1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሀምዶክ ስልጣን መልቀቅና የሱዳን ቀውስ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 25 2014

ዶ/ር አስናቀ ከፋለ እንደሚሉት በጎርጎሳውያኑ 2019 የቀድሞ የሱዳን መሪ ኦማር አልበሽርን ተክተው የአገሪቱ የሽግግር መንግስት እንዲመሩ የተሾሙት ሃምዶክ በሱዳን ተፈላጊውን ለውጥ ለማምጣት የቻሉ አይመስልም፡፡ሃምዶክ አሁን ስልጣናቸውን የለቀቁት በሱዳን በቀጠለው የህብረተሰቡ ግፊት ሳይሆን እንዳልቀረ ነው ባለሙያው ያብራሩት፡፡

https://p.dw.com/p/455aL
Sudan Khartoum | Premierminister zurückgetreten | Abdalla Hamdok
ምስል Mahmoud Hjaj/Anadolu Agency/picture alliance

የሀምዶክ ስልጣን መልቀቅና የሱዳን ቀውስ

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ትናንት ስልጣናቸውን መልቀቃቸው ለአገሪቱም ሆነ ለቃጣናው መልካም ዜና ይዞ ሊመጣ እንደማይችል እየተገለጸ ነው። አንድ የፖለቲካ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ለአንድ ዓመት ያህል ከኢትዮጵያ ጋር አታካራ ለመፍጠር ሲንቀሳቀስ የከረመው የኻርቱም ወታደራዊ ክንፍ የሱዳን ሲቪል መሪዎችን ገፍቶ የአገሪቱን ስልጣን የሚቆናጠጥ ከሆነ ወትሮም በስጋት ለተከበበው የአፍሪካ ቀንድ የባሰ ችግር ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በፊናው ስለሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑ አስታውቋል። ሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ የዛሬ 2 ወር ገደማ ነበር በወታደራዊ አመራሮች የመፈንቅለ መንግስት እርምጃ ለቁም እስርም የተዳረጉት፡፡ በኃያላኑ አገራት እና ዓለማቀፍ ማህበረሰብ ውትወታ እንዲሁም የሰላ ማስጠንቀቂያን ያስተናገደ የሱዳን ወታደራዊ ክንፉ ከሁለቱ ሳምንታት እገታ በኋላ አብደላ ሓምዶክን በድርድር ወደ መንበራቸው ቢመልሳቸውም የሱዳናውያኑን ቁጣ ማርገብ ግን ከቶውኑም አልተቻለውም፡፡ ታዲያ በመላው አገሪቱ አገርሽቶ ከቀጠለው የሱዳናውያን ተቃውሞ በኋላ ሃምዶክ ትናንት በቃኝ ብለው ከሃላፊነታቸው መነሳታቸውን አሳውቀዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዶ/ር አስናቀ ከፋለ እንደሚሉት በጎርጎሳውያኑ 2019 የቀድሞ የሱዳን መሪ ኦማር አልበሽርን ተክተው የአገሪቱ የሽግግር መንግስት እንዲመሩ የተሾሙት የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ሃምዶክ በሱዳን ተፈላጊውን ለውጥ ለማምጣት የቻሉ አይመስልም፡፡

Sudan | Proteste nach dem Militärputsch
ምስል Marwan Ali/AP/picture alliance

ሃምዶክ አሁን ስልጣናቸውን የለቀቁት በሱዳን በቀጠለው የህብረተሰቡ ግፊት ሳይሆን እንዳልቀረ ነው ባለሙያው ያብራሩት፡፡ ይህ ደግሞ ሁለት ይሁኝታዎች በሱዳን እንዲከሰቱ በር የሚከፍትም ይሆናል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በፊት በውስጥ የፀጥታ ጉዳይ መያዟን ተከትሎ ሱዳን  ከኢትዮጵያ ጋር በምትወዛገብበት የአልፋሽቃ ለም መሬት ላይ ወታደሮቿን ብታሰፍርም ኢትዮጵያ ለችግሩ ወታደራዊ እልባት ከመስጠት መቆጠቧ ይታወሳል፡፡ የዚህ ውሳኔ ተገቢነት ላይም ዶ/ር አስናቀ ይህን ብለዋል፡፡

Sudan | Massenproteste gegen Militärputsch in Omdourman
ምስል AFP/Getty Images

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከቱርኩ የዜና ወኪል አናዶሉ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ኢትዮጵያንና ሱዳን የድንበር ጉዳዩን በውይይት በመፍታት ሰላማቸውን ያስጠብቃሉ ማለታቸው ይታወሳል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባድር ዲና ሙፍቲ ዛሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ወቅታዊውን የሱዳን ጉዳይ በቅርበት እንደምትከታተልና መፍትሄው በራሳቸው በሱዳናውያን እንዲመጣ ትሻለች ብለዋል፡፡

ስዩም ጌቱ

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ