1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሀረሪ የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የምርጫ ዉጤቱን መቀበሉ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 4 2014

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ዘግይቶ ምርጫ የተካሄደባቸውን ክልሎች የምርጫ ውጤት መግለፁን ተከትሎ በሀረሪ ክልል የሚገኙ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ህዝብ እና መንግስት አሸንፈውበታል ያለውን የምርጫ ውጤት መቀበሉን አስታውቋል፡፡

https://p.dw.com/p/41h1I
Äthiopien Gemeinsamer Rat der politischen Parteien von Harari
ምስል Mesay Teklu/DW

የተመረጠው መንግስት ለውጥ እንዲያመጣ ጠይቀዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ዘግይቶ ምርጫ የተካሄደባቸውን ክልሎች የምርጫ ውጤት መግለፁን ተከትሎ በሀረሪ ክልል የሚገኙ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ህዝብ እና መንግስት አሸንፈውበታል ያለውን የምርጫ ውጤት መቀበሉን አስታውቋል፡፡ ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያቀፈው የጋራ ምክር ቤት በቀጣይ ከአሸናፊው ጋር በጋራ እንደሚሰራ ገልፆ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርቧል።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ መሀመድ ሀሰን በክልሉ በተካሄደው ምርጫ ህዝብ እና መንግስት አሸናፊ መሆናቸውን በመጥቀስ ውጤቱን መቀበሉን አስታወቀዋል ፡፡ ምርጫውን ሙሉ በሙሉ ላሸነፈው የብልፅግና ፓርቲ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት በቀጣይ የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ተሳትፎአቸው እንዲቀጥል ጠይቀዋል። በክልሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አንዱ የሆንው የሀረሪ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት/ሀዲድ ተወካይ አቶ ረምዚ ዓሊ የምርጫውን ውጤት መቀበላቸውን ገልጠው በቀጣይ የህግ የበላይነትን ማስከበር ፈተና በሆነበት ክልል የተመረጠው መንግስት ለውጥ እንዲያመጣ እና ምክር ቤቱ በጥንካሬ አስፈፃሚውን የሚቆጣጠር ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በምርጫው ሂደት ፕሮግራማችንን ለህዝብ አስተዋውቀናል ያለው የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ/ነእፓ ሀረር ቅርንጫፍ ተወካይ አቶ አብዱልአፊዝ አህመድ ፓርቲያቸው በእኩልነት ላይ ተመስርቶ ከአሸናፊውም ሆነ ሌሎች ፓርቲዎች ጋር ይሰራል ብለዋል።

የኢትዪጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ/ኢዜማ ሀረር ተወካይ አቶ አዝማች ጌጡ በበኩላቸው በሀረሪ ክልል አንገብጋቢ ላሏቸው የመጠጥ ውሀ፣ እና የኑሮ ውድነት አሸናፊው ፓርቲ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት የሀረሪ ክልል ምርጫን ብልፅግና ፓርቲ የክልል እና የፌደራል ምክር ቤት መቀመጫዎችን ሙሉ በሙሉ ማሸነፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡

 

መሳይ ተክሉ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ