1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዐቢይና ኦዴፓ የገጠማቸው ተቃውሞና የትዊተር መስራች ጉብኝት በኢትዮጵያ

ዓርብ፣ ኅዳር 19 2012

አንዳንድ የማኅበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚዎች ብልፅግና ፓርቲ በይፋ ባይመሰረትም የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችን በይፋ እየተሰናበቱ ነው። በአራት አባላት፣ በአምስት አጋሮች ከ28 አመታት በላይ ኢትዮጵያን ያስተዳደረው ኢሕአዴግ በጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አህመድ አጋፋሪነት የጀመረው የውህደት መንገድ አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል። 

https://p.dw.com/p/3TuSq
Nobelpreisträger Abiy Ahmed

የኢሕአዴግ ውህደት ትችት በርትቶበታል

በጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ አባባል የኢትዮጵያ ብልፅግና ፓርቲ በይፋ የተመሰረተ ይመስላል። ጠቅላይ ምኒስትሩ ትናንት በፌስቡክ ባሰራጩት የቪዲዮ መልዕክት ንግግራቸውን ሲጀምሩ «ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና የብልፅግና ፓርቲ አባላት በሙሉ» የሚል አገላለጽ ተጠቅመዋል። 
ጠቅላይ ምኒስትሩ ትናንት ሐሙስ ይኸን መልዕክት በፌስቡክ ገፃቸው በቪዲዮ ሲያስተላልፉ ከኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች አንዱ የሆነው ደኢሕዴን ገና የውህደቱን ጉዳይ አላጸደቀም። ዐቢይ በመልዕክታቸው «የኢሕአዴግ ውህደት የፌደራል መንግሥታዊ አወቃቀሩን አፍርሶ በአሐዳዊ ሥርዓት ይተካል» የሚል ወቀሳ ለሚሰነዝሩ ምላሽ ሊሰጡ ሞክረዋል። 
መጀመሪያ በጠቅላይ ምኒስትሩ የፌስቡክ ገፅ የተሰራጨው እና ዘግየት ብሎ በብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ፣ ከገዢው ግንባር የጠበቀ ቁርኝት ባለው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዲሁም በኢሕአዴግ የማኅበራዊ ድረ-ገፆች የተቀባበሉት ቪዲዮ ሌሎች ሁለት አላማዎች ያሉትም ይመስላል። ዐቢይ በአማርኛ እና በኦሮሚኛ ቋንቋ በተላለፈ መልዕክታቸው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውጥንቅጥ በአዎንታዊ እና አሉታዊ ምክንያቶች ስማቸው ለሚነሳው የቄሮ እና የፋኖ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ከጎናቸው እንዲሰለፉ ሊያግባቡ ሞክረዋል። 
ዐቢይ «የብልፅግና ፓርቲ መሠረቱ በኦሮሚያ ክልል የቄሮን ትግል በአማራ ክልል የፋኖን ትግል በደቡብ ዘርማ እና ሌሎች ወጣት አደረጃጀቶች በጋራ ያደረጉትን ትግል ከተረት ተረት ወደ እውነተኛ ብልጽግናና ሰላም፤ ዴሞክራሲያዊ እና አንድነት ለማሸጋገር የተደረገ ሒደት መሆኑ ታምኖ ቄሮዎች፤ ፋኖዎች እንኳን ደስ ያላችሁ፤ የታገላችሁበት ፓርቲያችሁ ተመስርቷል። ከፓርቲያችሁ ጋር ሆናችሁ ስታነሱ የነበረውን ጥያቄ ወደ ተግባር እንዲመለስ አስፈላጊውን ጥረት እንድታደርጉ ጥሪዬን ላቀርብላችሁ እፈልጋለሁ» ብለዋል። 

ሰመረ ሙሉጌታ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "ቄሮ፣ ፋኖ እና ዘርማ ወደ ስልጣን ስላመጣችሁኝ እንደምስጋና ሐወልት አቆምላችሗለሁ። ተያ በኋላ ግን ዋ! አርፋቹ ተቀመጡ፣ አትቅበጡ ፣ አትቅበጥበጡ" ማለታቸው ነው ሲሉ የግል አተያያቸውን ፅፈዋል። 

Äthiopien |  Abstimmung EPRDF
ምስል EPRDF

ጠቅላይ ምኒስትሩ ሶስቱን ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች በስም ጠርተው ሲያመሰግኑ ሌሎችን ችላ ብለዋል የሚል ቅሬታ በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ታይቷል። ሳሙኤል በላይነሕ የሲዳማ ዞን ክልል ለመሆን ባሳለፈው የፖለቲካ ውጣ ውረድ የጎላ ሚና የነበራቸው ኤጄቶዎች ተዘንግተዋል የሚል ስሜት አድሮባቸዋል። ሳሙኤል «የጠቅላይ ምኒስትሩ ንግግር "ኤጄቶዎች ለሀገራዊ ለውጥ ሳይሆን ለሕዝባችሁ ልዕልና ስለታገላችሁ በየአካባቢያችሁ የማስታወሻ ሃውልት ማቆም ትችላላችሁ" እንደማለት ነው። ባይሉም አይቀርም» ሲሉ ስሜታቸውን በፌስቡክ ጽፈዋል። ሳሙኤል «ብቻ የዐቢይ መንግሥት ያሠራቸውን ኤጄቶዎችን ይፍታልን፤ ምርጫ ቦርዱ የመጨረሻውን የሕዝበ ውሳኔውን ውጤት ይፋ ያድርግልን፤ የደቡብ ክልል መንግሥት ቶሎ ስልጣኑን ያስረክበን እንጂ በቤታችን ብዙ የምንነጋገረው ብዙ የምንሠራው ሥራ አለብን። ስለ ብልፅግናውም ቢሆን። በግፍ የታሠሩ ኤጄቶዎች እስካልተፈቱ ድረስ የሲዳማ ወጣት ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ሊሆን አይችልም" ሲሉ ጠንከር ያለ አስተያየት ሰንዝረዋል። 

ዐቢይ ፓርቲያቸው ሕጋዊ የምዝገባ ሒደት አልፎ የምርጫ ቦርድ እውቅና ከማግኘቱ በፊት «ፓርቲያችሁ ተመስርቷል» ለማለት ያበቃቸው ምክንያት ባይታወቅም በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ግን መነጋገሪያ መሆኑ አልቀረም። በተለይ ጠቅላይ ምኒስትሩ በፌስቡክ እና በትዊተር ገፃቸው የኢሕአዴግን ውህደት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እንዳጸደቁ ማስታወቃቸው «ክቡርነትዎ፣ በጉዳዩ ላደረሱን ፈጣን መረጃዎ እናመሰግናለን። ፓርቲዎ ከዚህ ቀደም እንደተሰቃየንበት ሳይሆን ሁሉም ድምፆች ዕኩል ወደሚደመጡበት አዲስ ምዕራፍ ይመራናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን» ከሚለው የሑንዴሳ ስለሺ አስተያየት ጀምሮ በርካታ ሙገሳ እና ትችት አስተናግዷል። ያረጋል መኩሪያው «ውህደቱን እንደግፋለን ነገር ግን የፓርቲው ፕሮግራምና አደረጃጃቱ ለሕዝቡ ግልፅ ይሁን። የንፁህ ኢትዮጵያዊያን ሞት ይብቃ። ፍትህ ይስፈን። እዚህ ላይ በትኩረት መስረት ያስፈልጋል» ብለዋል።

መሐመድ ጁሐር «የደኢሕዴን የስብሰባ ውስኔ ሳይታወቅ የትም አይደርስም በሚል ስሜት መግለጫ መሰጠቱ ለደኢሕዴን ያላቸውን ንቀት ያሳያል። ለነገሩ ደኢሕዴን ድሮም በግ ነው። ወዳሻቻው የሚጎትቱት» ሲሉ ዐቢይ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ተችተዋል። ደኢሕዴን ውሕደቱን በሙሉ ድምጽ ማፅደቁን ያስታወቀው ትናንት ሐሙስ ማምሻውን ነበር። 
ኑርሑሴን ፈቂ ሐሴኖ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) ውህደቱን ሲያጸድቅ «ለማ መገርሳ በስብሰባው አልነበሩም የሚል መረጃ አለ። ለማንኛውም ከኦሮሚያ የሚያገኙትን ድምፅ (በምርጫ) እናያለን» የሚል አስተያየት አስፍረዋል። ፌልሜታ ገዳ በበኩላቸው «ኦዲፒ እንደ ፓርቲ አልተስማማም፤ በአንጃ እንጂ። ይህ የፓርቲዉ ጉዳይ ነዉ፣ ውሸት ግን ያሳፍራል፤ ወንጀልም ነዉ» የሚል ሌላ አስተያየት ጠቅላይ ምኒስትሩ ስለ ውህደቱ ባሰፈሩት መረጃ ሥር ፅፈዋል። 
የኢሕአዴግ ውሕደት ጉዳይ በኦዲፒ ውስጥ መከፋፈል ፈጥሯል የሚል ተባራሪ መረጃ ቢሰማም ማረጋገጫ አልተገኘም። የኦሮሞ ልሒቃን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ባደረጓቸው ውይይቶች ይኸው ጉዳይ በተደጋጋሚ ሲነሳ ተስተውሏል። ከዚያ ባሻገር ግን ኦዲፒ ወደ ብልፅግና ፓርቲ ለመቀላቀል መወሰኑ የበረታ ትችት ተሰንዝሮበታል። 

ደረጄ በጊ በበኩላቸው የጠቅላይ ምኒስትሩን ፓርቲ የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች «ተባብረው ሊያስቆሙ ይገባል» የሚል ዕምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። «የኦሮሚያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ያለው በኦነግ፣ በኦፌኮ እና በኦብፓ እጅ ነው። እነዚህ ተደራድረውም ሆነ ተቀባብለው ወደ አንድ ነገር መድረስ ካልቻሉ በምንም መልኩ ዐቢይን መውቀስ አንችልም። ከእነዚህ አንዱ በስግብግብነት ወይም በአጉል ትምክህት የኦሮሞን የወደፊት ዕጣ ማበላሸት የለበትም። ምክንያቱም ዐቢይ ለራሱ ያሰበውን እሱ እያደረገ ነው። እነርሱም እውነት ለኦሮሞ ህዝብ ታግለው ከሆነ የሚፈተኑበት ሁነኛ ጊዜ አሁን ነው። ማወቅ ያለባቸው በአሁኑ ወቅታዊ ሁኔታ ኦሮሚያን የትኛውም ፓርቲ ብቻውን ማስተዳደር አይችልም። ይህንን ከግንዛቤ በመስገባት የሆነ ነገር ላይ ደርሰው ብልፅግና ፓርቲን ያስቆመሉ ብዬ አስባለሁ» የሚለው በፌስቡክ የሰፈረ የደረጄ በጊ አስተያየት ነው። 
ያለም ዱቼ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ «ሁሉም ፓርቲዎች ውህደቱን በሙሉ ማፅደቃቸው እንዳስገረመኝ ማመን እፈልጋለሁ» ሲሉ ጽፈዋል። ለጠቅላይ ምኒስትሩ ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መልዕክት ደግሞ «እርስዎ እና የእርስዎ ቡድን በሚቀጥለው ምርጫ አሸናፊ ትሆናላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ» ብለዋል። ቶሎሳ ጉርሜሳ «ብልፅግና ፓርቲ በኦሮሚያ ቦታ የለውም። እንዳያስቡ ብዙ ምርጫዎች አሉን» ሲሉ አስተያየታቸውን አስፍረዋል። አባ ጋዮ የተባሉ ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ እንደ ቶሎሳ ሁሉ አዲሱ ፓርቲ በኦሮሚያ ተቀባይነት የለውም ከሚል ድምዳሜ ደርሰዋል። «ከ5000 በላይ የቄሮ አጥንት እና ደም ገብሮ ለዚህ ሥልጣን ያበቃዎ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ነው። ለማ መገርሳን አጭበርብረው ድምፅዎን በማጥፋት አራት ኪሎ ከገቡ በኋላ እውነተኛ ማንነትዎን ገለጡ። በኦሮሚያ እና በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ክሕደት ፈፅመዋል» ሲሉ ጠቅላይ ምኒስትሩን ከሰዋል። 
ምኅረቱ ታደሰ «የፓርቲዎቹ ሁሉም አባላት በውህደቱ ጥቅም እና ጉዳት ላይ በቂ መረጃ ቢኖራቸው እና ቢሳተፉ የተሻለ ነበር» የሚል አስተያየት አላቸው። ገሬ ሲሳይ አማረ « ‘ ማፍረስ ቀላል ነው፤ መገንባት ነው የሚከብደው’ ለሚለው አባባል የእርስዎ ስራ በቂ ማስረጃ ነው» ብለዋል።

Äthiopien Protest
ምስል Reuters/T. Negeri

የትዊተር ሥራ አስፈፃሚ በኢትዮጵያ

የትዊተር ሥራ አስፈፃሚ ጃክ ዶርሴይ እና የቀድሞው የአሊባባ ሊቀ-መንበር ጃክ ማ በሳምንቱ የወጣቶች ሥራ አጥነት ወደ ሚያንገበግባት ኢትዮጵያ ጎራ ብለው ነበር። ሁለቱም ቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ ኩባንያ መሥርተው ስኬታማ ማድረግ ችለዋል። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ ሔደው የተቀበሏቸው ቻይናዊው ጃክ ማ በኢትዮጵያ ዲጂታል የግብይት እና የስልጠና ማዕከል ለማቋቋም የመግባቢያ ስምምነት ፈርመዋል። ተጠቃሚዎች በ140 ፊደላት መልዕክት የሚያስተላልፉበትን ትዊተር የተባለ የማኅበራዊ ድረ-ገፅ ከሌሎች ሶስት የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የመሰረቱት እና ተቋሙን በሥራ አስፈፃሚነት የሚመሩት ጃክ ዶርሴይ ግን የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ያን ያክል ትኩረት የተሰጠው አልነበረም። 

ጃክ ዶርሴይ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ላይ መሠረት አድርገው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ጀማሪ ኩባንያዎች ካቋቋሙ ኢትዮጵያውያን ተገናኝው ውይይት አድርገዋል። ጃክ ዶርሴይ ከጎበኟቸው፤ ቁጭ ብለው ካነጋገሯቸው አብዛኞቹ ወጣቶች እና ታዳጊዎች ናቸው። የአይ ኮግ ፕሪጀክት ማኔጀር የሆነችው ቤተልሔም ደሴን፣ የልባዊ አካዳሚ ተማሪዎችን፣ የኩዱ ቬንቸርስ ተባባሪ መሥራች እና ኃላፊ ኖኤል ዳንኤልን ጨምሮ ከበርካታ ሥራ ፈጣሪዎች ጋር ተገናኝተው የተነሷቸውን ፎቶዎች በትዊተር ገፃቸው አጋርተዋል።

ራይድ የተባለው የታክሲ አገልግሎት ከመሠረተችው ሳምራዊት ፍቅሩ ጋር በተነሱት ፎቶ «ከ90 በመቶ በላይ ተቀጣሪዎቿ ሴቶች ናቸው» ሲሉ አድንቀዋል። እንደ እሳቸው ስኬታማ ኩባንያ መሥራች የሆነውን ደቡብ አፍሪካዊ ኤሎን ሙስክን ጠቅሰው «የቴስላ ምርቶችን በኢትዮጵያ ማስተዋወቅ ትፈልጋለች» የሚል መልዕክት አስፍረዋል። ቴስላ በኤሎን ሙስክ የተቋቋመ ኩባንያ ሲሆን በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ቅንጡ ተሽከርካሪዎች በማምረት ይታወቃል። ወጣት የሥራ ፈጣሪዎች የሚያግዘው ብሉ ሙን የተባለ ኩባንያን የመሰረቱት ዶክተር እሌኒ ገብረ መድህን «ስለማድመጥህ እና አስደናቂ እይታዎችህ እናመሰግናለን» ሲሉ ለጃክ ዶርሴይ ትዊተር ላይ ፅፈዋል። ዶርሴይ ወደ ብሉ ሙን ቢሮ አቅንተው የስድስት ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን ዕቅድ አድምጠዋል።  ዶክተር እሌኒ እንደፃፉት ጃክ ዶርሴይ «የንግድ ሥራ ከመጀመር ይልቅ  አንድ ጉዳይ ስለመፈጸም አስባለሁ። ለራሳችሁ ሐቀኛ ሁኑ» የሚል አስተያየት ለኢትዮጵያውያኑ ሰጥተዋል። 

ጃክ ዶርሴይ በዚህ ወር ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ጋና፣ ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካን ጎብኝተዋል። ወደ አገራቸው ሲመለሱ ባስተላለፉት የመጨረሻ መልዕክት አፍሪካ በመጪዎቹ አመታት በዓለም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ገበያ ትልቅ ሚና እንደሚኖራት ጠቁመዋል። በጎርጎሮሳዊው 2020 ዓ.ም. ከሶስት እስከ ስድስት ወራት ኑሯቸውን በአፍሪካ ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም ከአዲስ አበባ ወደ ሳንፍራንሲስኮ ሲያቀኑ ገልጸዋል።  

እሸቴ በቀለ

ተስፋለም ወልደየስ