1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለም አቀፉ ሽምግልና፤ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘገባ እና የተቃውሞ ሰልፎች 

ዓርብ፣ ኅዳር 3 2014

ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴው በዚህ ሳምንትም በበርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ አስተያየቶችን እያስተናገደ ነው። በየጊዜው ለመጠቆም እንደሞከርነው ጽንፍ የያዙ እና ለችግሩ ከመፍትሄ ይልቅ አባባሽ የሆኑትን ወደ ጎን ብለን ትርጉም ያለው ትችት እና ሃሳብ ያዘሉትን መራርጠናል። 

https://p.dw.com/p/42wLQ
Äthiopien | Treffen Getachew Reda, Olusegun Obasanjo und Debretsion Gebremichael
ምስል Privat

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት 

መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጀው የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር /ህወሃት/ ጥቃቴን አጠናክሬ ወደ ዋና ከተማ አዲስ አበባ እየተጠጋሁ ነው የሚል መልእክት በሚያስተላፍበት ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ሁሉም ወገኖች የጦር መሣሪያቸውን አስቀምጠው ወደ ሰላም ድርድር እንዲገቡ የሚቀርበው ጥሪ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተጠናክሮ ተሰምቷል። ይኽን ተከትሎም የአፍሪቃ ሕብረት የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ የቀድሞ የናይጀሪያ ፕሬዝደንት ኦሊሴንጎን ኦባሳንጆ ወደ መቀሌ ተጉዘው እሁድ ዕለት ከህወሃት አመራሮች ጋር መወያየታቸው ይፋ ሲሆን፤ ናሲር ኢተፋ በፌስቡክ፤ «በማንኛውም መንገድ ጦርነት መፍትሄ አይደለም። መፍትሄው ከታማኝ ሰዎች ጋር መወያየት እና የአሁን የኢትዮጵያ ችግሮች ከባለድርሻ አካላት ጋር ሁሉ መገናኘት ነው። መልእክታችንን እንኪቀበሉት ድረስ ማቅረባችንን እንቀጥላለን። ከእኔ ጋር ሁኑ።» ሲሉ ለሰላም ሌሎችም ከጎናቸው እንዲቆሙ ጋብዘዋል። ኤልያስ ዋሪሶ በበኩላቸው፤ «ከሁሉ በላይ ስለ አጠቃላይ ሁኔታው ኃላፊነት የሚሰማው እና የሚመለከተው መንግሥትን እንደመሆኑ ለሰላም እና ለሰላም ቅድሚያ ቢሰጥ ጥሩ ነው። ምክንያቱም ሰላም የሰው ህይወትም ሆነ የንብረት ኪሳራ ይቀንሳል።» ባይ ናቸው።  አብዛኛው በሚባል ደረጃ በዚህ ሃሳብ የሚያስማማ አይመስልም፤ ሰያው ቃዋ የሚል የፌስቡክ ስም ያላቸው አስተያየት ሰጪ« «ሰላማዊ ሰዎች ላይ ዘረፋ ግድያና እንግልት የሚያደረገው የአሸባሪው ቡድን ነው፣ ከአሸባሪ ጋር የትኛው አገር ተደራድሮ ያውቃል? አሜሪካና ምዕራባዊያን ለኢትዮጵያ ህዝብ አዝናችሁ ይመስለኝም።» በማለት ዘገባውን ያቀረበውን ዶቼቬለን ሳይቀር ተችተዋል። የሀብታሙ የኋላሸት ሃሳብም ይመሳሰላል፤ «የኢትዮጵያ ህዝብ ከአሸባሪና አገር አፍራሽ ድርጅት ጋር ከዚህ በኋላ ምንም ድርድር እንዲኖር አይፈልግም። የትኛውም አካል መንግሥትን ጨምሮ የድርድሩን ሀሳብ የሚደግፍ ከሆነ ከአሸባሪው ድርጅት ተለይቶ አይታይም።» ሲሉም ያስጠነቅቃሉ። ያሬድ ግርማ ደግሞ ፤ «ሕጋዊ መንግሥት እና በሽብርተኝነት የተፈረጀን እኩል ማድረግ ተገቢነት የለውም።» ነው የሚሉት። አህመዲን አቡበከር አህመዲን ደግሞ ምነው ድርድሩ አረፈደ የሚሉ ይመስላል፤ «አሁን ይህ ሁሉ ግፍና መከራ ከደረሰ በኋላ ነው ድርድር? የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶች፤ አትሌቶች እና እናቶች ሲለምኑ አሻፈረኝ ያለ ቡድን ጋር ድርደር ብሎ ነገር አንቀበልም።» የበሃይሉ ወርቁ ተሰማ አስተያየትም ይመሳሰላል፤ «ድርድር ያበቃው ደብረፅዮንን ተንበርክከው ሰላም እንዲወርድ የለመኑት እናት ጊዜ ነው ።አሁን ሁሉም ያበቃለት ጉዳይ ነው። እንዲህ አይነት ቁማር ዐቢይ እኛ ኢትዮጵያውያን እንደማንቀበል አስረግጦ ይንገራቸው።» ኦብሲ ሪኪቻ ጅሬኛቲ ደግሞ፤ «በእትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን ከፈለጉ ለአሸባሪው ቡድን ማገዝ ትተው ገለልተኛ ሆነው አሸባሪው ቡድን ንፁሃን ላይ እየፈፀመ ያለው ከመሠረቱ ተጠንቶ ለሕግ እንዲቀርብ መሥራት ነው። ያለበለዛ የአሸባሪውን ጥፋት እየደበቁ በርዳታው ምክንያት ዕቃ እያቀረቡለት በህዝብ የተመረጠ መንግሥት ላይ በተለያየ መንገድ ጫና ማድረግ በኢትዮጵያውያን የዓይን ብሌናችን ውሥጥ አሸዋ መርጨት ሥለሆነ አኛ ኢትዮጵያውያን መቸም ቢሆን ለሀገራችን ሉዓላዊነት እና ክብር በአንድነት ቆመን መስዋትነትን ለመክፈል ዝግጁ ነን።» ይላሉ። አብዱልረዛቅ አብደላ ግን ስለሰላም ዘማሪ ናቸው፤ «ለሰዉ ልጆች ሰላም፤ ለሰዉ ልጆች ፍቅር፤ ለሰዉ ልጆች ሰላም» ለሰዉ ልጆች ፍቅር ፣ ለሰዉ ልጆች••• ባለላም ዙሪያ ሁሉ••• » ካሉ በኋላ ፤ « እስካሁን ብዙ ሰው ስለሞተ ከዚህ በኋላ ብዙ መሞት አለበት ብሎ የሚያስብ ህዝብ ጋር መኖር ድንቅ ነው። የኔ ብቻ ካልሆነ የሚል ድንዙዝ እያለ እንዴት ተብሎ በሰላም ይኖራል? ኧረ እባካችሁ ያስታርቀንና የተቀረው ምስኪን ህዝብ በሰላም ይኑርበት። ትዕቢተኝነት ምን ያደርጋል!!» በማለት የሰላም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።  

Symbolbild I BigTech I Social Media
ምስል Jakub Porzycki/NurPhoto/picture alliance

 

የሕወሓት ታጣቂዎች በአማራ ክልል የነፋስ መውጫ ከተማን ተቆጣጥሩበት ወቅት ሴቶችን በቡድን መድፈር፣ ሐብት ንብረት መዝረፍና ማጥፋታቸውን የሚዘረዝርውን የአምነስቲ ኢንተርናሽናልን ዘገባ አስመልክቶ በርካቶች በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመውን ግፍ ያወገዘ አስተያየታቸውን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አስነብበዋል። ዋስይሁን በላይ «በጦር ወንጀለኝነት ለዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት መውሰድ ያስፈልጋል።» ሲሉ እሸቱ ያኖሬ በበኩላቸው፤ «ዘላለማዊ የታሪክ ጠባሳ።» ብለውታል። ግርማ ሽፈራው ከዚህም የባሰ ስለመኖሩ ነው የጠቆሙት፤ «ገና መቼ ተነገረና ግፍና በደላቸው ተቆጥሮ አያልቅም በቃላት ለመናገርም ይዘገንናል !!ከሰው አልፎ በእንስሳትና በምርት ላይም የክፋት ብትራቸው አርፏል!» ዶቼቬለንም አምነስቲ አለ ከማለት ውጪ እናንተም እውነቱን ተናገሩ ብለውናል። አቶ ግርማ፤ ዶቼቬለ መረጃዎች ላይ ተመሥርቶ እውነታውን ለማሳወቅ እንግዳ አይደለም፤ ሆኖም አስተያየትዎን በአዎንታዊነት እንደምንቀበለው ለመግለጽ እንወዳለን። ትግራይ ወንድም የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ ዘገባውን ያመኑ አይመስሉም፤ «ፍጹም ሀሰት ነው። አማራ እና አፋር ክልል እያንዳንዱን ቤተሰብ ደውላችሁ ጠይቁ።» ይላሉ። ፋይዛ ሚፍታ ግን ስጋታቸው ከፍ ያለ ነው፤ «ወሎንስ እንዴት አድርገውት ይሆን? » በማለትም ይጠይቃሉ። ኦስማን ኢብራሂምም ተጨማሪ ጥቆማ ነው የሰጡት፤ « እስኪ ወደ ወለጋም ይውረዱና ያጣሩ እንዲሁም ወሎ ውስጥስ ስንት ነገር ፈፅመዋል?» 

Ätopien | Unterstützer des Premierministers feiern
ምስል Tiksa Negeri/REUTERS

ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ የመከበቧ ወሬ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መሰራጨቱ በሩቅ ላሉ ብዙዎች ስጋት መሆኑ ታይቷል። የከተማዋ እና የአካባቢው ከተሞች ነዋሪዎችም አልተከበብንም ሰላም ነው ከሚለው መልእክታቸው ጎን ለጎን ትክክለኛ መረጃ አያስተላልፉም ያሏቸውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን የተቹበት፤ በውጊያ እየተሳተፉ ያሉትን የህወሃት እና ኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችን ያወገዙበት ሰልፍ በየቦታው ተካሂዷል። ግዛው አየለ በፌስቡክ፤ «ገራሚ አለም ውስጥ መኖሬን ያወቅሁት አሁን ነዉ፤ ትልቅ ስም እና ዝና ያላቸው የመገናኛ ተቋማት *** ትልቅ ነጭ ውሸት መዋሸታቸው ብቻ ሳይሆን *** ላንቃቸው የሚከፈተው በሙስና መሆኑ አጀብ አሰኝቶኛል ።» ይላሉ፤ ታምራት ዳንኤል ሃቶም እንዲሁም « አሳፋሪና አሳዛኝ ድርጊት ነው። የምዕራባውያንና የእነሱ ሚዲያቸዉ በይፋ ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እንደከፈቱ የዓለም ማህበረሰብ አውቋል።» ነው የሚሉት። ኢሪሶምፒያ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ደግሞ፤ « ይኽን የዛሬውን ሰልፍ CNN ከዘገበው ሰልፉ መካሄዱን አላምንም።» ሲሉ ተሳልቀዋል። ጌታሁን ዳምጤ ደግሞ፤ «ምዕራባውያን ሆን ኢትዮጵያን ተውልን አይመለከታችሁም» ነው ያሉት። የትዊተር ተጠቃሚው ካሚል ኑሪ በበኩላቸው፤ «ኢትዮጵያውያን ከምዕራባውያን ጣልቃገብነት እናት ሀገራችሁን ለመከላከል በአንድነት ተነሱ።» የሚል ጥሪ አስተላልፈዋል። የተለያዩ ኤምባሲዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሠራተኞቻቸው እና ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ማሳሰባቸውን በተመለከተ፤ ሰለሞን አማረ ፤ «ሀገራችንን ለቃችሁ የምትወጡ የአፍሪቃ ሃገራት፤ ሊግ ኦፍ ኔሽን ላይም ብቻችንን ነበርን፤ አሁንም ብቻችንን ነን እና መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ።» በማለት ትዝብታቸውን ሲያጋሩ ሙክታር አሊ ደግሞ በትዊተር፤ «ኢትዮጵያን ለቅቃችሁ ወደ ሀገራችሁ ግቡ ከተባሉ የውጪ ሀገር ዜጎች ጉዳይ ምን እንማራለን?» ብለው ከጠየቁ በኋላ፤ « የሀገርን መኖር አስፈላጊነት ነው፤ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!» ሲሉ ምላሹን ሰጥተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ