1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፣ የኢትዮጵያ ጦርነትና መዉጪያዉ ዘዴ

እሑድ፣ ነሐሴ 2 2013

ጦርነቱ ምንም ምክንያት ቢሰጠዉ የርስ-በርስ መሆኑ ሊያከራክር አይገባም።እርግጥ ነዉ የርስ በርሱ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት የመቀሌና የአዲስ አበባ ፖለቲከኞችን ለመሸምገል የሞከሩ ነበሩ።ዉጊያዉ ከተጀመረ በኋላ ግን ተፋላሚዎችን ለማደራደር ወይም ለመሸምገል የሞከረ  አንድም የሐገር ሽማግሌ፣ አንድም፣ የየትኛዉም የኃይማኖት አባት የለም።ካለም አልተሰማም።

https://p.dw.com/p/3yfS3
Äthiopien |  Demonstration von Unterstützern des Staudammprojekt GERD
ምስል Seyoum Getu/DW

ዉይይት፣ «ሐይ» ባይ ሽማግሌ እንዴት ጠፋ?

ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።ባለፈዉ ጥቅምት ማብቂያ ትግራይ ላይ የተጀመረዉ ጦርነት የሺዎችን ሕይወት ቀጥፏል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚነግረን ሚሊዮኖችን አፈናቅሏል፣ አሰድዷል፣ አስርቧልም።በደሐይቱ ሐገር ሐብት ንብረት ላይ ያደረሰዉ ጥፋት በቢሊዮን ዶላር ከመገመቱ ባለፍ ገና በቅጡ አልተጠናም።
ጦርነቱ ከሞት፣ ስደት፣ ረሐብ ያመለጠ የሚመስለዉን ግን ወትሮም በድሕነት የሚማቅቀዉን ኢትዮጵያዊ ኑሮ አናግቶታልም።ከየአካባቢዉ እንደምንሰማዉ ጦርነቱ በቀጥታም፣ በተዘዋዋሪም ባደረሰዉ ጫና ምክንያት የብዙ ሕዝብ መደበኛ ሥራ ታጉሏል።የምግብ፣ የማጣፈጪያና የመጠጥ ዋጋ አሻቅቧል።
የኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥት ከአንድ ወር በፊት የተናጥል ተኩስ አቁም ቢያዉጅም ዉጊያዉ ከትግራይ አልፎ ወደ አማራና አፋር ክልሎችም ተዛምቶ ሕይወት፣አካል፤ሐብት ንብረት እያጠፋ፣ ሠላማዊ ሰዎችን እያፈናቀለ ነዉ።ÄthiopieTigray
ተፋላሚ ኃይላትና ደጋፊዎቻቸዉ በየመገናኛ ዘዴዉ የገጠሙት አንዱ ሌላዉን «የማበሻቀጥ» ዘመቻ ከፕሮፓጋንዳ አልፎ ተራ ስድብ፣ በተፋላሚዎች ላይ ከማነጣጠር ዘልሎ በነፃ መገናኛ ዘዴዎችና የፖለተካ ተንታኞች ላይ ስም ማጥፋት ስድብና ማስፈራራት ላይ ደርሷል።
በዘፈቀደ የሚነዛዉ ስድብና ዛቻ የኢትዮጵያዉያንን ነባር ባሕል እንዴትነት፣ የዘመኑ ፖለቲከኞችና የየደጋፊዎቻቸዉን  ብስለት እስከየትነት እያጠያያቀ፣ ሕዝቡ ግራ እያጋባ እያሰጋም ነዉ።በረጅም ጊዜ ታሪኳ ለነፃነት የመስዋት ጀግንነትን ከመነጋገር ብልሐት፣ የመንግስታዊ አስተዳደር ሥርዓትን፣ ከሽምግልና ወግ የቀየጠ ባሕል አዳብራለች የምትባለዉ ኢትዮጵያ ዛሬ ዜጎችዋን የሚያረግፍ፤የሚያሰድድ፣ ለተመፅዋችነት የዳረገ ጦርነትን ማስወገድ አልቻለችም።
ጦርነቱ ምንም ምክንያት ቢሰጠዉ የርስ-በርስ መሆኑ ሊያከራክር አይገባም።እርግጥ ነዉ የርስ በርሱ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት የመቀሌና የአዲስ አበባ ፖለቲከኞችን ለመሸምገል የሞከሩ ነበሩ።ዉጊያዉ ከተጀመረ በኋላ ግን ተፋላሚዎችን ለማደራደር ወይም ለመሸምገል የሞከረ  አንድም የሐገር ሽማግሌ፣ አንድም፣ የየትኛዉም የኃይማኖት አባት የለም።ካለም አልተሰማም።ከሁለት ሳምንት በፊት «ጉዳዩ የሚያሳስበን ኢትዮጵያዉያን» ያሉ ወገኖች ተፋላሚዎች ተኩስ አቁመዉ እንዲደራደሩ የሚጠይቅ ሰነድ አሰራጭተዉ ነበር።የሰነዱ አዘጋጆች እራሳቸዉ እንዳሉት ስማቸዉን እንኳን በይፋ ለመናገር አልደፈሩም።
ምክንያታቸዉ ባንዱ ወይም በሌላዉ ወገን ወይም በየደጋፊዎቻቸዉ ላንዱ ወይም ለሌላዉ ትወግናላችሁ ከሚል ዉግዘት፣ስድብና ስም ማጥፋት ዉርጅብኝ ለመዳን ነዉ።የሰዎቹ ሥጋት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በኢትዮጵያዉያን መካከል ያሳደረዉን የመጠላላትና መጠፋፋት ደረጃን ለመረዳት ትንሹ ምሳሌ ነዉ።
ሰሞኑን ደግሞ ከካርቱምና ዋሽግተን እንደሰማነዉ አሜሪካኖች በእነአብደላ ሐምዶክ በኩል  የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችን ለማስታረቅ የመፈለጋቸዉ ዜና ሽዉ ብሏል።ግን ገና ደርዝ አልያዘም።
ናጄሪያዎችን፣ ሱዳኖችን፣ ኮንጎዎችን ስትሸመግል የኖረችዉ ኢትዮጵያ፤ ለኬንያ፣ ለደቡብ አፍሪቃ፣ ለዚምባቡዌ፣ለናሚቢያ ለሌሎችም የአፍሪቃ ሐገራት ሕዝብ ነፃነት የደከመችዉ ኢትዮጵያ ዛሬ የጦርነት የስደት፣ ረሐብ፣ የመጠላላት ሐገር ናት።የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች እራሳቸዉ ለፈጠሩት ችግር የዋሽግተን-ብራስልሶችን መፍትሔ ሲጠብቁ ዜጎቻቸዉ እያለቁ ነዉ።እስከመቼ? በዛሬ ዉይይታችን የሚያናነሳዉ ጥያቄ ነዉ።

Äthiopien Gedenken an den verstorbenen in Tigray
ምስል Solomon Muchie/DW
Äthiopien I Konfliktregion Tigray
ምስል Mahmoud Hjaj/AA/picture alliance

ነጋሽ መሐመድ