1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዋግሕምራ ዞን ሰዎች በረሐብ እየሞቱ ነው

ረቡዕ፣ ጥቅምት 10 2014

በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በጦርነት ስር ባሉ አካባቢዎች ሰዎች በርሀብና በመድኃኒት እጥረት 10 ሰዎች መሞታቸውን የአይን ምስክር እና የዞኑ አስተዳደር ዐስታወቁ። በዞኑ ከ635 ሺህ በላይ ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ ምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/41ulg
Bahir Dar | Binnenflüchtlinge aus Waghemra
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በዚህ ሳምንት ብቻ የ11 ሰዎች ሕይወት አልፏል

ከነሐሴ 2013 ዓም መጀመሪያ ጀምሮ የህወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ወረራ ከፈፀሙበት ጊዜ ጀምሮ አብዛኛው በምግብ ለሥራ (safety net) መርሃ ግብር ይታገዝ የነበረው ሕዝብ ለከፋ የምግብ እህል እጥረት መጋለጡን የብሔረሰብ አስተዳደሩ በተደጋጋሚ ሲገልፅ ቆይቷል።

በዚሁ በጦርነት ቀጠና ለአስቸኳይ የምግብ እጥረት ለተጋለጠው የኅብረተሰብ ክፍል ርዳታ እንዲያደርሱ ለዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች ጥሪ ቢቀርብም አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ባለመቻላቸው ሰዎች በርሀብና በመድኃኒት እጥረት እየሞቱ እንደሆነ ነው ባለስልጣናት የሚናገሩት። በዝቋላና በጋዝጊብላ ወረዳዎች በዚህ ሳምንት ብቻ የ11 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የብሔረሰብ አስተዳደሩ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት መምሪያ ኃላፊ አቶ መልካሙ ደስታ ተናግረዋል። አንድ የአካባቢው ተፈናቃይ ከተጨባጭ ምንጭ አገኘሁ ብለው እንዳስረዱት በጋዝጊብላ ብቻ 10 ሰዎች በምግብ እትረት ሕይወታቸው አልፏል።

የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ገብሬ በበኩላቸው አብዛኛው የብሔረሰብ አስተዳደሩ በጦርነት ቀጠና ውስጥ በመሆኑ ምንም ዓይነት የገበያ እንቅስቃሴ የለም፣ ረጂ ድርጅቶችም እርዳታ ማድረግ ባለመቻላቸው የአካባቢው ነዋሪ በመድሀኒትና በእለታዊ የምግብ አቅርቦት እጥረት ሕይወቱ እያለፈ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የእለት ርዳታ ለማድረስ ቃል የገቡና ስምምነት ያደረጉ ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶችም ቃላቸውን መጠበቅ ባለመቻላቸው በጥቂት ቀናት ውስጥ በብሔረብ አስተዳደሩ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ እንደሚፈጠር አስጠንቅቀዋል። በተጨባጭ ርዳታ የሚፈልገው የብሔረሰብ አስተዳደሩ ሕዝብ ከ635 ሺህ በላይ እንደሚሆን ገልፀዋል። የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ መስፍን ሰሞኑን «የክልሉም ሆነ የፌደራሉ መንግሥት ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች በሕወሓት ለተያዙ አካባቢ ነዋሪዎች የምግብና የመድኃኒት በማቅረብ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥያቄ የቀረበላቸው ቢሆንም እስካሁን ምንም ነገር አላደረጉም» ብለዋል።

በጦርነት ቀጠና ውስጥ ካሉት 635ሺህ ርዳታ ፈላጊዎች በተጨማሪ 32ሺህ 630 የዋግኽራ ነዋሪዎች ተፈናቅለው በእብናትና በባሕርዳር አካባቢ ይገኛሉ።

ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ 
ነጋሽ መሐመድ