1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወደ አፍሪቃ የተመለሱ ቅርሶች ዳግም ላለመሰረቃቸዉ ምን ማስተማመኛ አለ?

ሐሙስ፣ ሐምሌ 7 2014

በቅኝ ግዛት ዘመን ከአፍሪቃ የተዘረፉ ቅርሶች ወደ የሃገራቸዉ ከተመለሱ በኋላ ደግመዉ ላለመዘረፋቸዉ አልያም ላለመዉደማቸዉ ምን ማስተማመኛ አለ? ባለፈዉ ሰሞን ጀርመን በቅን ግዛት ዘመን ከአፍሪቃ የተዘረፉ ከ 1000 በላይ ቅርሶችን እንደምትመልስ ማስታወቅዋ ይታወቃል። ለእርሶ ቅርስ ማለት ምን ማለት ነዉ? ለእርሶ ቅርስ ማለት ምን ማለት ነዉ?

https://p.dw.com/p/4E5iR
Geraubte Kulturgüter aus der Kolonialzeit
ምስል Daniel Bockwoldt/dpa/picture alliance

አፍሪቃ ዉስጥ ዳግም ቅርሱ ስላለመሰረቁ ምን ማስተማመኛ አለ?

  

በቅኝ ግዛት ዘመን ከአፍሪቃ የተዘረፉ ቅርሶች ወደ የሃገራቸዉ ከተመለሱ በኋላ ደግመዉ ላለመዘረፋቸዉ አልያም ላለመዉደማቸዉ ምን ማስተማመኛ አለ? በያዝነዉ ሳምንት ካሜሩናውያን በአንድ የጀርመን ሙዚየም ውስጥ ከ100 ዓመት በላይ የተቀመጡና ከካሜሩን የተዘረጡ ቅርሶችን ለመጀመሪያ ጊዜ በዓይናቸዉ አይተዋል። ባለፈዉ ሰሞን ጀርመን በቅን ግዛት ዘመን ከአፍሪቃ የተዘረፉ ከ 1000 በላይ ቅርሶችን እንደምትመልስ ማስታወቅዋ ይታወቃል። ካሜሩን በጀርመን ቅኝ ግዛት ስር ሳለች የተዘረፈዉ እና  ኮሎኝ ከተማ በሚገኘው ራውተንስትራሁ -ጆስት-በተባለ ሙዚየም ውስጥ ተቀምጦ የሚገኘዉ "ሌፌም" የተባለዉ በብረት የተሰራዉ ምስል ከካሜሩን ከተዘረፉት ቅርሶች መካከል አንዱ ነው። እነዚህ ወደ አፍሪቃ ሃገራት የሚመለሱ ቅርሶች እንደገና ከአፍሪቃ አለመዘረፋቸዉ ምን ያህል አስተማማኝ ነዉ? በአፍሪቃ ሙዝየም ዉስጥ ጥራታቸዉ ተጠብቆ መቀመጣቸዉስ ምን ያህል አስተማማኝ ነዉ?

Rautenstrauch-Joest-Museum | Köln, Deutschland
ምስል Alexandria Williams/DW

ጀርመን በተለያዩ ቤተ- መዘክሮቿ የሚገኙ እና በቅኝ ግዛት ዘመን ከቀድሞው የቤኒን ሥርወ መንግሥት ተዘርፈው የተወሰዱ ቅርሶችን ለመመለስ መስማማትዋን ተከትሎ፤ ዶ/ር ዮሐንስ ዘለቀ እጅግ አስደሳች ዜና ሲሉ ነዉ የገለፁት። ዶ/ር ዮሐንስ ዘለቀ በዋሽንግተን ዲሲ የሲምሶንያን የተፈጥሮ ሳይንስ ሙዝየም ተመራማሪ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል ናቸዉ።

Stiftung Preußischer Kulturbesitz l Nigerianische Delegation besucht Berlin
ምስል SPK/photothek.net/Florian Gaertner

ጀርመን በተለያዩ ቤተ-መዘክሮቿ የሚገኙ፣ በቅኝ ግዛት ዘመን ከአፍሪቃ ተዘርፈው የተወሰዱ ቅርሶችን ለመመለስ የተስማማችዉ ባለፈዉ ሰሞን ነበር። የጀርመን መንግሥት  የቤኒን ነሃሶች የሚል መጠርያ ያለዉን ወደ 1100 የሚጠጉ ከነሃስ እና ከተለያዩ የብረት አይነቶች፤ ከቀንድ እንዲሁም ከቆዳ የተሰሩት የናይጀሪያ ቅርሶችን በቀጥታ ለመመለስ ከናይጀሪያ መንግሥት ጋር ተስማምቷል፤ የመግባብያ ሰንድም በርሊን ላይ ተፈራርመዋል። በዋሽንግተን ዲሲ የሲምሶንያን የተፈጥሮ ሳይንስ ሙዝየም ተመራማሪ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል ዶ/ር ዮሐንስ ዘለቀ እንደሚሉት ይህ ለናይጀርያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪቃ ብሎም ለተዘረፉ ቅርሶች መመለስ ትልቅ ዜና ነዉ። ወደ ናይጀርያ ይመለሳል የተባለዉ ጥንታዊና በአሁኑ ወቅት የማይገኘዉ ቅርስ በቤኒን ሥርወ መንግሥት ዘመን የተሰራ የፊት ማስክ ወይም ጭንብል አይነት ቅርስ ነዉ ብለዋል።  

Äthiopien | Neu entdeckte prähistorische Stätte Yalda-Tuome in der Sonderzone Konso
ምስል Yohannes Zeleke/Addis Ababa University

ከአስር ቀናት በፊት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ፤ የጀርመን የባህልና የመገናኛ ብዙኃን ኮሚሽን ኮሚሽነር ክላውድያ ሮት፤ የናይጀሪያ የባህል ሚኒስትር፤ ላይ መሐመድና የናይጀሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ ዙባይሮ ዳዳ፤ በርሊን ላይ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል። ከመግባብያዉ ሰንድ ስምምነት በኋላ በርሊን ቤተ- መዘክር የነበሩ ሁለት በቤኒን ሥርወ መንግሥት ዘመን የተሰሩ የነሐስ ቅርሶች ለናይጀሪያ በቀጥታ ተሰጥተዋል። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ከርክክቡ ሥነ-ስርዓት በኋላ ባሰሙት ንግግር ለናይጀሪያ የተመለሱት እነዚሁ ሁለት ከነሐስ የተሰሩ ጥንታዊ ቅርሶች በጀርመን ከሚገኙት ከአንድ ሺህ በላይ ከሚሆኑት መካከል አንዱ ነዉ። ቅርሶቹ በጀርመን እጅ ገብተዉ ከ120 ዓመት በላይ መቀመጣቸዉ ስህተት ነበር ብለዋል። ቅርሱን ለመመለስ ስምምነት ላይ መደረሱን ደግሞ ታሪካዊ ሲሉ አወድሰዋል።

«ዛሬ ታሪካዊ ስምምነት ላይ ስለደረስን እለቱን የምናከብርበት ምክንያት አለን።እነዚህ ቅርሶች እጹብ ድንቅ ብቻ አይደሉም፤ከአፍሪቃ የተከበሩ ታላላቅ ሀብቶች ጥቂቶቹ ናቸው።የቅኝ ግዛት ጥቃት ታሪክንም የሚነግሩን ናቸው»

Deutschland | Ausstellung "I miss you" im Rautenstrauch-Joest-Museum in Köln
ምስል Annabelle Steffes-Halmer/DW

በጀርመን ቤተ-መዘክሮች ውስጥ የሚገኙትን የቤኒን ነሐሶችን ለመረከብ ወደ ጀርመን የመጡት የናይጀሪያ ቤተ- መዘክሮችና ጥንታዊ ቅርሳ ቅርሶች ብሔራዊ ኮሚሽን ሃላፊ አባ ኢሳ ቲጃኒ «ናይጀሪያ እና ጀርመን በፊርማ ያጸደቁት ስምምነት 1130 የሚሆኑት  ቅርሳ ቅርሶች ለባለቤታቸው ለናይጀሪያ የመመለሳቸው ይፋ ማረጋገጫ እና ታሪካዊ ብለውታል» «ርምጃዉ ለናይጀርያ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አፍሪቃ ሃገራት ታሪካዊ» መሆኑንም ተናግረዋል።

ባለፈዉ ዓመት የጀርመን እና የናይጀሪያ መንግሥታት እንዲሁም በጀርመን የቤተ- መዘክር ተወካዮች በ20 ቤተ- መዘክሮች ዉስጥ የሚገኙት ጥንታዊ የመዳብ ቅርሳ ቅርሶች ወደ ናይጀርያ እንደሚመለሱ ይፋ ማድረጋቸዉ የሚታወስ ነዉ። በዋሽንግተን ዲሲ የሲምሶንያን የተፈጥሮ ሳይንስ ሙዝየም ተመራማሪ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል ዶ/ር ዮሐንስ ዘለቀ እንደሚሉት፤ ከባለፉት 20 እና 30 ዓመታት ጀምሮ የተዘረፉ ቅርሶች ወደ መጡበት ሃገር እንዲመለሱ የተመ የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት፤ ዩኔስኮን ጨምሮ፤ የተለያዩ ዓለምአቅፍ ድርጅቶች መወትወት መጀመራቸዉን አስታዉሰዋል። የቤንኒ ነሐስ ቅርስ በቤኒን ሥርወ መንግሥት ወቅር በብዛት ይሰራ የነበረና፤ ከዝያ ዘመን ወድያ ያልተሰራ የማይገኝ ቅርስ መሆኑን ተናግረዋል። ይህ አይነቱ ቅርስ በተለይ በሩስያ ፤ በብሪታንያ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ይሁንና አፍሪቃ ሃገራት ቅርሱን ሲያስመልሱ ፤ ቅርሶቹ ተጠብቀዉ የሚቀመጡበት አመቺ ቦታ መዘጋጀት እንዳለበት፤ ብሎም የዓለም ተመራማሪዎች ጥናት እንዲad,ርጉ አመቺ ሁኔታ መዘጋጀት እንዳለበት አሳስበዋል።

Äthiopien | Neu entdeckte prähistorische Stätte Yalda-Tuome in der Sonderzone Konso
ምስል Yohannes Zeleke/Addis Ababa University

እንደ ዶ/ር ዮሐንስ ሁሉ የናይጀሪያዉ የቤተ- መዘክሮችና ጥንታዊ ቅርሳ ቅርሶች ብሔራዊ ኮሚሽን ሃላፊ አባ ኢሳ ቲጃኒ ሃገራቸዉ ቅርሶችን ስታስመልስ በጥንቃቄ ልታስብ የሚገባቸዉ ጉዳዮች እንዳሉ ጠቁመዋል። ይሁንና ሃገራቸዉ ናይጀርያ ለሁሉ ነገር ዝግጅትዋን ማጠናቀቅዋን ነዉ የተናገሩት።   

«እነደዚህ ዓይነት ቅርሶችን በቀጥታ ማዛወር ዝግጅት የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ብዙ ተያያዥ ጉዳዮች አሉ።ቅርሶቹን ለማጓጓዝ ፈቃደኛ የሆኑ ባለሞያዎች ያስፈልጋሉ።ከዚህ ሌላ ስለ መድን ዋስትና ኢንሹራንስም እንነጋገራለን። ስለ ጥበቃና ሌሎችም ጉዳዮች ትነጋገራለህ አስተሻሸግም እንዲሁ። ይህ በአንድ ለሊት የሚያልቅ ሳይሆን ጊዜ የሚወስድ ሂደት ነው። ስለዚህ እነዚህ ቅርሶች በጥንቃቄ ባለሞያዎች በሚሰጡት አስተያየት መሠረት ወደ ናይጀሪያ  እንዲመለሱ ይደረጋል። ናይጀሪያም ቅርሶቹን ለመቀበል ዝግጁ ናት።  የቅርሶቹ ማከማቻ እና ማሳያ ስፍራዎች ቅርሶቹ ከመሄዳቸው በፊት ተዘጋጅተዋል። »

Deutschland | Ausstellung "I miss you" im Rautenstrauch-Joest-Museum in Köln
ምስል Annabelle Steffes-Halmer/DW

ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያን ጥቅምት ወር እንጊሊዝ ከ 100 ዓመት በፊት ከናይጀሪያ የዘረፈቻቸውን ቅርሶችን መመለስዋ ተዘግቦአል። ቅርሶቹ ተዘርፈው ከተወሰዱ በኋላ ወደ በብሪቲሽ ሙዚየም ውስጥ የቆዩ ነበሩ። የቤኒን ስርወ መንግስት ከመዳብ የተሰሩ ቅርሶች በአሁኑ ወቅት በደቡብ ምዕራብ ናይጀሪያ በሚገኘዉ በቤኒን ባህላዊ ቤተ መንግስት መመለሳቸዉን ሮይተርስ ዘግቧል። በርካታ የአፍሪቃ አገራት በቅኝ ግዛት ጊዜ በአውሮጳዊያን የተዘረፉባቸውን ቅርሶች ለማስመለስ በጥረት ላይ ይገኛሉ። 90 በመቶ የሚሆነው የአፍሪቃ ቅርሶች አሁንም በአውሮጳ እንደሚገኙ ይነገራል። ፈረንሳይ እና እንጊሊዝ በአንጻራዊነት ብዙ የአፍሪቃ ቅርሶች የሚገኙባቸው አገራት መሆናቸዉን የቅርስ ጉዳይ ምሁራን ይናገራሉ። የአፍሪቃ ቅርሶችን የያዙ ምዕራባዉያን ሃገራት ይህንን ቅርስ ወደ መገኛቸዉ ሃገራት የመመለሳቸዉ ተስፋ ትልቅ መሆኑን ዶ/ር ዮሐንስ ዘለቀ ተናግረዋል።

ቅርስ የአንድን ሃገር ታሪክን ባህልን ጠንቅቆ ወይም አቅፎ ከዘመን ዘመን የሚያሸጋግር ሰነድ ነዉ ሲሉ የተናገሩት ዶ/ር ዮሐንስ ዘለቀ፤ ቅርሱ በተገኘበት ሃገር የሚኖር ማኅበረሰብ፤ ዋጋ የከፈለበት የታሪክ የባህሉ አሻራ ያረፈበት ሰነድ መሆኑን አብራርተዋል። የአንድን ሃገር ቅርሱ ታሪኩ ሲዘረፍ፤ የራሱ የሆነዉ አሻራ ሲወሰድበት የኔነዉ የሚለዉ ነገር የሚያሳጣ በመሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ ቅርሱን ባህሉን የመጠበቅ ሃላፊነት እንዳለበት ምሁራን ይመክራሉ።

ሙሉዉን ዝግጅት የድምፅ መያዣ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ