1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ቤተልሔም ደሴ

ዓርብ፣ ጥር 10 2011

ቤተልሔም ደሴ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ሴቶች ልጆች የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆኑ ፈጣሪም መሆን እንደሚችሉ በአርዓያነት የምትጠቀስ ናት። ስኬታማ መሆን የጀመረችው ገና በአዳጊነት ዕድሜዋ ነው።

https://p.dw.com/p/3BlMl
Coding Expertin Betelhem Dessie
ምስል B. Dessie

የኮዲንግ ባለሙያ ቤተልሔም ደሴ

የ 19 ዓመቷ ቤተልሔም ደሴ በኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ተሰጥዎኦዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ዝናን ያተረፈች ወጣት ናት። ሐረር ከተማ ተወልዳ ያደገችው ቤተልሔም ስኬታማ መሆን የጀመረችው ገና በአዳጊነት ዕድሜዋ ነው። « አባቴ ኮምፒውተር እና ኤሌክትሮኒክስ የሚሸጥበት ሱቅ ነበረው። 9 ዓመቴ ላይ ልደቴን ማክበር ፈልጌ ብር ጠየኩት እሱ ግን ብሩን አልሰጥሽም አለኝ። ከዛ እኔ ራሴ ሰርቼ ያገኘሁትን ብር በሙሉ ለልደቴ አውለዋለሁ በሚለው ተስማማን። ከዛ ወደ 1600 ብር ሰራሁ። ያኔም ይህንን ስራዬን የሚያስተዋውቅልኝ ድረ ገፅ መስራት ፈለኩ።»
እንደ አሁኑ ኮምፒውተር እና ኢንተርኔት ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም ባልተስፋፋበት ሰዓት ራሷን እያስተማረች ድረ ገፅ መስራት የጀመረችው ቤተልሔም በአሁኑ ሰዓት በሮቦት አርቴፊሻል እውቀት ላይ ተመርኩዞ የሚሰራው iCog Laps ድርጅት የፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ እና የSOLVE IT ፕሮጀክት አማካሪ ሆና ትሰራለች። ይህም ፕሮጀክት ለማህበረሰቡ ችግሮች በቴክኖሎጂ የታገዘ መፍትሄ ያፈላልጋል። ከዚህም በተጨማሪ ቤተልሔም በግል እና ከሌሎች መስሪያ ቤቶች ጋር በትብብር የሰራቻቸው የሶፍት ዌር ፕሮግራሞች ባለቤት ናት። 
ቤተልሔም በተለይ የኢትዮጵያን ማህበረሰብ ህይወት ሊያሻሽሉ የሚችሉ ፕሮጀክቶች ላይ አተኩራ ሰርታለች። ወደ ውጪ ሀገር ሄዳ፣ ጥሩ ክፍያ ተከፍሏት ከመስራት ይልቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆና ለሌሎች ምሳሌ መሆኑን ትመርጣለች። ስለሆነም ሌሎች በእሷ እድሜ ያሉ ወጣቶች የኮምፒውተር ቋንቋዎችን ተጠቅመው ኮምፒውተሮች እንዲታዘዙ ማድረግ የሚያስችላቸውን የኮዲንግ ዕውቀት እንዲጨብጡ ታስተምራለች። አሁንም ድረስ ወንዶች በሚያመዝኑበት የሙያ ዘርፍ ላይ ነው የምትሰራው ቤተልሔም ሌሎች አዳጊ ሴት ወጣቶችን የምታበረታታው ምን እያለች ይሆን?
« ብዙ ጊዜ ያለው ችግር አርዓያ የሚሆን ሰው ማጣት ነው። እኔም ሳድግ ሴቶች ሰርተው በቴክኖሎጂ ላይ ሰርተው እንደዚህ አይነት ውጤት አመጡ የሚል ነገር ሰምቼ አላውቅም። ስለዚህ እንደዚህ መሆን ይቻላል የሚለውን ለማሳየት ነው። 
ቤተልሔም አባቷን ከአርዓያ ይልቅ ደጋፊዬ ነበር ስትል ትገልፃቸዋለች። ይህም እሷ ኮድ ማድረግ በጀመረችበት ጊዜ ብዙም በአካል ተገኝቶ ሊያስተምራት የሚችል ሰው ባለመኖሩ ነው። ቤተልሔም ከልጅነቷ ጀምሮ በነበራት ተሰጥዎ ላይ ስትሰራ፣ «ችሎታዋን የሚያደንቁ ወይም የሚያበረታቱ ብቻ ሳይሆን የሚያጣጥሉም ገጥመዋታል። ገጠመኟንም ወጣቷ በድረ ገጿ ላይ ፅፋለች። 
ቤተልሔም እነዚህ ገጠመኞቿ ለሀገሯ ያሏትን ህልሞች ለማሳካት እንደውም ጥንካሬ እንደሆኗት ትናገራለች። ወጣቷ በዚህ አዲስ በተጀመረው የጎርጎሮሳዊው 2019 ዓ.ም. በርካታ አስደሳች ፕሮጀክቶች ያለቻቸውን አቅዳለች። « በተለይ በሴቶች እና ቴክኖሎጂዎችን በት/ቤት በማስተዋወቅ ላይ በርትቼ እሰራለሁ።  የ SOLVE IT ፕሮጀክት ላይ ደግሞ እንዴት ነው የስራ ፈጠራ ያላቸውን ሰዎች አሰልጥነን ወደ ትክክለኛ  ቢዝነዝ የምናስገባው ወይም የምናመቻቸው የሚለው ላይ መስራት አቅጃለሁ።» ትላለች ያላትን የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ እውቀት ተጠቅማ ለሌሎችም እያካፈለች ኢትዮጵያ ውስጥ በመስራት ላይ የምትገኘው ቤተልሔም ደሴ። 

DW Shift - Netzwerker Karlie Kloss
ምስል DW
Coding Expertin Betelhem Dessie
ምስል B. Dessie

ልደት አበበ 
ተስፋለም ወልደየስ