1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለም ለኮሮና ተሐዋሲ ክትባት እየተረባረበ ነው

ቅዳሜ፣ ግንቦት 8 2012

የኮሮና ተሐዋሲን ለመዋጋት በርካታ ምርምሮች እየተከናወኑ ነው። አብዛኞቹ ምርምሮች ታዲያ የሚከወኑት ከአፍሪቃ ውጪ ነው። ኮሮና የፈጠረው ቀውስ እና ስጋት መላ ዓለምን ለኮሮና ተሐዋሲ ክትባት እንዲረባረብ ማድረጉ ደካማ ምጣኔ ሐብት ላላት አፍሪቃም ሊተርፍ ይችል ይኾናል። ምናልባትም ያልተጠበቀችው አፍሪቃ ዓለምን ትታደግም ይኾናል።

https://p.dw.com/p/3cJLe
ምስል picture-alliance/dpa/C. Gateau

ዓለም ለኮሮና ተሐዋሲ ክትባት እየተረባረበ ነው

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሳይንቲስቶች የኮሮና ተሐዋሲ ክትባትን ለማግኘት ከፍተኛ ርብርብ ላይ ናቸው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ምርምሮችም እየተከናወኑ ነው። ክትባቱን ለማግኘት ገንዘብ ከየአቅጣጫው ይፈሳል፤ ሳይንቲስቶችም እንቅልፍ አጥተው ለክትባቱ ግኝት እየታተሩ ነው። በመላው ዓለም የሚገኙ ሳይንቲስቶች ክትባቱን ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥናት በዓለም ጤና ድርጅት በኩል አስተሳስረውታል።

ሲቴል የተሰኘው የክሊኒክ ምርምሮች ላይ ጥናት የሚያደርግ ተቋም እስከ ዓርብ፤ ግንቦት 7 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በሰበሰበው መረጃ መሰረት ኮቪድ 19ን የሚመለከቱ 1072 ምርምሮች በዓለማችን የተለያዩ ቦታዎች እየተከናወኑ ነው። ከእነዚህ ውስጥ ታዲያ አፍሪቃ ውስጥ የሚደረገው ምርምር ቊጥሩ 31 ብቻ ነው።  ምርምሩ በዋናነት ከሚካሄድባቸው የዓለማችን ክፍሎች ቻይና በቀዳሚነት ትገኛለች፤ 342 ምርምሮች ይከናወኑባታል። ለኮቪድ 19 ክትባት አለያም መድኃኒት ለማግኘት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ደግሞ 196 ምርምሮች እየተከናወኑ ነው። አውሮጳ በአጠቃላይ 297 ምርምሮችን በኮቪድ ዙሪያ ታከናውናለች።  

የዓለም ጤና ድርጅት መጋቢት ወር ውስጥ ባቀረበው የትብብር ሐሳብ መሰረት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሳይንቲስቶች ኮቪድ 19 ላይ ምርምር ለማድረግ በጋራ እየሠሩ ነው። በትብብሩ ዙሪያ ተሰባስበው የሚሠሩ የምርምር ተቋማቱ ከ30 ሃገራት የተውጣጡ ሲኾኑ፤ ከ70 በላይ ናቸው። የመሰባሰባቸው ዓላማም በተናጠል የሚደረጉ ጥናቶችን በማቀናጀት ክትባቱ የሚገኝበት ጊዜን ማቀላጠፍ ነው።

Deutschland Forschung Coronavirus
ምስል picture-alliance/dpa/C. Gateau

ከምርምር ፕሮጀክቱ ስብስቦች አንዱ የኾነው የኦክስፎር ዩኒቨርሲቲ የተዛማች በሽታዎች ሠነድ ምርመራ ተቋም ዳይሬክተር ፊሊፕ ጉዌሪን የምርምር ስብስቡ አንዳች ችግር እንደተጋረጠበትም ይናገራሉ። ለምርምር የተሰባሰቡት ተቋማት ዋነኛ ዓላማቸው በኮቪድ 19 የሚሞቱ ሰዎች ቊጥርን መቀነስ ላይ ያተኮረ ነው። ተቋማቱ የወከሏቸው ሃገራት አብዛኛዎቹ የተደራጀ የጤና ስርዓት እና በኮቪድ 19 የታመሙ ሰዎች ድጋፍ የሚያገኙበት ቊሳቋስ በስፋት ያላቸው ናቸው። ምርምራቸውም ይኽንኑ ትኩረት ያደረገ ነው። አፍሪቃ ውስጥ የጤና ተቋማት በስፋት አለመደራጀታቸው እና በኮቪድ 19 በጽኑእ ለሚታመሙ ሰዎች በቂ አጋዥ መሣሪያዎች አለመኖር ለአኅጉሪቱ ከወዲሁ የተጋረጠ ተግዳሮት ነው።

ለአንዱ አካባቢ የታሰበ ክትባት በሌላው አካባቢ ውጤቱ ያን ያኽል ሊኾንም ይችላል የሚል ጥርጣሬ ያደረባቸው ደግሞ ጆሐንስቡርግ ውስጥ በሚገኘው የዊትዋተርስሳንድ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ክፍል ኃላፊዋ ሔለን ሪስ ናቸው። ክትባቶቹ ባንዳንድ አካባቢዎች ጥሩ ውጤት አምጥተው በሌላው ደከም ሊሉ የሚችሉትም በነዚያ አካባቢዎች ሌሎች በሽታዎች የመዛመታቸው እና ተመጣጣኝ ምግብ እጥረት መኖሩ ነውም ብለዋል። ክትባቶቹ አፍሪቃን ችላ ያሉም ይመስላሉ ሲሉ አክለዋል።  

Symbolfoto Impfstoff
ምስል picture-alliance/Geisler-Fotopress/C. Hardt

አፍሪቃውያን ምንም እንኳን እጅግ ጥቂት ቢባልም የአፍሪቃ አኅጉርን ያማከለ የኮቪድ 19 ምርምር እያደረጉ ነው። አብዛኛው ምርምር ታዲያ በሀገር በቀል ምርቶች ላይ እና እጽዋቶች ላይ በማተኮር ባሕላዊ መድኃኖቶችንም ያማከለ ነው። አፍሪቃ መሰል ምርምር ለማከናወን ብዙውን ጊዜ የሚገጥማት የገንዘብ እጥረት ምርምሮቹ እንዳይፋጠኑ ሰበብ ሲኾኑም ይታያል። አፍሪቃ ውስጥ የኮቪድ 19 መድኃኒትን አገኘን፤ መከላከያውን ለማምረት ጫፍ ደርሰናል የመሳሰሉ ተስፋዎች ብልጭ ሲሉ ይታያል። አኹንም ድረስ በተጨባጭ የሚታዩ ነገሮች የሉም።

የአፍሪቃ ኅብረት የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽንን ለመታገል ለሚደረግ ምርምር 19 ሚሊዮን ዩሮ መድቧል። የአፍሪቃ የሳይንስ አካዳሚ በበኩሉ ኮሮና ላይ ምርምር ለማድረግ ከመንግሥታት እና ሌሎች ለጋሶች 2,5 ሚሊዮን ዩሮ አሰባስቧል። ምናልባት ግን አፍሪቃ ያሰባሰበችው ይኽ ገንዘብ የአውሮጳ ኅብረት ተሐዋሲውን በዓለም ዙሪያ ለመዋጋት በሚል ከመደበው የ7,4 ቢሊዮን ዩሮ አንጻር ትንሽ ሊመስል ይችላል። እናም በአኅጉሪቱ የሚደረጉ ምርምሮች እጅግ አነስተኛ ቢኾኑም፤ የአኅጉሪቷን ነዋሪዎች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ በመኾናቸው ሊደገፉ ይገባል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ