1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሄሬሮ እና የናማ ጎሳ ተወካዮች ክስ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 9 2009

የጀርመን ቅኝ ገዢ ጦር እጎአ ከ1904 እስከ 1908 በናሚቢያ ሕዝብ ላይ ለፈፀመዉ  ጭፍጨፋ የጀርመን መንግሥት ለተበዳይ ወገኖች ካሳ እንዲከፍል የሄሬሮ እና የናማ ጎሳ ተወካዮች ባለፈው ታህሳስ መጨረሻ  በኒው ዮርክ ዩኤስ አሜሪካ ክስ መመስረታቸው ይታወሳል። ክሱ የተፈለገውን ውጤት ያስገኝ ይሆን? 

https://p.dw.com/p/2ZRwT
Namibia Frauen des Herero Volkes
ምስል picture-alliance/AP Photo/

የሄሬሮ እና የናማ ጎሳ ተወካዮችን ክስ የማዳመጡ ጉዳይ፣ የረጲ አደጋ፣ ድርቅ

በአሁኗ ናሚቢያ የጀርመን ቅኝ አገዛዝ ካበቃ ከአንድ መቶ ዓመት ከበለጠ ጊዜ በኋላ ሁለት የናሚቢያ ጎሳ ተወላጆች  ጀርመንን በጅምላ ጭፍጨፋ ወንጀል ከሰዋል። የናሚቢያ ተወላጆች በተለይ የሄሬሮ እና ናማ ጎሳዎች በጀርመን ቅኝ ገዢ ጦር እጎአ ከ1904 እስከ 1908 ያኔ የደቡብ ምዕራባዊ አፍሪቃ፣ የአሁኗ ናሚቢያ ውስጥ ለፈፀመው ጭፍጨፋ ካሳ እንዲከፈላቸው በመጠየቅ ከሁለት ወር በፊት ነበር በኒው ዮርክ ክሳቸውን የመሰረቱት። የከሳሽ ጠበቆች የሔሬሮ እና ናማ ጎሳ ባህላዊ መሪዎች ተወካዮች በጋራ ባቀረቡት ክስ አኳያ ችሎት መጀመር አለመጀመር በሚለው ጉዳይ ላይ ባለፈው ሀሙስ ከዳኞች ጋር ቅድመ ውይይት ጉባዔ አካሂደው ለጎርጎሪያዊው ሰኔ 21፣ 2017 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዘዋል።  

የሄሬሮ እና የናማ ጎሳ ተወላጆች ተወካዮች ቬኩሊ ሩኮሮ እና ዴቪድ ፍሬደሪክ በኒው ዮርክ ፍርድ ቤት ርዳታ በጀርመን እና በናሚቢያ መካከል በተጀመረው ድርድር ላይ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች መሳተፍ እንዲችሉ ለማስገደድ ወይም የጀርመን እና የናሚቢያ መንግሥታት፣እንዲሁም፣  የሄሬሮ እና የናም ጎሳ ተጠሪዎች የሶስትትዮሽ ድርድር እና ስምምነት እንዲያደርጉ  ይፈልጋሉ። ጀርመን እና ናሚቢያ የ20ኛው ምዕተ ዓመት የመጀመሪያው የተባለውን የጅምላ ጭፍጨፋን በተመለከተ ካለፈው አንድ ዓመት አንስተው በመደራደር ላይ ይገኛሉ።  በታሪክ ምሁራን ዘገባ መሰረት፣ የጀርመን ቅኝ ገዢ ጦር በ20ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ ላይ በአንፃር ባመጹ የናሚቢያ፣ የሄሬሮ እና ናማ ጎሳ ተወላጆች ላይ ባካሄደው ጭፍጨፋ ከ80 ሺህ የሄሬሮ ጎሳ ተወላጆች መካከል 65 ሺህ፣ ከ20 ሺህ የናማ ጎሳ መካከል ደግሞ 10 ሺህ ገድሏል።  ይሁን እንጂ፣ ሁለቱም መንግሥታት ቀጥተኛ ውይይት ለማካሄድ ፈቃደኛ አልሆኑም።  የከሳሽ ጠበቃ ኬኔት ማካሊየን የሄሬሮ እና የናማ ጎሳዎች ባህላዊ መሪዎች፣ የጭፍጨፋው ሰለባዎች ህጋዊ ተወካዮች በመሆናቸው፣  አብረው መደራደር አለባቸው ሲሉ በኒው ዮርክ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ የጀርመን መንግሥት ካሳ እንዲከፈላቸው ተወካዮቹ ጠይቀዋል፣ ምክንያቱም፣ የጀርመን ቅኝ ገዚ ጦር ወታደሮች ከፈፀሙት አስከፊ ጭፍጨፋ ጎን መሬታቸውን፣ የቀንድ ከብቶቻቸውን እና ንብረታቸውን መነጠቃቸውን ያመለከቱት ማክካሊየን፣ ለዚህ ዓይነቱ ግዙፍ የንብረት ዘረፋ ካሳ የማይከፈልበት አሰራር ዓለም አቀፍ ሕግን እንደሚጥስ አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ፣ ዩኤስ አሜሪካ ውስጥ የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ ብዙዎች በጋራ የሚመሰረቱት ክስ  ለችሎት የሚበቃበት ሂደት ቀላል አይደለም። እጎአ በ2001 ዓም የሄሬሮ ተወካዮች በጀርመን መንግሥት እና በጀርመን ባንክ አንፃር አቅርበውት የነበረው ክስ መክሸፉን ይታወሳል። በደቡብ አፍሪቃ የጆሀንስበርግ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ሕግ ፕሮፌሰር ሚያ ስዋርት አሁን የተጀመረው ጥረት ሊሳካም ላይሳካም ይችላል ባይ ናቸው።
« አንዲት የናይጀሪያ ዜጋ በሀገራቸው ይሰራ የነበረው የብሪታንያውያን እና ኔዘርላንዳውያን የሼል ነዳጅ ኩባንያ በኒጀር ደለል አደረሰው ባሉት የመብት ጥሰት ጥፋት አንፃር ሰባት ዓመት ቀደም ሲል እጎአ በ2006 ዓም የ«ኪዮቤል ጉዳይ» በሚል ስም በዩኤስ አሜሪካ ለመሰረቱት ቡት ክስ  በ2013 ዓም ክስ የአሜሪካውያን ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ስንመለከት፣ የሄሬሮ ተወካዮች ክስ የሚሳካ አይመስለንም። የዩኤስ አሜሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሼል አደረሰው የተባለው ጥፋት በአሜሪካ ምድር ባለመፈፀሙ እና ዩኤስ አሜሪካን የማይመለከት በመሆኑ ከሳሾች ክሳቸውን በዚያ ሊያቀርቡ አይችሉም ሲል ነበር የወሰነው። »
ፍርድ ቤቱ ይህንኑ ውሳኔ የደረሰው፣ ይህንን አሰራር ሲደግፍ የቆየው እጎአ በ1789ዓም የወጣው «ኤልየን ቶርትስ አክት» የተባለው ልዩ የሕግ ሰነድ በወቅቱ እንደማይሰራ በማመልከት ነበር። ብዙ ፍርድ ቤቶች  እና ጠበቆች ሕጉ ከዩኤስ ውጭ የሚታዩ ጥሰቶችን ለመክሰስ ያስችላል በሚል ሲጠቀሙበት ነበር የቆዩት።  
ከ2013 ወዲህ የሕጉ ሰነድ ዩኤስን በተመለከተ ብቻ ነw የተሰራበት። ያም ቢሆን ግን ማክካሊየን ክሱ ሊሳካ ይችላል የሚል ግምት አላቸው። ጠበቃዋ ስዋርት ግን ፍላጎቱ የለም ባይ ናቸው።
« የ«ኤልየን ቶርትስ አክት» አጠቃቀምን በተመለከተ ፍርድ ቤቶች በወቅቱ አሉታዊ አቋም የመያዝ አዝማሚያ ያሳያሉ። ይኸው የውጭ ዜጎች በዩኤስ አሜሪካ ክስ እንዲመሰርቱ ያስችላል የተባለው ልዩ የሕግ ሰነድ ገደብ ሊያርፍበት ይገባል፣ የሕጉ ሰነድ ተቋማትን እንዳይከሰሱ በመፍራት በተለያዩ ሀገራት እንዳይሰሩ ሊያደርጋቸው አይገባም ባዮች ናቸው። ከዚህ ሌላም አሁኑ በዩኤስ አሜሪካ የሚታየው ሁኔታ እንደሚጠቁመው ልዩው የሕግ ሰነድ ያን ያህል ተቀባይነት አላገኘም። »

Deutschland Demonstration in Berlin Genozid deutscher Truppen in Namibia
ምስል Imago/IPON
Namibia  Paramount Chief Vekuii Rukoro
ምስል picture-alliance/dpa/J. Bätz
Namibia Aufstand der Herero in Südwestafrika
ምስል picture-alliance/dpa

የሄሬሮ  እና ናማ ጎሳ ተወካዮች ምናልባት ክስ በመመስረት የመገናኛ ብዙኃን ትኩረትን የብሪታንያውያን እና የአሜሪካውያን መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት አግኝተዋል፣ ይህ እስካሁን ይቅርታ ባልጠየቀው የጀርመን መንግሥት ላይ ግፊት አጠናክሮ፣ የችሎት ሂደት እንዳይጀመር ምናልባት ስለሚሰጋ ከሄሬሮ እና ናማ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ስምምነት ላይ ሊደርስ ይችል ይሆናልየሚል ተስፋ እንዳላቸው አንዷ የሄሬሮ ተጠሪ ኤስተር ምዊንጃንግዌ  ገልጸዋል።

« የጀርመን መንግሥት ምናልባት አንድ ቀን ተነስቶ በአንፃሩ ክስ መመስረቱን እና በጠበቆቹ አማካኝነት እንደሚታገለው ሊናገር ይችል ይሆናል። ወይም በጉዳዩ ላይ ከፍርድ ቤት ውጭ ስምምነት ልንደርስ እንችል ይሆን በሚል ጥያቄ ሊያቀርብ ይችል ይሆናል። ይህም በጭፍጨፋው የተጎዱትን እና ከድርድሩ ተገልለናል ብለው የሚሰማቸውን ማህሀበረሰቦች በድርድሩ ወደማሳተፍ ሊያመራቸው ይችል ይሆናል። ይህ ገሀድ ከሆነ ሂደቶች እንዴት መቀጠል እንደሚኖርባቸው እናውቃለን። »

ዳንየል ፔልስ/አርያም ተክሌ