1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጤናና የአካባቢ ተፈጥሮ በ2016፤

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 18 2009

የወባ በሽታን ማጥፋት እንደሚቻል በጎ ዜና፣ የHIV ተሐዋሲን ስርጭት ዳግም እንዳይስፋፋ ደግሞ ስጋት የተሰማዉ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2016 ነዉ። የዓለም የሙቀት መጠን እንዳይጨምር ርምጃ ለመዉሰድ በፓሪስ የተስማማዉ ዓለም የአየር ንብረት ዉጥን አላምንም የሚሉ ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ 45ኛ ፕሬዝደንት የመሆናቸዉን ዜና ሲሰማ የተደናገጠዉም ኢንዲሁ።

https://p.dw.com/p/2Uvk1
China Impfungen in Shanghai
ምስል picture-alliance/dpa/W. Yadong

AMH Umwelt & Gesundheit (Jahresrückblick2016) CMS - MP3-Stereo

 

በዓለማችን 1,8 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎችን ለሙሉ ለሙሉ ወይም ከፊል ዓይነስዉርነት የዳረገዉን ዓይነማዝ ወይም ትራኮማን ጨምሮ ሌሎች የተዘነጉ ያላቸዉ 17 በሽታዎችን እስከ መጪዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2020 ድረስ ፈፅሞ ለማጥፋት ካልሆነም በቁጥጥር ሥር ለማድረግ ማቀዱን የዓለም የጤና ድርጅት ያሳወቀዉም ከአምስት ቀናት በኋላ አሮጌ በምንለዉ በ2016 ዓ,ም ነዉ። ሳይት ሴቨርስ የተሰኘ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አካሄደዉ የተባለዉ አንድ ቅኝት ኢትዮጵያ ዉስጥ በዓይነ-ማዝ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር በአሳሳቢ ደረጃ እየጨመረ ነዉ ማለቱም አይዘነጋም።

ጥናቱ እንደሚያመለክተዉ ይህ የጤና ችግር ከድህነት ጋር የተቆራኘ ይመስላል። የንፁህ ዉኃ አቅርቦትም ሆነ የንፅህና መጠበቂያ ስልቶች ማለትም መጸዳጃ ቤትና የመሳሰሉትን አብዛኛዉ የዓለማችን ድሀ ወገን የማግኘት ዕድሉ የተወሰነ መሆኑን የተመድ መረጃዎች ያመለክታሉ። እስከ ጎርጎሪዮሳዊዉ 2015ዓ,ም  ድረስ ንፁህ የመጠጥ ዉኃ እና የንፅህና መጠበቂያን ለመላዉ የዓለም ህዝብ የማዳረስ ዕቅድ እንደታሰበዉ ባለመሳካቱ፤ አሁንም 2,4 ቢሊየን ሕዝብ የዚህ ዕድል ተጠቃሚ አልሆነም።

ክትባትን በሰፊዉ የማዳረሱ ርምጃ የሕፃናት ሞትን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለዉ በማሳሰብ አገልግሎቱን ማስፋፋት እንደሚገባ ዩኒሴፍ ያሳሰበዉም በዚሁ ዓመት ነበር። ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ አካባቢዎች አጣዳፊ ተቅማጥ እና ተዉከት በምሕፃሩ አተት በመባል የሚታወቀዉ የጤና ችግር መከሰቱ ተነግሮ ሊወሰዱ የሚገቡ ጥንቃቄዎች በሀገር ዉስጥ መገናኛ ብዙሃን ጭምሪ ሲተላለፉ የነበረበት ዓመትም ነዉ ተሰናባቹ 2016።

Lesotho Mobile Gesundheitsversorgung: Bluttests
ምስል picture-alliance/dpa/D. Kurokawa

HIV AIDS በመላዉ ዓለም በሰዉ ልጆች ላይ ያደረሰዉን ከፍተኛ ጉዳት ለመቀነስ ባለፉት ዓመታት የተጠናከረ ዘመቻ በመካሄዱ ዉጤት መታየቱን በዘርፉ የተሠማሩ ባለሙያዎች ሲናገሩ ተደምጧል። ሆኖም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ቅስቀሳ እና ትምህርቱ  እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ የHIV ስርጭት እንዳይባባስ እያሰጋ መሆኑም በዚሁ ዓመት ተሰምቷል።

በአዎንታዊ መልኩ ከተሰሙ ጤና ነክ ዜናዎች ዋነኛዉ በቀጣይ አራት ዓመታት ዉስጥ የወባ በሽታ ፈፅሞ ሊጠፋባቸዉ የሚችሉ ሃገራት የመኖራቸዉ ብስራት ነዉ። የዓለም የጤና ድርጅት አልጀሪያ፤ ቦትስዋና፣ ኬፕ ቬርዴ፣ ኮሞሮስ፣ ደቡብ አፍሪቃ እና ስዋዚላንድ  እስከ ጎርጎሪዮሳዊዉ 2020ዓ,ም ድረስ ወባን ፈፅመዉ ማጥፋቱ ሊሳካላቸዉ እንደሚችል ተናግሯል። የዚህ ዓመት የዓለም የወባ ቀን ሲታሰብ መሪዉ ቃል የነበረዉ «ወባን ፈጽመን እናጥፋ» የሚለዉ ነዉ። 

የወባ በሽታ ዛሬም ከሰሃራ በስተደቡብ በሚገኙ ሃገራት የሞት መንስኤ ከሚሆኑ የጤና ችግሮች አንዱ ነዉ። በመላዉ ዓለም በወባ ምክንያት ከሚቀጠፈዉ የሰዉ ሕይወት 90 በመቶዉ የአፍሪቃዉን መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት በየጊዜዉ ይፋ ያደርጋል። በሽታዉን የምታስተላልፈዉ የወባ ትንኝ መድኃኒቶችን መላመድ መጀመሯ ችግሩን ዉስብስብ ሊያደርገዉ እንደሚችል እየተነገረ ባለበት በዚህ ወቅት የዶሮ ጠረን የወባ ትንኟን እንደሚያባርር ተሰምቷል።

ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2013ዓ,ም አጋማሽ ጀምሮ በምዕራብ አፍሪቃ ተስፋፍቶ  ከ11ሺህ ሰዎች በላይ የፈጀዉ የኤቦላ  ወረርሽኝ ከሁለት ዓመት ተመንፈቅ በኋላ ስጋትነቱ ማብቃቱ የተነገረዉ በዚሁ በ2016ዓ,ም ነዉ። በመጨረሻዉ ከወረርሽኙ ነፃ የሆነችዉ ላይቤሪያ ናት። የወረርሽኝ ጉዳይ ከተነሳ የዚካ ተሐዋሲ በላቲን አሜሪካን ሃገራት በወረርሽኝ መልክ መከሰቱ በዚህ ዓመት ነበር። በተለይ በብራዚል መስፋፋቱ ሲነገር የነበረዉ የዚካ ተሐዋሲ ለሪዮ ኦሎምፒክም እንቅፋት ሊሆን ተቃርቦ እንደነበር አይዘነጋም። ባለፈዉ ኅዳር ወር ነዉ የዓለም የጤና ድርጅት ዚካ በወረርሽኝነት እንደማያሰጋ ያስታወቀዉ። አፍሪቃ በከፍተኛ የደም ግፊት የሚሰቃዩ በርካቶች ያሉባት ክፍለ ዓለም መሆኗም በዚሁ ዓመት መገባደጃ ላይ ተሰምቷል።

China Hangzhou G20 Klimagipfel - Barack Obama, Xi Jingping, Ban Ki-Moon
ቻይናና ዩናይትድ ስቱትስ የፓሪሱን ስምምነት ሲያጸድቁ ምስል Reuters/H. Hwee Young

ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ አና የደቡብ አፍሪቃ ሃገራት ለከፋ ድርቅ የተጋለጡበት ዓመትም ነበር ተሰናባቹ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2016። ድርቁ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመታት እያሰለሰ, በሚከሰተዉ ኤሊኞ በተሰኘዉ የአየር ጠባይ መለዋወጥ ምክንያት መባባሱ ነዉ የሚነገረዉ።

በጎሪጎዮሳዊዉ 2015ዓ,ም ኅዳር መጨረሻ ፓሪስ ላይ ከተካሄደዉ የተመድ የአየር ንብረት ለዉጥ ተከታታይ ጉባኤ የተገኘዉ አዎንታዊ ስምምነት በ2016ዓ,ም በአብዛኞቹ የመንግሥታቱ አባል ሃገራት ተቀባይነት እያገኘ ተፈርሟል። ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታት እንደተካሄዱት የአየር ንብረት ለዉጥ ተመልካች ጉባኤዎች ብዙም ባይወራላቸዉም ስምምነቱን ወደተግባር ለመለወጥ የሚያስችሉ መግባባቶች የታዩባቸዉ ጉባኤዎች በዚህ ዓመትም ተካሂደዋል።

ከባቢ አየርን በስዉር የሚበክሉ አዉቶሞቢሎችን ለገበያ በማቅረብ ከፍተኛ ካሳ ለመክፈል የተገደደዉ የአንጋፋዉ የአዉቶሞቢል ፋብሪካ ፎልክስ ቫገን ባለቤት የሆነችዉ ጀርመን  በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን በብዛት ለመጠቀም እንቅስቃሴዋን በይፋ መጀመሯንም በዚህ ዓመት ነዉ ያሳወቀችዉ።  በዚሁ በ2016ዓ,ም መስከረም ላይ ነበር በርካታ ሃገራት ፓሪስ ላይ የተደረሰዉን ስምምነት መቀበላቸዉን በፊርማቸዉ ያረጋገጡት።  የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ እና የቻይናዉ ሺ ዢንፒንግ የቡድን 20 ሃገራት ስብሰባ ከመካሄዱ አስቀድመዉ ነበር፤ ስምምነቱን ማጽደቃቸዉን ያሳወቁት። ብዙም ሳይቆይ ማራካሽ ሞሮኮ ላይ ዓመታዊዉ የአየር ንብረት ተመልካች ጉባኤ እየተካሄደ የአየር ንብረት ለዉጥ መኖሩን አላምንም የሚሉት ቢሊየነር ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካኑ ምርጫ አሸንፈዉ ፕሬዝደንት የመሆናቸዉ ዜና ሲሰማ በተስፋ መንቀሳቀስ የጀመረዉን ስብስብ አደናገጠ። በዚህም ምክንያት ይመስላል የማራካሹ የአየር ንብረት ለዉጥ ተከታታይ ጉባኤ የበፊቶቹን ያህል ትኩረት አላገኘም ነበር።  በዚሁ ዓመት ለአካባቢ ተፈጥሮ በምታደርገዉ ጥንቃቄ በዚህ ዓመት የተዘጋጀዉን የካርቦን ንግድ ጉባኤ ሩዋንዳ አስተናግዳለች።

UN Klimakonferenz COP22 in Marokko
የማራካሹ ጉባኤምስል Imago/Xinhua

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ