1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፤ የአረቦች ዉዝግብ ዳፋ በአፍሪቃ ቀንድ

እሑድ፣ ሰኔ 18 2009

የቀጠር ጦር ከሥልታዊዉ የባብኤል መደብ መጋጠሚያ ላይ ከሰፈረ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አሰብ-ኤርትራ፤ በርበራ-ሶማሊላንድ ላይ ጦር ማስፈሯ ወይም ለማስፈር ማቀዷ ግን የቀጠር እርምጃ ከአፍሪቃዊቱ ኢትዮጵያ በላይ አረባዊቱን አቡዳቢን ማብሰልሰሉን ለመረዳት እስካለፈዉ ወር ማብቂያ ድረስ መጠበቅ ነበረብን።

https://p.dw.com/p/2fIV6
Arabische Liga Treffen Hauptsitz Kairo
ምስል Reuters

Diskussion forum (250617) - MP3-Stereo

ጤና ይስጥልኝ እንደምን ሠነበታችሁ።ለዛሬዉ ዉይይታችን «የአረቦች ዉዝግብ ተፅዕኖ በአፍሪቃ ቀንድ» የሚል ርዕስ ሰጥነዋል።በ2006 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያን መዉረሩን በመቃወም የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ እንዲወስን የጠየቀች አንዲት ሐገር ነበረች።ቀጠር።

የትንሺቱ ሐገርን ጥያቄ የሰማ እንጂ የተቀበላት ኃያል ዓለም አልነበረም።ይሁንና የመልከዓ ምድርና   የሕዝቧን ቁጥር ትንሽነት፤ የቴክኖሎጂ፤ የጦር፤ የፖለቲካ፤ የዲፕሎማሲ አቅሟን ደካማነት በክምር ሐብቷ ጡንቻዋ የምታካክሰዉ ሐገር የኢትዮጵያ መንግስት እንደ ጠላት የሚያያቸዉን መንግሥታት ወይም ቡድናትን መደገፏን አላቆመችም።

የኢትዮጵያ መንግሥት የቀጠርን ርምጃ በመቃወም ከሐገሪቱ ጋር የነበረዉን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በ2008 እስከ ማቋረጥ ደርሶ ነበር።በ2006 የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያ መዝመቱን ቀጠር ስትቃወም የተቀበላት እንዳልነበረ ሁሉ፤ በ2008 ኢትዮጵያ፤ ቀጠር «ከኤርትራ መንግሥት ጋር ካላት ጠንካራ ግንኙነት አልፋ፤ አሸባሪዎችንና ፅንፈኞችን ትደግፋለች» በማለት ሥትወነጅላት የአዲስ አበባን ሮሮ ከቁብ የቆጠረዉ አልነበርም።

Eritrea Präsident Isayas Afewerki
ምስል picture-alliance/dpa

እንዲያዉም ጊዜ፤ ጊዜን ሲሸረዉ ቀጠር ኤርትራና ኢትዮጵያን፤ ኤርትራና የጁቡቲን ሸምጋይ ሆና ብቅ አለች። ኤርትራን ከጅቡቲ ጋር ማስታረቁ በ2010 ሲሰምርላት አስመራ እና አዲስ አበባን ለማቀራረብ ያደረገችዉ ጥረት በጅምር ቀርቶ የጥበቀት ሚዛኑ ወደ አስመራ ቢደፋም ከሁለቱም ጋር የነበራት ግንኙነት ግን እስከያዝነዉ ወር ድረስ አልተስተጓጎለም ነበር።


 ቀጠር፤ ጅቡቲና ኤርትራን በሚያወዛግበዉ በራስ ዱሜራ ኮረብታና ደሴት ላይ ሠላም አስከባሪ ጦሯን ሥታሰፍር እርምጃዉ ከሁለቱ ሐገራት ቀጥሎ የሚመለከተዉ ኢትዮጵያን መሆኑን ለማወቅ  የፖለቲካ አዋቂ እማኝነት አያስፈልግም።የቀጠር ጦር ከሥልታዊዉ የባብኤል መደብ መጋጠሚያ ላይ ከሰፈረ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አሰብ-ኤርትራ፤ በርበራ-ሶማሊላንድ ላይ ጦር ማስፈሯ ወይም ለማስፈር ማቀዷ ግን የቀጠር እርምጃ ከአፍሪቃዊቱ ኢትዮጵያ በላይ አረባዊቱን አቡዳቢን ማብሰልሰሉን ለመረዳት እስካለፈዉ ወር ማብቂያ ድረስ መጠበቅ ነበረብን።የሪያድ፤ማናማ፤ አቡዳቢ እና የካይሮ ገዢዎች በቀጠር ላይ የጣሉት ማዕቀብና የሚሰነዝሩት ዉንጀላ ከነዳጅ ዘይት ከሚዛቀዉ ሐብታቸዉ የሚቆነጣጥርን እንዳሳሰበ ሁሉ፤ የአፍሪቃ ቀንድ መንግስታትን የኃይል አሰላለፍ ገለባብጦታል።በድንበር ግዛት ይገባኛል ሰበብ ጦር የተመዘዙት ኤርትራና ጀቡቲ ካስታራቂ፤ አደራዳሪ ምናልባትም ረጂያቸዉ ቀጠር ጋር የነበራቸዉን ጠብቅ ወዳጅነት ሠርዘዉ  የሳዑዲ አረቢያና የተባባሪዎችዋ ታማኞች ሆነዋል።

Präsident Ismail Omar Guelleh Dschibuti
ምስል picture-alliance/ dpa

ፑንትላንድ እና ሶማሊላንድ እንደ ኤርትራና ጅቡቲ ሳዑዲ አረቢያና ተከታዮችዋ የወሰዱትን እርምጃ ሲደግፉ፤ ሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክ፤ ኢትዮጵያና ሱዳን የኩዌይቱ አሚር የጀመሩትን ሽምግልና እንደሚደግፉ አስታዉቀዋል።የቀድሞ ወዳጆዋ ኤርትራና ጅቡቲ እንደከዷት የተረዳችዉ ቀጠር በሁለቱ ሐገራት ድንበር ያሰፈረችዉን ሠላም አስከባሪ ሠራዊቷን አንስታለች።የቀጠር ጦር የለቀቀዉን ሥፍራ የኤርትራ ጦር ተቆጣጥሮታል መባሉ ዉዝግቡን እንደገና ቀስቅሶ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት መነጋገሪያ ርዕስ እስከመሆን ደርሷል።

የአረቦቹ ጠብ ዳፋ በአፍሪቃ ቀንድ ሐገሮች ላይ የሚያደርሰዉ መዘዝ እስካሁን ካየንና ከሰማነዉም  ዉዝግብ፤መካሰስና መወነጃጀልም የከፋ ሊሆን ይችላል የሚሉ ብዙ ናቸዉ።እንዴት? በዉይይታችን ለመዳደስ እንሞክራለን።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ