1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለም አቀፍ የዘርፈ ብዙ ድህነት መለኪያ ጥናት

ዓርብ፣ መስከረም 11 2011

ሕንድ ባለፈዉ 10 ዓመት ፈጣን መሻሻል አሳይታለች ሲል ዓለም አቀፍ የዘርፈ ብዙ ድህነት መለኪያ ጥናት (MPI) ገለፀ። ድርጅቱ ይፋ ባደረገዉ መረጃ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍራቃ ሃገራት የሚታየዉ ድህነት ግን ከፍተኛ ስጋት ፈጥል ብሏል። በዓለም ዙርያ ከሚገኙ በድህነት ከሚማቅቁ ሰዎች መካከል ግማሹ ሕጻናት መሆናቸዉን አስታዉቋል።

https://p.dw.com/p/35Jl6
Kenia Kind sammelt Müll in einem Slum in Nairobi
ምስል picture-alliance/AP Images/B. Curtis

በናይጀርያ 97 ፤ በኢትዮጵያ 86 ፤ ሚሊዮን ሕዝብ ደሃ ነዉ

 

በጎርጎረሳዉያኑ  2010 በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) እና በኦክስፎርድ የድህነት እና የሰብአዊ ልማት ፕሮጀክት(OPHI) የወጣዉ ለሰዉ ልጆች መሰረታዊ ነገሮች ማለትም ጤና ፤ ትምህርት እና  የኑሮ ደረጃን የዳሰሰ የድህነት መዘርዝርን ይፋ አድርጎአል። መዘርዝሩ  መሰረት በዓለም 105 ሃገር ነዋሪዎች የጤና  የትምህርት እና  የኑሮ ደረጃን ተከታትሎ በወጣዉ መረጃ መሰረት፤ በሃገራቱ ውስጥ ከአራት ሰዎች አንዱ ወይም በአጠቃላይ 1.3 ቢሊዮን የሚሆነዉ ሰዉ በዓለም አቀፍ የድህነት መረጃ መዝርዝር  ልኬቶች ደሃ ነዉ።

ምንም እንኳ ሕንድ ዉስጥ ከፍተኛ ድህነት ዉስጥ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር አሁንም ከፍተኛ ቢሆንም ቅሉ በድህነት ቅነሳ መዘርዝር ከፍተኛ ዉጤትን ያሳየች ሕንድ መሆንዋ ግን ተጠቅሶአል። ሕንድ  በጎርጎረሳዉያኑ 2005/06  እና   በጎርጎረሳዉያኑ 2015/16 በሃገሪቱ የሚታየዉን የድህነት መጠን ከ 55% ወደ 28% ቀንሷል ። እንደመዘርዝሩ በሕንድ ድህነት በግማሽ መቀነሱን ያሳያል።  የኦክስፎርድ የድህነት እና የሰብአዊ ልማት ፕሮጀክት ዳይሬክተር ሳቢና አልከሪ እንደገለፁት ይህ የሕንድ ዉጤት በድህነት ቅነሳ ታሪካዊ ነዉ። 

«ድህነትን በተመለከተ ለበርካታ አስር ዓመታት በሕንድ ምንም አይነት መረጃ አልነበረም። ከጎርጎረሳዉያኑ 2005 እና 06 ጀምሮ ግን አስደሳችና አስገራሚ ለዉጦችን ማየት ጀምረናል» 

የኦክስፎርድ የድህነት እና የሰብአዊ ልማት ፕሮጀክት ዳይሬክተር ሳቢና አልከሪ  271 ሚሊዮን ሕዝብ ከድህነት ቀንበር መላቀቁንም ተናግረዋል።  

«ምንም እንኳ በሕንድ የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ቢጨምርም በድህነት ይኖር ከነበረዉ  635 ሚሊዮን ሕዝብ ቁጥሩ ወደ 364 ሚሊዮን ዝቅ ብሎአል። ያ ማለት በሕንድ  271 ሚሊዮን ሕዝብ ከድህነት አራንቋ ተላቋል። ይህ ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነዉ»

Sabina Alkire, Leiterin der "Oxford Poverty and Human Development Initiative (OPHI)"
ሳቢና አልከሪ ምስል Oxford Poverty and Human Development Initiative

ዓለም አቀፍ የዘርፈ ብዙ ድህነት መለኪያ ጥናት መሰረት በዓለም ዙርያ ዕድሜያቸው ከ 18 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ገሚሱ በድህነት ይኖራሉ።  በዓለማችን ከሦስት አንዱ ሕጻን ማለትም 668 ሚሊዮን ሕጻናት በድህነት ኑሮአቸዉን እየገፉ ነዉ።  ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪቃ ሃገራት ዉስጥ ከሚገኙ ሕጻናት መካከል ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት ህጻናት በተለያዩ ዘርፎች  ድህነት ዉስጥ ይገኛሉ። ከነዚህ መካከል 90 % የሚሆኑት ሕጻናት በደቡብ ሱዳን እና በኒጀር እንደሚገኙ ዓለም አቀፍ የዘርፈ ብዙ ድህነት መለኪያ ጥናት አመልክቶአል።

ድህነት በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሃገራት ዉስጥ የተለያዩ ቅርፆች ቢኖሩም አብዛኛው የዓለማችን  ሕዝብ በጣም ድሃ በሆኑት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ እንደሚገኙ  በስቃይ ላይም እንደሚገኙ ጥናቱ ይጠቁማል። በናይጀርያ  97 ሚሉዮን ሕዝብ በኢትዮጵያ ደግሞ 86 ሚሊየን ሕዝብ በድህነት እንዳለ ጥናቱ ያመለክታል። የሕጻናት እንክብካቤ የሚሰጠዉ «Save the Children» የተሰኘዉ ድርጅት የሕንድ ቅርንጫፍ ዋና ተጠሪ ቢዲሻ ፒላ ለ«DW» እንደገለፁት ድሕነትን በመቅረፍ ረገድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሌላ አህጉር ይልቅ በአፍሪቃ ትልቅ ሚናን ይጫወታሉ። 

Infografik Indikatoren der Armut EN

« እዝያ የልማት ማስፋፋቱ እቅድ ለየት ያለ ነዉ። በአፍሪቃ የሲቢሉ ማኅበረሰብ በአገልግሎት አቅርቦት እጅግ ግዙፍና ትርጉም ያለዉ ትልቅ ሚናን ይጫወታል።  መንግሥት ዘላቂ አገልግሎቶችን መስጠት በማይችል ጊዜ ሁሉ የልማት አጋሮች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መሬት ወርደዉ ግዙፍና በርካታ መርሐ ግብሮችን ተፈፃሚ ያደርጋሉ ምክንያቱም ይህን ማድረጉ አስፈላጊ ነዉ። » 

የድህነት ቅነሳን በተመለከተ በመላ አፍሪቃ የሚሰማዉ ዜና ሁሉ ጥሩ አይደለም ማለት ግን አይደለም። ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (UNDP) ከሰሃራ በታች ባሉ አፍሪቃ ሃገራት የሚታየዉን ልማት በተመለከተ ይፋ ባደረገዉ መጨረሻ ዘገባ የልማት ለዉጦች መታየታቸዉን ጠቅሶአል። ድርጅቱ በተለይ ከጎርጎረሳዉያኑ 2006 እና በ 2017 በነዚሁ ሃገራት የሰዉ ልጆች ሕይወት በሰባት ዓመት መጨመሩንም አትቶአል።   

የሰብአዊ ልማት ፕሮጀክት ዳይሬክተር ሳቢና አልከሪ ዓለም አቀፍ የዘርፈ ብዙ ድህነት መለኪያ ጥናት መዘርዝር በዓለም ዙርያ ድህነትን ለመቀነስ አንድ ግብዓት መሆን ይችላል ሲሉ ተስፋቸዉን ገልፀዋል።

Infografik Weltregionen mit der höchsten Armutsquote EN

«መንግስታት ውስጣዊ ጉዳዮችን ለማሻሻል ያስመዘገቡት እድገትን ለመቆጣጠር፤  በግልጽ እንዲታይ ለማድረግና  ተቀባይነት እንዲኖረዉ  ሊጠቀሙበት ይችላሉ።»

በጎርጎረሳዉያኑ ጥቅምት 17 ታስቦ የሚዉለዉ የዓለም የድህነት ቀን ዓለም አቀፍ የዘርፈ ብዙ ድህነት መለኪያ ጥናት ዶሴ በኢንተርኔት አማክኝነት ለዓለም ይፋ ይሆናል።  በዚህም ምሁራን የአካባቢዉን ብሎም የሃገሮቻቸዉን መረጃ መተንተን እንዲችሉ ያስችላቸዋል።

"እንዴት ሊሻሻል እንደሚችል አስበዉ እንዲደርሱበት እንሻለን። ምክንያቱም የእርሱ አእምሮ የፈጠራ ችሎታዎች እና ስለጉዳዩ ያላቸዉ ዙርያ መለስ እዉቀት በዉጭ ካሉ ጉዳዮች የተሻለ መስታት ስለሚስችላቸዉ ነዉ» 

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ