1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ2013 ዕዉነትና የ2014 ተስፋ

እሑድ፣ መስከረም 2 2014

2013፣ ኢትዮጵያ ዉስጥ የጦርነት፣ የግጭት፣ የበሽታና  የተፈጥሮ መቅሰፍቶች ጥፋትና ዉድመት ከተመዘገቡባቸዉ ዘመናት አንዱ መሆኑ ብዙ አያጠያይቅም።የጎሳዎች ግጭት፣የፖለቲካ ሽኩቻና የስልጣን ሽሚያ በተለይ ሰሜን፣ሰሜን-ምዕራብና ምዕራብ ኢትዮጵያ ብዙ ሺዎችን የገደለ፣ሚሊዮኖችን ያፈናቀለና ብዙ ሚሊዮኖችን ለረሐብ ያጋለጠ ጦርነትና ጥቃት አስከትሏል

https://p.dw.com/p/40B7k
Äthiopien | Neujahrsfest | Shinoye Spiel
ምስል Seyoum Getu/DW

ዉይይት፤ ኢትዮጵያ በ2013 የታየባት ቀዉስ በ2014 ይቃለል ይሆን?

ጤና ይስጥኝ አድማጮች።ለዛሬዉ ዉይይታችን «የአሮጌዉ ዓመት ዕዉነታና የአዲሱ ዓመት ተስፋ በኢትዮጵያ» የሚል ጥልቅል ርዕስ ሰጥተነዋል።ኢትዮጵያ ብዙዎች እንደሚፅፉት ለሕዝቧ «አስደሳች» የሚባል ዘመን እንዳሳለፈች ሁሉ የረጅረጅም ጊዜ ታሪኳ በፈተና፣ መከራና መቅሰፍቶች የተሞላ ነዉ።አንዳዶች የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነት ታሪክ ነዉ እስከማለትም ይደርሳሉ።

አባባሉ እዉነትም ሆነ ሐሰት 2013፣ ኢትዮጵያ ዉስጥ የጦርነት፣ የግጭት፣ የበሽታና  የተፈጥሮ መቅሰፍቶች ጥፋትና ዉድመት ከተመዘገቡባቸዉ ዘመናት አንዱ መሆኑ ብዙ አያጠያይቅም።ከሐቻምና የተንከባለለዉ የጎሳዎች ግጭት፣የፖለቲካ ሽኩቻና የስልጣን ሽሚያ በተለይ ሰሜን፣ ሰሜን-ምዕራብና ምዕራብ ኢትዮጵያ ዉስጥ ብዙ ሺዎችን የገደለ፣ሚሊዮኖችን ያፈናቀለና ብዙ ሚሊዮኖችን ለረሐብ ያጋለጠ ጦርነትና ጥቃት አስከትሏል።

የአንበጣ ወረርሺኝ፣የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭትና የአየር መዛባት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያንን ኑሮ አናግቶ ገሚሱን ለተመጽዋችነት፣ የተቀረዉን ለስደት ዳርጓል።ግጭት፣ጦርነት በሽታና ወረርሺኙ አልበቃ ያለ ይመስል ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ ይኖሩና ይሰሩ የነበሩ ምናልባት በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ወደ ሐገራቸዉ እንዲመለሱ በመገደዳቸዉ ወይም በመታሰራቸዉ እራሳቸዉም፣ ቤተሰቦቻቸዉም ለችግር ተጋልጠዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ በ2012 ከድሕነት ጠገግ በታች ይሮር የነበረዉ ኢትዮጵያዊ 31 ሚሊዮን ነበር።የ2013ቱ ጦርነት፣ግጭት፣የአንበጣና የኮሮና ወርሺኝ፣መፈናቀልና መባረር ሲታከልበት ከድሕነት ጠገግ በታች የሚኖረዉ ሕዝብ ወደ 40 ሚሊዮን ይጠጋል ተብሎ ይገመታል።

በ2013 ከጥር እስከ መጋቢት በነበሩት ሶስት ወራት አስቸኳይ ሰብአዊ ርዳታ የሚያስፈልገዉ ኢትዮጵያዊ ቁጥር 23.5 ሚሊዮን ነበር።ዓመቱን የሸኘነዉ የርዳታ ፈላጊዉ ቁጥር የማየሉ፣ሰዎች በረሐብ የመሰቃየት-የመሞታቸዉን ዜና እየሰማን ነዉ።ኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳንን ከመሰሉ ጎረቤቶችዋ ጋር የገጠመችዉ ዉዝግብ የናረበት፣ አወዛጋቢ የድንበር ግዛትዋ በዉጪ ኃይል የተያዘበት፣ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላት ግንኙነት የሻከረበትም ዓመት ነበር።

በዚሕ ሁሉ ፈተና መሐል ግን ኢትዮጵያ በአብዛኛ ግዛቶችዋ ብሔራዊ ምርጫ አስተናግዳለች።በአዲሱ ዓመት አዲስ መንግስት ይመሰረታል ማለት ነዉ።የአምናን ዕዉነት በወፍ በረር ቃኝተን ዘንድሮን ለማማተር አንዲት ፖለቲከኛ፣ አንዲት ደራሲና አንድ የሐገር ሽማግሌ ጋብዘናል።

ነጋሽ መሐመድ