1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ዘርፈ ብዙ ችግሮች የቀፈደዱት የሥጋ ኢንዱስትሪ

ረቡዕ፣ መስከረም 23 2011

የኢትዮጵያ የሥጋ ኢንዱስትሪ የገጠሙትን ችግሮች ለመቅረፍ ወደ ውጪ የምትልካቸውን የቁም እንስሳት ማቆም እንደሚገባት የኢትዮጵያ ስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የሰራው ጥናት ጠቁሟል። ጥናቱ በሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት ውይይት ይደረግበታል።

https://p.dw.com/p/35vim
Schlachthaus Fleischerei Metzger
ምስል Fotolia/industrieblick

ዘርፈ ብዙ ችግሮች የቀፈደዱት የስጋ ኢንዱስትሪ

የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች ጠፍረው የያዟቸውን ችግሮች አጥንቶ የቁም እንስሳት ወደ ውጪ አገራት ባይላኩ ከሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል። የማዕከሉ ጥናት በዋንኛነት ሥጋ አቀነባብረው ወደ ውጪ የሚልኩ ኩባንያዎች የገጠሟቸው ችግሮችን በመለየት ላይ ያተኮረ ሲሆን ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት እና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት ይደረግበታል። የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የገበያ ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ጋሹ እንደሚሉት ጥናቱ ሁሉንም የቁም እንስሳት ንግድ በአንድ ጊዜ ይቁም የሚል ጥቆማ አላቀረበም። 

"ጥናቱ የሚለው በአገር ውስጥ የማረድ አቅም በተፈጠረባቸው በሒደት ተራ በተራ እንደምናስቆም ነው። ሁሉንም በአንድ አይደለም። በአንድ ጊዜ የምናስቆማቸው ለምሳሌ በግ እና ፍየል ባለድርሻዎች ሁሉ ተወያይተው ብንቆም ይሻላል የሚል ስምምነት ላይ ብንደርስ ራሱ በግ እና ፍየልን በቁም ወደ ውጪ መላክ የሚያዋጣበት ጊዜ ደግሞ አለ። ለምሳሌ በረመዳን እና በአረፋ በዓላት ወቅት የቁም እንስሳት በጣም በሰፊው ነው የሚፈለገው። በዚያን ወቅት በልዩ ሁኔታ መፈቀድ እንደሚችል ሁሉ ሐሳብ ያቀረበ ጥናት ነው እኛ ጋር ያለው"
በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎችም ሆኑ ሥራውን ቀረብ ብለው ያጠኑ ባለሙያዎች እንደሚሉት የኢትዮጵያ የሥጋ ኢንዱስትሪ ባለፉት አመታት የአዳዲስ ባለወረቶችን ቀልብ መግዛት ቢችልም ዕድገቱ እና አገሪቱ ያገኘችው ገቢ ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ለውጭ ገበያ የሚሆን ስጋ የሚዘጋጅባቸው ቄራዎች ቁጥር ባለፉት አምስት አመታት ገደማ ከነበረበት በእጥፍ ማደጉን የሚናገሩት አቶ አበባው መኮንን የዘርፉ ዕድገት ዘገምተኛ መሆኑን ከታዘቡ መካከል አንዱ ናቸው። ሶስት የውጭ ኩባንያዎችን ጨምሮ 12 አባላት ያሉትን የኢትዮጵያ ስጋ አቀነባባሪዎች እና ላኪዎች ማኅበር በጸሐፊነት የሚያገለግሉት አቶ አበባው ዕድገቱ አዎንታዊ መልክ እንዳለው ያስረዳሉ። 

"በ2009 ዓ.ም. ወደ 19 ሺሕ 779 ሜትሪክ ቶን ስጋ ነው ወደ ውጪ የተላከው። በገቢም ወደ 100.2 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል። በ2010 ወደ 20 ሺሕ 550 ቶን ስጋ የተላከ ሲሆን ወደ 103 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል። በመጠንም በገቢም ዕድገት አለው። ዕድገቱ ግን ከኢንቨስትመንቱ አንፃር ሲታይ በጣም ዘገምተኛ ነው። ምክንያቱም ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ ከፍተኛ የሆነ ኢንቨስትመንት ነው ወደ ዘርፉ የገባው። ከአምስት ከስድት አመታት በፊት የነበሩ ኤክስፖርት ቄራዎች ቁጥራቸው ከስድስት የዘለለ አይደለም። አሁን በዕጥፍ አድጓል ማለት ያቻላል። የኤክስፖርት አፈፃጸሙ በዚያ ደረጃ እድገት አላመጣም። ግን ዕድገቱን በጠቅላላ ስንወስደው አዎንታዊ መልክ አለው"
በማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሠረት ከ53 ሚሊዮን በላይ የቀንድ ከብት፣ ከ25 ሚሊዮን በላይ በጎች እና ከ22 ሚሊዮን በላይ ፍየሎች ያላት ኢትዮጵያ ተስፋ የጣለችበት የስጋ ገበያ ለምን ስኬታማ መሆን ተሳነው? ወደ ውጪ አገራት የሚላከው የቁም እንስሳት እና የስጋ ምርት አንዳቸው በሌላቸው ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩትስ እንዴት ነው? አቶ መኮንን እንደሚሉት ከኢትዮጵያ ወደ ውጪ ከሚላከው በግ አገሪቱ ለውጪ አገራት ከምታቀርበው የበግ ስጋ ይልቃል። 
"የበግ ስጋ ኤክስፖርታችን በጣም አነስተኛ ነው። በቁም ወደ ውጪ የሚላከው የበግ ንግድ ደግሞ በጣም ከፍተኛ ነው። ወደ ውጪ የሚላከው የበግ ስጋ አነስተኛ የሆነበት ምክንያት የቁም በግ ከእኛ ስለሚያገኙ ፤ ትኩስ ስጋ የማግኘት ዕድላቸው ሰፊ ስለሚሆን እና ሐይማኖታዊ ነገሮችም ሊኖሩ ስለሚችሉ አንዱ ምክንያት ይኸ ሊሆን ይችላል የሚል ዕሳቤ አለ። በአገር ውስጥ የማረድ አቅም በፈጠርንባቸው ላይ የቁም እንስሳት ወደ ውጪ መላክ ማቆም ብንችል ጥቅም ይኖረዋል። የቁም እንስሳት ንግድ ላይ ስራ ሊፈጠርለት የሚችለው ውስን ሰው ነው። በስጋ ኤክስፖርት ግን ቄራ ውስጥ የሚገኙ ሰራተኞች በጣም ብዙ ናቸው። ስራ አጥ ወጣቶች እንስሳቱን ተደራጅተው ወደ ቄራ ሊያመጡ ይችላሉ። ከዚያም በላይ ግን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ እንሸጋገራለን እያልን እንስሳትን በቁም መላክ ማለት ብዙ ሐብትን አሳልፎ እንደመስጠት ነው የሚቆጠረው"
አቶ መኮንን ጋሹ የኤክስፖርት ስጋ የሚያዘጋጁት ቄራዎች "አመታዊ የማምረት አቅማቸው በጣም ዝቅ ያለ ነው" ሲሉ ይናገራሉ። በኃላፊው ማብራሪያ መሰረት "የዕርድ እንስሳት ለኤክስፖርት ቄራዎች በሚፈለገው መጠን፤ በሚፈለገው ጥራት በሚፈለገው ዋጋ እና በሚፈለገው ጊዜ ውስጥ አለመቅረባቸው" ዋንኛ ችግር ነው። በዚሁ ምክንያት የውጭ ንግዱ ተጎድቷል። አቶ መኮንን እንደሚሉት የኢትዮጵያ የእንስሳት ሐብት ቁጥር ከፍተኛ ነው ይባል እንጂ  የአረባብ እና ግብይት ሥርዓቱ ዛሬም ድረስ ኋላ ቀር ነው። በግ፣ በሬ እና ፍየል የመሳሰሉ እንስሳት ስጋን ወደ ውጪ አገራት የሚልኩ ኩባንያዎች ዛሬም ኑሮውን ለመደገፍ ከእርሻ ሥራው ጎን ለጎን የቤት እንስሳት ከሚያረባው ገበሬ እና ድርቅ ከሚፈትነው አርብቶ አደር ትከሻ አልወረዱም። አቶ አበባው መኮንን አመቱን ሙሉ ለዕርድ የሚሆኑ እንስሳት ቋሚ በሆነ መንገድ ማግኘት በዘርፉ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ፈተና መሆኑን ያስረዳሉ።
"እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለንግድ የተቋቋሙ ዘመናዊ የእንስሳት እርባታዎች የሉም። ስጋን ወደ ውጪ የምንልከው ካርብቶ አደሩ አካባቢ በነጋዴ እና በኤክስፖርትራ ቄራዎች ከገበበያ ላይ እየሰበሰብን ነው እንጂ ወደ ዘመናዊ የእንስሳት እርባታ የገባ ባለሐብት የለም። ትልቁ ማነቆ ነው ብለን የገመገምንው አንደኛ ቋሚ እና ወጥ የሆነ የእንስሳት አቅርቦት የለም"
የዘመናዊ እንስሳት እርባታ አለመኖር ፈተና ግን በአቅርቦት ብቻ የተወሰነ አይደለም። በዓለም አቀፍ የስጋ ግብይት እንስሳቱ የመጡበትን አካባቢ መለየት አንደኛው መስፈርት መሆኑን የሚያስረዱት አቶ መኮንን ኢትዮጵያ ይኸን መመለስ የምትችልበት የእርባታ ዘዴ አለመዘርጋቷን ይገልፃሉ። 
 ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ እና ሱዳንን ጨምሮ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ከኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ይገዛሉ። የኢትዮጵያ የስጋ ደንበኞች አብዛኞቹ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ናቸው። ሳዑዲ አረቢያ እና ዩናይትድ አረብ ኤሚሬት ቀዳሚውን ደረጃ ይይዛሉ። አቶ አበባው የኢትዮጵያ የስጋ ኢንዱስትሪ በተበተቡት ችግሮች ምክንያት በእነዚሁ አገሮች ብቻ ተወስኗል።
"በእንስሳት ሐብት ከአፍሪቃ አንደኛ ነን። ከዓለም ዘጠነኛ ወይም አስረኛ ላይ ነው የምንቀመጠው። ግን ይኸ ያለን የእንስሳት ሐብት ገበያው የሚፈልገውን የጥራት ደረጃ የጤና መስፈርቶችን ከማሟላት አንፃር ከፍተኛ ክፍተቶች አሉ። ለዚያም ነው አብዛኛው ወደ ውጪ የሚላከው የስጋም የቁም እንስሳትም መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ላይ ተንጠልጥሎ ያለው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የገዢ አገራትን የጥራት ደረጃ ከማሟላት አንፃር የሚሰሩ ስራዎች ቢኖሩም ተወዳዳሪ ሆኖ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የሚቻልበት አግባብ ላይ አይደለም አሁን ያለንው። 

Australien wildes Schaf 40 Kg Wolle
ምስል Reuters/RSPCA
Äthiopien Market in Mekele
ምስል DW/Y. G. Egziabher

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የስጋ ፍጆታ ያላቸውን አገሮች ገበያ ለመድፈር ፈፅሞ ዝግጁ አትመስልም። አቶ መኮንን ኢትዮጵያ ወደ አውሮጳ እና አሜሪካ ገበያዎች ስጋ መላክን ከፈለገች በርካታ መስፈርቶች ማሟላት እንደሚጠበቅባት ይናገራሉ። 

እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ