1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሄፒታይተስ ህክምና

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 28 2011

በተሐዋሲ አማካኝነት ጉበት ላይ ጉዳት የሚያደርሰው በህክምናው ቫይራል ሄፕታይተስ በመላው ዓለም 325 ሚሊየን ሰዎችን መያዙን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። በተለይ ሄፕታይተስ ቢ እና ሲ የሚባለው የበሽታው አይነት ሳይታወቅ ለረዥም ጊዜ በሰውነት ተደብቆ ሕይወት ሊቀጥፍ የሚችል በመሆኑ ፤ ድምፅ አልባው ገዳይ በመባል ይታወቃል።

https://p.dw.com/p/3Oxa3
Impfaktion für Jugendliche
ምስል picture-alliance/dpa/B. Roessler

ሕክምናው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት ይሆን?

በሐምሌ ወር ማለቂያ ባሉት ቀናት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰዎች ስለሄፕታይተስ ግንዛቤ እንዲያገኙ ቅስቀሳ ተደርጓል። በወቅቱ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በትዊተር ባስተላለፉት ጥሪ ምንም እንኳን በሽታው በመላው ዓለም 325 ሚሊየን ሰዎችን መያዙ ቢታወቅም፤ አሁንም ከ10 ሰዎች ስምንቱ ተገቢውን ምርመራ እና ህክምና ማግኘት አለመቻላቸውን አመልክተዋል።

ሄፕታይተስ በየዓመቱ 1,3 ሚሊየን ሕዝብ እንደሚገድል ባለፈው ሐምሌ 21 1ቀን 2011ዓ,ም ስለበሽታው ግንዛቤ ለመስጠት የተሰራጨው መረጃ ያመለክታል። በሽታውን አስቀድሞ መከላከልም ሆነ ታክሞ መዳን እንደሚቻል የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በዕለቱ ያስተላለፉት መልእክት አመልካች ነው። ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በትዊተር የጽሑፍ እና የቪድዮ መልእክታቸው ሃገራት ለዚህ በሽታ የሚደረገውን ምርመራም ሆነ ህክምና በጤና አገልግሎት ማዕቀፋቸው በማካተት ትኩረት እንዲሰጡት አሳስበዋል። በዚህ ዝግጅታችን ባለፈው ዓመት ስለዚሁ የጤና ችግር ምንነት እና ሊደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ የሀኪም ማብራሪያ ማቅረባችን ይታወሳል። በዚህ ዓመት ስለዚህ ድምፅ አልባ ገዳይ በሽታ ከዓለም የጤና ድርጅት የተሰጠውን ማብራሪያ መስማታቸውን የነገሩን  አበራ እያዩ የተባሉ አድማጭ፤ እስካሁን መድኃኒት ማግኘት እንዳልቻሉ በመግለፅ ሀኪም እንድንጠይቅላቸው ስለጤና ችግራቸው  ገልፀውልናል።

Der Schriftzug "Hepatitis B" in einem Impfpass
ምስል picture-alliance/dpa/D. Naupold

የአድማጫችንን ጥያቄ መነሻ በማድረግ የሁል ጊዜ ተባባሪያችን የሆኑትን የውስጥ ደዌ ከፍተኛ ሃኪም እና አዲስ አበባ በግል የህክምና አገልግሎት የሚሰጡት ዶክተር ቶሌራ ወልደየስን ጠየቅን። ዶክተር ቶሌራ ስለበሽታው ምንነት እና የምርመራ ሂደት በማብራራት ጀመሩ፤

«ሁፕታይተስ በብዙ ነገሮች ነው የሚከሰተው። ሄፕታይተስ በመርዛማ ነገሮች ሊመጣ ይችላል፤ ለምሳሌ ከሚጠቀሱት ማንኛውም መድኃኒት ሄፕታይተስን ሊያስከትል ይችላል። በተለይ የኤች አይቪ መድኃኒቶች፣ የቲቢ መድኃኒቶች ሄፕታይተስን ያመጣሉ።»

ጠያቂያችን የጤና ችግራቸው ከሄፕታይተስ ቢ ወደ ሲ መሸጋገሩ እንደተነገራቸው ገልጸውልናል። የውስጥ ደዌ ከፍተኛ ሀኪም ዶክተር ቶሌራ ግን ሄፕታይተስ ቢ ወደ ሲ አይለወጥም ነው የሚሉት።

ለሄፕታይተስ ቢ ህክምና ለማግኘት አስቀድሞ የቫይረሱ ወይም የተሐዋሲው መጠን መታወቅ እንዳለበት ያም በዓለም አቀፍ መለኪያ 20 ሺህ ከደረሰ፤ በተጨማሪም የጉበት ኢንዛየም ምርመራ መደረግ እንዳለበት ነው ዶክተር ቶሌራ ያስረዱት። መድኃኒቱን ለማግኘት ቀላል እንዳልሆነም አፅንኦት ሰጥተዋል።

እሳቸው እንደሚሉት ጉበት ከፍተኛ ጉዳት እስኪደርስበት አይጠበቅም ቀደም ሲል በገለፁት መሠረት አስፈላጊው ምርመራ ተካሂዶ መድኃኒቱ ሊሰጥ ግድ ነው። ለምርመራው ከጉበቱ ናሙና ሁሉ ተወስዶ የደረሰበት ደረጃ መታወቅ እንደሚኖርበትም አመልክተዋል።

HEPATITIS C VIRUS
ምስል picture-alliance/BSIP/C. James

ጠያቂያችን የቫይረሱ መጠን ይመስላል  ወደ 3 ሺህ 50 ደርሷል መባላቸውን ገልፀውልናል። ከዚህ ተነስቶ ስለህክምናቸው ምን ማለት ይቻላል? ባለሙያው መድኃኒት ለመጀመር የሚቻልበትን ደረጃ በመጠቆም፤ እሳቸው ግን በመስፈርቱ መሠረት ክትትል ብቻ እንደሚያስፈልጋቸው ነው ያመለከቱት።

የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሰዎች መዳን በሚችል በዚህ በሽታ ሕይወታቸው እንዳይቀጠፍ ክትባት እንዲያገኙ ያስፈልጋል ያሉትን የገንዘብ መጠን ለለጋሾች አቅርበዋል። ክትባቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኝ እና ማንኛውም ሰው ሊከተብ እንደሚችል ዶክተር ቶሌራ ገልጸዋል። አስቀድሞ ግን ሄፕታይተስ ቢ እንዴለበት በምርመራ መረጋገጥ አለበት። የህክምና ባለሙያዎች እንዲከተቡ እንደሚመከር፤ ኤች አይቪ በደማቸው የሚገኝም ተመርምረው መከተብ እንደሚችሉ፤ በመድኃኒት መሸጫውም ክትባቱ መኖሩን ገልጸዋል።

የተከበሩ አድማጭ ከውስጥ ደዌ ከፍተኛ ሀኪሙ ከዶክተር ቶሌራ ወልደየስ ማብራሪያ በቂ መረጃ እንዳገኙ ተስፋ እናደርጋለን። ህክምና ያላገኙበትንም ምክንያት ተረድተዋል ብለን እንገምታለን። የህክምና ክትትል ማድረግዎን ይቀጥሉ። ጤናዎ እንዲመልስም እንመኛለን። ለማብራሪያው ዶክተር ቶሌራን እናመሰግናለን። ሙሉ ቅንብሩን ከድምፅ ዘገባው ያድምጡ፤

ሸዋዬ ለገሠ