1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፤ የኢትዮጵያ የብር ለዉጥ ግሽበትንና የፖለቲካ አለመረጋጋትን ይታደግ ይሆን?

ሰኞ፣ መስከረም 11 2013

የገንዘብ ለዉጡ በተለይ የሀገርን ሀብት ባልተገባ መንገድ ወደ ግል ኪሳቸው በማስገባት በሙስና በርካታ ገንዘብ ያካበቱ ሰዎችን ኪስ የሚያደርቅ በመሆኑ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ብለዉ አብዛኞች ይህን የመንግሥት ርምጃ በይሁንታ ተቀብለዉታል። በሌላ በኩል ለርምጃዉ መንግሥት ዘግይቶአል ፤ ለምን አሁን ሲሉም ትችት የሰነዘሩ ጥቂቶች አይደሉም።

https://p.dw.com/p/3ikrS
Äthiopien Alte Banknoten werden verändert, um die Korruption zu bekämpfen
ምስል Privat

«ኢኮኖሚዉ እንዲረጋጋጋ ግን በቅድምያ ሃገሪቱ ዉስጥ የሚታየዉ የጎሳ ግጭት፤ ጥቃት በአፋጣኝ መቆም ይኖርበታል»

በያዝነዉ ሳምንት መጀመርያ መስከረም 4፣ 2013 ዓ/ም የኢትዮጵያ መንግሥት  የመገበያያ ብር ኖቶችን መቀየሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ይፋ አድርገዋል። አምስት ብርን ሳይጨምር በ  10፤ 50፤ እና  100 ብር ላይ የተደረጉት ለዉጦች ብሎም ይፋ ከሆነዉ አዲሱ 200 የብር ኖት ጋር  ተቀያሪዉ ብር በእኩል ደረጃ እስከ ሦስት ወራት ድረስ ያገለግላል ተብሎአል።  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ  95 በመቶ የሚሆነዉ አሮጌዉ ብር በአንድ ወር ጊዜ ዉስጥ መቀየር እንዳለበት መታሰቡን እና ከ 10 ሺህ ብር በላይ የያዘ ሰዉ የባንክ ሂሳብ ከፍቶ መቀየር እንዳለበት ተናግረዋል። አዲስ የታተመዉ ብር ከፍተኛ የደህንነት ማረጋገጫ የተካተተበት በመሆኑ ባንኮች ብሩን በመቀየር ሂደት ሃሰተኛ ብር እንዳይቀይሩ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ አጽኖት ሰጥተዉ አስጠንቅቀዋል። የብር ኖቶች መቀየራቸው በኢትዮጵያ የተስፋፋውን የህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ለመቆጣጠር ወሳኝ እርምጃ ነው ተብሎአል። ይህ ለዉጥ በተለይ የሀገርን ሀብት ባልተገባ መንገድ ወደ ግል ኪሳቸው በማስገባት በሙስና  በርካታ ገንዘብ ያካበቱ ሰዎችን ኪስ የሚያደርቅ በመሆኑ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ብለዉ አብዛኞች ይህን የመንግሥት ርምጃ በይሁንታ ተቀብለዉታል። በሌላ በኩል ለርምጃዉ መንግሥት ዘግይቶአል ፤ ለምን አሁን ሲሉም ትችት የሰነዘሩ ጥቂቶች አይደሉም። መንግሥት የኢትዮጵያን የመገበያያ ገንዘብ ለምን መቀየር አስፈለገዉ ? የብር መቀየር ለሃገሪቱ  የኤኮኖሚ ማንሰራራትም ሆነ ፖለቲካዊ መረጋጋት ያለዉ አንደምታ እና ፋይዳ ምን ይሆን ? በዚህ ርዕስ ላይ ሃሳባቸዉን እንዲያካፍሉን የጋበዝናቸዉ ፤ ዶክተር አጥናፉ ገብረመስቀል፤ የምጣኔ ኃብት ባለሞያ  በኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ማኅበር አባል እና የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መምህር ዶክተር እዮብ ተስፋዬ የማክሮ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ባለሙያው  እና  የንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀ–መንበር፤  መምህር ማረዉ አበበ  በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ  የፌደራሊዝም መምህርና በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ናሽናል ሚዲያ ሳፖርትን ከመሰረቱት አንዱ እንዲሁም  ሰለሞን ሙጬ የዶቼ ቬሌ ጋዜጠኛ ናቸዉ።

ሙሉ ዉይይቱን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!

 

አዜብ ታደሰ