1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ወጣቶችን ከጎዳና ማንሳትና ፈተናው»

ዓርብ፣ ጥቅምት 7 2012

በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት የጎዳና ተዳዳሪዎችን በሙያ በማሰልጠን ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበትን መንገድ እያመቻቸ ይገኛል። አንዳንዶች ግን መልሰው የጎዳናውን ህይወት ተቀላቅለዋል። «ሰውን አሳ ማጥመድ እንዲችል ማሳየት ነው እንጂ እነሱን አሳ እየቀለበ የሚኖር ስርዓት የለም።» ይላሉ የዘርፉ ምክትል ስራ ኃላፊ አቶ አለሙ።

https://p.dw.com/p/3RUiI
Film Emra & Dabo
ምስል R&B RÄUBER & BANDITEN FILM

« ወጣቶችን ከጎዳና ማንሳት እና ፈተናው»

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኑሮዋቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ሰዎችን በተለይም ወጣቶችን በጀት መድቦ የማቋቋም ስራ እየሰራ እንደሆነ ይናገራል። ይህም ካለፈው ዓመት 2011 ዓ ም አንስቶ ተጠናክሮ እንደቀጠለ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አለሙ አሰፋ ይናገራሉ። « በአጠቃላይ እስከ 3500 ዜጎችን የማቋቋም ስራ ነው የተሰራው ከነዚህ መካከል 1400 የሚሆኑትን ከቤተሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ ተደርጓል።» አብዲ ፣በአዲስ አበባ ሰርቶ ለመኖር ከወሰኑት የጎዳና ተዳዳሪዎች መካከል አንዱ ነው። ወጣቱ ባለፈው ዓመት በመንግሥት ድጋፍ የሙያ ስልጠና አግኝቶ የስራውንም ዓለም ለአንድ ወር ያህል ተቀላቅሎ ነበር። ይሁንና ከወራት በኋላ ኑሮውን መልሶ ጎዳና ላይ አድርጓል። « ልብስ ስፌት ሰልጥኜ ነበር። ስልጠናው ግን እንደው አለፋችሁ እንድንባል ነው እንጂ ብቁ አላደረጉንም» ሲል ይተቻል።የ 26 ዓመቱ አብዲ መንግሥትን የሚወቅሰው ራሳችንን ለመቋቋም የሚሆነን በቂ ገንዘብ አልሰጠንም በሚል ነው።ከዚህ በተጨማሪም በቂ ስልጠና አለማግኘታቸውንም እንደ ችግር ያነሳል።  « መንግሥት ለመቋቋሚያ የሰጠን ገንዘብ ትንሽ ነው። ከ4000 ብሩ 3000ውን ከዛው ከመጠለያችን ሳልወጣ ነው የጨረስኩት። ለምንም ነገር አይሆንም»

Afrika Obdachlosigkeit  - Straßenkinder schlafen auf einer Fussgaengerbruecke in Addis Abeba
በየጎዳናው መንገድ ዳር የሚተኙ ወጣቶችምስል Imago/photothek

ዳንኤል ብለን የምንጠራው ወጣት እንደ አብዲ በልብስ ስፌት ሰልጥኖ አሁንም በስራ ላይ ይገኛል። ወጣቱ ለስድስት ወር እንደሰለጠነ ነው የነገረን። ይሁንና  መንግሥት በቅጡ አላቋቋመንም ሲል እሱም ይወቅሳል። « ከማሰልጠኛ ውጡና የራሳችሁን ቤት ተከራዩ ተባልን። 4000 ብሩ ለመቋቋሚያ በቂ አይደለም። ከምንኖርበት በጉልበት አስወጡን።»

የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አለሙ እንደሚያብራሩት ከሆነ ወጣቶቹ የተሰጣቸው መቋቋሚያ 4000 ብር ፣ሥራ ከጀመሩበት መሥሪያ ቤት ደሞዝ እስኪከፈላቸው ድረስ በቂ ነበር። « 4000 ብር የምንሰጣቸው እኛ መሠረታዊ የሆነውን የመቋቋሚያ ስራ ሰርተን ነው። ጥቅምት 1 የተቀጠረ የጎዳና ተዳዳሪ ደሞዝ የሚከፈለው ጥቅምት 30 ስለሆነ እስከዛው የሚበላው ነገር ስለማይኖረው፣ ለቤት ኪራይ፣ ለትራንስፖርት እና ለአልባሳት የሚሆን የመቋቋሚያ ፓኬጅ ነው።» ይላሉ አቶ አለሙ።

ዳንኤል በ800 ብር ቤት ተከራይቶ እንደሚኖር እና ለምግብ፣ ለትራንስፖርት እና ለሌሎች መሰረታዊ ነገሮች የሚተርፈው 400 ብር ብቻ እንደሆነ ገልፆልናል። በዚህ የተነሳም ወደ ጎዳና ህይወት እንዳይመለስ እሰጋለሁ ይላል። « ላለመውጣት እየሞከርኩ ነው። እኛም ጫፍ ላይ ነን። ፋብሪካ እየሰራሁ። ከጓደኞቼ ገንዘብ እየተበደርኩ ነው። ኑሮዬ እንደበፊቱ ነው። ምግብ እንኳን ከሆቴል እየለመንኩ ነው።»

አቶ አለሙ ወጣቶቹ ተከፈለን የሚሉትን ደሞዝም ያስተባብላሉ። ምንም እንኳን አብዲ እና ዳንኤል የተቀጠሩበት ደሞዝ ዝቅተኛ ከሚከፈላቸው የሙያ ዘርፎች ውስጥ ቢሆንም ሊሻሻል የሚችል እንደሆነ ያስረዳሉ። « በርግጥ የ2000 በታች የሚከፈላቸው አሉ። ይሔ ግን የመነሻ ደሞዝ ነው።  በዛ ላይ በቀን ስምንት ሰዓት ከሆነ የሚሰሩት አራት ሰዓት ጨምረው ደሞዛቸውም በዛ ልክ ያድጋል። »

Straßenkinder Äthiopien
ከዚህ በፊትም ኢትዮጵያ ውስጥ በግል እና በማህበር ተደራጅተው የጎዳና ተዳዳሪዎችን የመደገፍ ስራዎች ተካሂደዋልምስል Fruits of compassion

የጎዳና ተዳዳሪዎች የነበሩት ዳንኤልም ሆኑ አብዲ ከሱስ ነፃ ነን ይላሉ። ራሳቸውን ለማስተዳደርም ብቁ እንደሆኑ ይናገራሉ። መንግሥት እነዚህን ወጣቶች በሙያ ካሰለጠነ በኋላ ምን ያህል መርዳት ይገባዋል? ለረዥም ዓመታት በአዲስ አበባ ዮንቨርስቲ የሶይሶሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሆነው ያገለገለሉት ዶክተር የራስ ወርቅ አድማሴ ከአሁን በኋላ ያለው የወጣቶቹ ድርሻ ነው ይላሉ። « አንድ አቅሙ የደረሰ ሰው ኃላፊነት ይወስዳል። ሁልግዜ ለመወደድ መንግስት እንዲህ ማድረግ አለበት ማለት አያስፈልግም። መንግሥት  ይህን መስራት ከጀመረ ቆይቷል። » ዶክተር የራስ ወርቅ እንደሚሉት ሌላም ችግር አለ። « ብዙ በሱስ የተጠቁ ልጆች አሉ። እነዚህን ልጆች በማስገደድ ካልሆነ በስተቀር በፍቃደኝነት ሊተው አይችሉም።»

በዓለም ባንክ ድጋፍ በ2012 ዓ ም ከኢትዮጵያ 11 ከተሞች 22,000 የሚሆኑ የጎዳና ተዳዳሪዎችን የማንሳት እቅድ ተይዟል። ይህም በእነዚህ 11 ከተሞች ጎዳና ላይ ይኖራሉ ተብሎ ከተጠናው ኢትዮጵያዊ አንድ አራተኛ ያህል መሆኑ ነው። 13 000 ያህሉ ደግሞ ከአዲስ አበባ ከተማ እንደሚነሱ ተነግሯል።

ልደት አበበ

ሂሩት መለሰ