሲጠባበቅ ቢቆይም አለመሳካቱን ዶክተር ዐቢይ ወርቁ የሆስፒታሉ የአጥንት ህክምና ዘርፍ ባልደረባ ቀዶ ህክምናውን ለማድረግ የሚረዱት ዕቃዎቹ ባለመድረሳቸው መስተጓጎሉን ገልፀውልናል።

በዚህም መገጣጠሚያ ላይ ባላቸው ከባድ ህመም የሚሰቃዩ እና ከፍለው መታከም የማይችሉ ምስኪን ታማሚዎችም በነፃ ቀዶ ህክምናው ተደርጎላቸው ከህመሙ ፋታ የማግኘት ዕድላቸው ደበዘዘ። ዶክተር ውብታዬ እነዚህን ታማሚዎች ለማከም ተስፋ ሰጥተዋቸው ባለመሳካቱ ማዘናቸውን አልሸሸጉም።

Äthiopien Dr. Wubtaye Duressa Tekle bei einer orthopädischen Operation
ምስል Dr. Wubtaye Duressa Tekle

ይህም ሆኖ ተስፋ የቆረጡ አይመስሉም፤ በመጪው የክረምት ወቅት ከአሜሪካ ወደ ሀገር ቤት ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚገቡ ሌላ የአጥንት ህክምና ከፍተኛ ባለሙያ ስላሉ እሳቸው ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉ ነግረውናል። ይህ የባሙያዎቹ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የከፍተኛ ህክምና ባለሙያ ያለህ ለምትለው ሀገር አዎንታዊ አስተዋፅኦ መሆኑ ባያነጋግርም፤ ታማሚዎች ዕድሉን ማግኘት እንዲችሉ ለሥራቸው መንገዱን ማመቻቸት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን የሁሉም የኢትዮጵያ ባለድርሻ አካላት መሆኑን አፅንኦት ሊሰጠው እንደሚገባ በማሳሰብ እንሰናበት። የበጎ ፈቃድ አገልግሎታቸውን ተሞክሮ ያካፈሉንን እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ