1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወደ ትምህርታቸው የማይመለሱ ቅጣት ይጠብቃቸዋል

ዓርብ፣ ኅዳር 12 2012

የኢትዮጵያ ሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ተፈጥሮ በነበረው ግድያና ውድመት ወቅት ወንጀል የፈጸሙሩ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ አደርጋለሁ አለ። ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ ከሳምንታት ነውጥ በኋላ በዳግም ምዝገባ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገባታቸው ለመመለስ መዘጋጀታቸውን እየገለጹ ነው።

https://p.dw.com/p/3TZEx
Karte Sodo Ethiopia ENG

ወንጀል የፈጸሙሩ አካላት በሕግ ይጠየቃሉ

ባለፉት ሳምንታት መረጋጋት ባልታየባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ተፈጥረው በነበሩ የሞት ፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት በአስተዳደራዊ እና በወንጀል እንደሚጠየቁ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል። በተጨማሪም፦ የተማሪዎችን ግጭት ካስተናገዱ ዩኒቨርሲቲዎች ተጠቃሾቹ የጅማ እና የደሴ ዩኒቨርሲቲዎች ለዳግም ምዝገባ በተቀመጠ የጊዜ ገደብ ወደ ትምህርት ገበታቸው የማይመለሱ ተማሪዎችን ሴኔቶቻቸው በሚወስኗቸው የአስተዳደራዊ ውሳኔዎች እርምጃ እንደሚወስዱ ገልጸዋል። በጅማ ዩኒቨርሲቲ ለሳምንታት ከሰነበተ አለመረጋጋት በኋላ ተማሪዎችን በዳግም ምዝገባ ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ የሚያስችል ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል አባ ፊጣ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።
“ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ ማስኬድ የሚያስችሉ ኹኔታዎች በመፈጠራቸው እና ሰፊ የውይይት መድረኮችን አካሂደን ኹኔታዎች ስለተመቻቹ እና የደህንነት ዋስትናው ስለተሻሻለ ትምህርት ለመጀመር ቅዳሜ እና እሑድ ምዝገባ ተካሂዶ ሰኞ ትምህርት ይጀመራል።“ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተፈጥሮ በነበረው በዚሁ አለመረጋጋት ምክንያት ከዩኒቨርሲቲው ርቀው የሄዱ ተማሪዎች በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ወደ ትምህርት ገበታቸው የማይመለሱ ተማሪዎችን የዩኒቨርሲቲው ሴኔት በወሰነው መሰረት አስተዳደራዊ ርምጃ እንደሚወስድ ዶክተር ጀማል አስረድተዋል።
“ በእኛ በኩል ገና ስለኾነ የወሰድነው እርምጃ የለም። የዩኒቨርሲቲው ሴኔት የራሱ አሰራር አለው። በዚያን ጊዜ የማይመለሱ ተማሪዎች ካሉ በአሰራሩ መሰረት እርምጃ መውሰዱ አይቀርም። “ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በዳግም ምዝገባ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የተቀመጠውን አቅጣጫ በዩኒቨርሲቲው ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ተግባራዊ እንደሚሆን የተናገሩት ደግሞ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን ናቸው። ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ስራውን ከማስጀመሩ በፊት በተማሪዎች መካከል እረቀ ሰላም መፍጠር ቀዳሚ ተግባራቸው መሆኑን ዶክተር አባተ ገልጸዋል። “ በየቡድን እያወያየን አራተኛ መድረካችንን ትናንት አካሂደናል። ጥዋት ላይ ከኦሮሚያ ልጆች ጋር ከሰዓት በኋላ ከአማራ ልጆች ጋር ውይይት አ,ድርገን ሁለቱም ተስማምተዋል። እርቁን ማታ አካናወን። ስታቀራርባቸው እየተላቀሱ ሲሳሳሙ ያልተለያዩ አሉ አሁንም ።“
በሀገሪቱ በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ለተፈጠረው የሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት በወንጀል እና አስተዳደራዊ ኃላፊነት ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት ደግሞ ለሕግ እንደሚቀርቡ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ጉርሙ እንዳሉት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ችግሮችን በትዕግስት የሚያይበት ወቅት አልፏል። “አብዛኞቹ ተማሪዎች ትምህርት ይፈልጋሉ፤ የተወሰኑት ተማሪዎች ደግሞ ይረብሻሉ፤ ስለዚህ የሚረብሹ እና ጥፋት ያለባቸውን ለይቶ መዳኘት ያስፈልጋል።  አስተዳደራዊም ይሁን ወንጀል የሰሩትን በወንጀል ህግ መጠየቅ አለባቸው“ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከህዳር 11 ቀን፣2012 ዓ.ም ጀምሮ ችግር የሚታይባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ሚኒስቴር ዲኤታው ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ዐስታውቀው ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት ሐሙስ ህዳር ቀን፣2012 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለተወሰነ ጊዜ የቆየ አለመረጋጋት ተከስቶ እንደነበር ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

ታምራት ዲንሳ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ