1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውኃን አብዝቶ መጠጣት እና የኩላሊት ሥራ

ማክሰኞ፣ የካቲት 29 2014

የኩላሊት ህመም በየትኛውም የዕድሜ ክልል ሊያጋጥም የሚችል መሆኑን ባለፈው ሳምንት የዘርፉ የህክምና ባለሞያ በጤናና አካባቢ መሰናዶ ገልጸዋል። ምርመራ ካልተደረገ በቀር በአብዛኛው የኩላሊት ህመም ምልክቶች እንደማያሳይም ነው ሀኪሙ የተናገሩት። በዚህ ምክንያትም ብዙዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ህመሙ ጠንቶ እና ተባብሶባቸው ወደ ህክምና እንደሚሄዱም ያስረዳሉ።

https://p.dw.com/p/48Beh
29.06.2011 Fit und Gesund nieren

ጤና እና አካባቢ



የኩላሊት ህመምን አስቀድሞ ለመከላከል የስኳር መጠንን ማወቅ፤ የደም ግፊትም መከታተል እንደሚጠቅም በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በኩላሊት ህክምና ክፍል የውስጥ ደዌ እና የኩላሊት ሀኪም እንዲሁም በዚሁ ሆስፒታል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር መምህር የሆኑት የዶክተር አቤል ዘመንፈስ ይመክራሉ።  
በቀን ለሰውነታችን በቂ የሚባለውን የውኃ መጠን መጠጣት አዘውትሮ በህክምና ባለሞያዎች የሚሰጥ ምክር ነው። የኩላሊትን ጤና ለመጠበቅ በሚል አብዝቶ ውኃ መጠጣት በተለይ ታማሚ ለኾነ ኩላሊት ሌላ ጫና እና ችግር እንደሆነ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በኩላሊት ህክምን ክፍል የውስጥ ደዌ እና የኩላሊት ሀኪም እንዲሁም በዚሁ ሆስፒታል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር መምህር የሆኑትን የዶክተር አቤል ዘመንፈስ ባለፈው ሳምንት ገልጸውልናል። ውኃ ለኩላሊት ጤናማ አሠራር ጠቃሚ መሆኑን ሲገልጹም በተለይ የኩላሊት ጠጠር እና ኢንፌክሽን ጋር የተያያዙ ህመሞችን የማስቀረት ሚና እንዳለው ዘርዝረዋል። ሆኖም ግን በታማሚ ኩላሊት ላይ አብዝቶ ውኃ የመጠጣቱ ነገር ችግሩን ሊያባብስ ይችላል በማለት አስጠንቅቀዋል።



የህክምናው ይዞታ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙዎች የሚዳረስ ነገር እንዳልሆነ የሚታይ ነው። የተሻለ ህክምና ለማግኘት በሚልም በርካቶች ወደተለያዩ ሃገራት እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ እየከፈሉ ይሄዳሉ። ህክምና ከሚያስፈልግበት ደረጃ ከመድረስ አስቀድሞ ሊደረግ የሚገባ ጥንቃቄ እንዳለ የዘርፉ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ ይመክራሉ። 
የኩላሊት ህመሙ ቆይቶ እና ተባብሶ ዲያሌሲስ ህክምና ላይ ከደረሰ በኋላ ግን ይላሉ የዘርፉ ሃኪም የሚያስፈልገው የህክምና አማራጭ ውስን ነው። ይኽም ዲያሊሲስ ወይም ንቅለ ተከላ ነው። እዚህ ደረጃ ላይ ከመድረስ በፊት ግን ለህመሙ አጋላጭ የሆኑ ነገሮች ላይ አስቀድሞ ተገቢውን ክትትል ማድረግ የተሻለ መሆኑንም መክረዋል። የኩላሊት ህመም ምልክት ስለማያሳይም ምርመራ ማድረግ እንደሚበጅም ነው ያመለከቱት። ሰዎች ጤናቸውን በተመለከተ በአመጋገብም ሆነ በአኗኗር ልማዳቸው የሚያደርጓቸው ተገቢ ጥንቃቄዎች ታምመው በህክምና ከሚያገኙት ርዳታ እጅግ የተሻለ መሆኑን አጽንኦት የሰጡት ዶክተር አቤል ዘመንፈስ ይኽን አስመልክቶ ልናስተውል ይገባል ያሉትን ምክር ለግሰዋል።
ሙሉ ቅንብሩን ከድምጽ ማዕቀፉ ያድምጡ።
 ሸዋዬ ለገሠ 

Nieren Nierentransplantation Niere Operation
ምስል Ben Schonewille/Zoonar/picture alliance

ማንተጋፍቶት ስለሺ