1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓይነስውርነት ያልገታው ጥረትና ስኬት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 12 2015

በጎርጎሪዮስ የዘመን ቀመር መጋቢት ወር የሴቶች ታሪክ የሚወሳበት እንደመሆኑ የጤና እና አካባቢ መሰናዶ ዓይነስውርነት ካለመችው ስኬት ያላስቀራትን የኮሌጅ መምህርት ያስተዋውቀናል።

https://p.dw.com/p/4P0ip
World Braille Day
ምስል Sumit Sanyal/picture alliance

ዓይነስውርነት ያልገታው ጥረትና ስኬት

ስለሴቶች ሲነሳ የሚደርስባቸው ጥቃት፣ የማኅበረብ ተጽዕኖ፣ ጉዳት እና ስሱነታቸው አዘውትሮ ይወሳል። አሉታዊው ገጠመኝ በመጉላቱ የተለያዩ ተግዳሮቶችን አልፈው ከስኬት ማማ በጥረታቸው የዘለቁትን ሸፍኗል። የአካል ጉዳተኛ መሆን አለመቻል እንዳልሆነ በጥረቷ ያረጋገጠችው የዕለቱ እንግዳችን መምህርት ለወየሁም በዚህ መልኩ ከተሸፈኑት አንዷ ናት። ተስፋ መቁረጥ ካሰቡበት አያደርስም  የምትለው ለወየሁ አየለ፤ በደብረብርሃን ትምህርት ኮሌጅ የአማርኛ ትምህርት ክፍል መምህርት እንዲሁም የሰሜን ሸዋ ዓይነስውራን መምህራን እና ተማሪዎች የሙያ ማሻሻያ እና መደጋገፍ ማሕበር ምክትል ሊቀመንበር ናት።  

ምሥራቅ ጎጃም ደብረ ወርቅ በምትባለው አካባቢ የተወለደችው የዛሬዋ የኮሌጅ መምህርት ለወየሁ አየለ፤ ገና በለጋ ዕድሜዋ ነው በፈንጣጣ ምክንያት የዓይን ብርሃኗን ያጣችው። አንዳንድ መጥፎ የምንለው አጋጣሚ ውሎ አድሮ የመልካም ዕድል በር መክፈቻ የሚሆንበት ጊዜ አለና፤ ትንሿ ለወየሁ ከምትኖርበት የገጠር አካባቢ ቤተሰቦቿ ለህክምና ብለው የወሰዷት ስፍራ ለዛሬ የሕይወት ስኬቷ መንገድ ፈጠረ። በዚሁ በሰበታ መርሀዕውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ያደገችው መምህርት ለወየሁ፤ በትምህርት  መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ከዚያም ወደ ሁለተኛ ደረጃ እስክትደርስ ድረስ ከመሰሎቿ ጋር ነበርና የተማረችው፤ እጅግም ልዩነቱ ሳይሰማት እና ሳይከብዳት መቆየቷን ታስታውሳለች።

እንዲህ እየቦረቀች ያደገችበት የዓይነስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ከገጠር ለወጣችው አዳጊ ቤተመንግሥት ከማደግ እኩል ነበር ትለዋለች። ይኽ የልጅነት የደስታ ጊዜ ግን ከዓይናማዎቹ እኩዮቿ ጋር በተማረችበት አጋጣሚ አልዘለቀም። እንድትጠነክር ግን አድርጓታል። እንደውም እሷ እንደምትለው ዓይነስውርነቱ በሌላው የሕይወት ጎን ካሳደረባት ጫና በቀር ለዛሬ ማንነቷ መንገድ በመጥረጉ ረገድ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል።

Angola Malanje Braille-Schreibmaschine
ዓይነስውራን የሚጠቀሙበት የብሬል መጻፊያ ምስል Nelson Camuto/DW

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ስታጠናቅቅ ያኔ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከሚፈተነው እጅግ ጥቂቱ ነበርና ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገባው በመጀመሪያው ፈተና እሷም አልተሳካላትም ነበር። ተስፋ ቆርጣ ግን አልተወችውም፤ ደጋግማ በመፈተን ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባትን ነጥብ ይዛ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ግቢ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ስነጽሑፍ የትምህርት ዘርፍ ለአስተማሪነት የሚሰጡ ትምህርቶችን ተምራ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በ1989 ዓም አገኘች። ከተመረቀች በኋላ ለማስተማር የደረሳት ዕጣ ወደ ትልውድ አካባቢዋ ነው የመለሳት። ከዚያም ወደ አስር ዓመት ገደማ በማስተማር ሥራ ቆየች። ማስተማርን እንደምትወደው የምትናገረው መምህርት ለወየሁ የሁለተኛ ደረጃ እና የመሰናዶ ተማሪዎች ጋር መልካም የመማር ማስተማር ጊዜ እንዳሳለፈች ነው ያጫወተችኝ። ዛሬም እነዚያን ተማሪዎቿን በአድናቆት ታነሳለች። ጥረት ጉብዝናቸው እኔንም በትጋት እንድዘጋጅ ያደርገኝ ነበር ነው የምትለው።

መምህርቷ ከትምህርት ዓለም መራቅን አልፈለገችም፤ መንፈሷ ዳግም ወደ ዩኒቨርሲቲ ተመለሽ አላት። እናም አደረገችው። በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ዓይነስውራንን ሊያግዝ የሚችል ቴክኒዎሎጂ እንደዛሬ ባለመኖሩ በጎ ፈቃደኛ ተማሪዎች ያደርጉላቸው የነበረውን ትብብር አትዘነጋውም።  

የበጎ ፈቃድ አንባቢዎቹ ለዓይነስውራኑ ዘርፈ ብዙ ትብብር ነው የሚያደርጉት፤ ማንበብ፤ የሚዘጋጁ የጽሑፍ የቤት ሥራዎችን ማዘጋጀት፤ በፈተና ጊዜ ደግሞ ፈታኝ ሆኖ መቅረብ። በማስተማር ሥራዋ ላይ ደግሞ ጥያቄ ማውጣት እንዲሁም ማረም የዓይናሞችን በጎ ፈቃደኝነት ትብብር ያሻት ነበር። ያ ዛሬ በቴክኒዎሎጂ መፍትሄ አግኝቷል ነው የምትለው ጠንካራዋ መምህርት። ቴክኒዎሎጂውን በተመለከተ ደግሞ፤ «የአሁን ልጆች በጣም ዕድለኞች ናቸው። እኔ አሁን ቢሆን ኖሮ ለዲግሪዬ የተማርኩት እንዴት ታድዬ ነበር እላለሁ። ለምን? ጻፉልኝ፤ አንብቡልኝ ብዬ በካሴት አስቀርጬ፤ ያ ሁሉ ቀርቶ እራሴ ከኢንተርኔት ላይ አውርጄ፤ እራሴው በደንብ አድርጌ አንብቤ እራሴ እዛው ላይ ተርጉሜ፤ እራሴ አስተካክዬ ወረቀቴን እሠራ ነበር።» ነው የምትለው።  

World Braille Day
ዓለምን በጣቶች ማንበብ ለዓይነስውራን የተሰጠው ፀጋምስል picture alliance/dpa/RIA Nowosti

አሁን መምህርት ለወየሁ ከራሷ አልፋ ለሌሎችም የትብብር እጇን ለመዘርጋት በቅታለች። የአካል ጉዳት አለመቻል ማለት እንዳልሆነ ሕያው ማሳያ የሆነችው መምህርት የሕይወት ተሞክሮዋን ተንተርሳ ለሌሎች መልእክት አላት። «ዋናው ተስፋ ያስፈልገናል፤ አንድ ቦታ ለመድረስ ተስፍ ማድረግ ያስፈልጋል። ተስፋ ከተቆረጠ ማንኛውን ነገር ቢሟላም ከንቱ ነው የሚሆነው። መጀመሪያ ተስፋ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሴቶች፣ ዓይነስውሮች በሚማሩበት ጊዜ ሊደርሱበት ያሰቡትን አላማ አጥብቀው ሊጓዙ ይገባል።»

መጋቢት ወር የሴቶች ታሪክ የሚነገርበት ወር እንደመሆኑ የአካል ጉዳተኛ መሆን አለመቻል እንዳልሆነ በጥረቷ ያረጋገጠችው የየኮሌጅ መምህርት ለወየሁ አየለን የሴቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታሰበብበት ወር ለጽናት ማሳያ እንድትሆን ወደእናንተ አቀረብናት።

 ሸዋዬ ለገሠ