«ወደ ትግራይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ ተደርጎአል የሚለዉ ክስ ተቀባይነት የለዉም» መንግሥት
ሰኞ፣ ጳጉሜን 1 2013ማስታወቂያ
መንግሥት ወደ ትግራይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ ክልከላ እያደረገ ነው የሚለው ክስ ተቀባይነት የለውም ሲል የሰላም ሚኒስቴር ተናገረ። መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ሲያደርግ ለትግራይ ሕዝብ የአንድ ወር፣ረጂ ድርጅቶችም የአንድ ወር በአጠቃላይ የሁለት ወር ምግብ አስቀምጦ መውጣቱን የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ዛሬ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
በተጨባጭ ለህወሓት ምሣሪያ ፣ መድኃኒት እና ምግብ የሚያቀርቡ ድርጅቶች በመገኘታቸው መንግሥት ሁለት ዘመናዊ የተሽከርካሪ መፈተሻ ማሽኖችን መትከሉንም ገልፀዋል። ሆኖም ሰባት የነበሩት የፍተሻ ኬላዎች ወደ ሁለት ዝቅ መደረጋቸውንም ትናግረዋል።
ወደ ክልሉ እስካሁን 538 ተሽከርካሪዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ጭነው መጓዛቸውን፣ ያም ሆኖ ግን 72 በመቶው ወደ ትግራይ የተጋዙት ተሽከርካሪዎች አለመመለሳቸው ይህም አሳሳቢ መሆኑን ገልፀዋል።
ህወሓት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በከፈተው ጥቃት 4.5 ሚሊዮን ዜጎች ለችግር እንደተጋለጡ የተናገሩት የሰላም ሚኒስትሯ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ወደ እነዚህ ክልሎች የሚቀርበው ሰብዓዊ ድጋፍ በቂ አይደለም ብለዋል።
ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀም የህወሓት ተፈጥራዊ ባህርይ ነው ሲሉም ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ተናግረዋል።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ