1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ወንዞችን ከቡና ተረፈ ምርት ብክለት መከላከያ ዘዴ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 13 2014

አቶ አመለወርቅ አሁን ሳይንሳዊ መፍትሔ እየተገኘለት ነው የተባለው የቡና ተረፈ ምርት እያስከተለ የሚገኘው ጉዳት ከፍተኛና አሳሳቢም ነው ይላሉ ፡፡ለወንዞች ብክለት መንስኤ የሆነውን የቡና ገለፈት በሳይንሳዊ መንገድ በማከምና ወደ ጤናማ የውሃ አካላት በመቀላቀል የተካሄደው ምርምር ውጤት ማስገኘቱን ተመራማሪ ዶ/ር ምህረት ይናገራሉ፡፡

https://p.dw.com/p/44iy2
Äthiopien Vermeidung von Umweltverschmutzung durch Kaffee-Nebenprodukte
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ወንዞችን ከቡና ተረፈ ምርት ብክለት መከላከያ ዘዴ

የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት በኢትዮጵያ ለአገር ውስጥ ፍጆታና ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የቡና ምርት ፈልፍሎ ለማዘጋጀት ከፍተኛ የውሃ አቅርቦት ይጠይቃል፡፡ በዚህም የተነሳ የሲዳማና የደቡብ ክልሎችን ጨምሮ በበርካታ የአገሪቱ ቡና አምራች አካባቢዎች የሚገኙ የቡና መፈልፈያ ድርጅቶች በቀላሉ ውሃ በሚያገኙባቸው የወንዝ ዳርቻዎች ላይ እንዲመሠረቱ አስገድዷቸዋል፡፡ ይህ ታዲያ የመርዛማነት ባህሪ ያለውና ከእሸት ቡና የገለፈት ተረፈ ምርት የሚወጣው ልጋግ በቀጥታ ወደ ወንዞች ስለሚለቀቅ ለብክለት እየዳረጋቸው ይገኛል፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች እንዳረጋገጡት የቡናው ገለፈት ልጋግ የወንዝ ውሃ በውስጡ ያለውን ንጥረ ነገራዊ ወይም ኬሚካላዊ ይዘት ያዛባዋል፡፡ ይህም ወንዙን በሚጠቀሙ ሰዎች እንዲሁም በቤትና በዱር እንስሳት ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል ይላሉ ባለሙያዎቹ ፡፡ በዚሁ የወንዞች ብክለት ዙሪያ የመፍትሄ አማራጮችን ሲያፈላልጉ የቆዩት የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች የቡና ተረፈ ምርቱን በሳይንሳዊ መንገድ ለማከም ያደረጉት ምርምር አሁን አሁን ውጤት እያስገኘላቸው የመጣ ይመስላል ፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የቴክኖሎጂ ተቋም መምህራን ተመራማሪ እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጱያ ስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ ጥናትና ምርምር ማዕከል አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር ምህረት ዳናቶ የምርምር ሥራው የተካሄደው በሲዳማ ክልል ዳሌ ወረዳ በሚገኘው የጊዳቦ ወንዝ ተፋሰስ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የምርምር ቡድኑ ለችግሩ ሳይንሳዊ መፍትሔዎች ከማፈላለጉ አስቀድሞ የቡና ተረፈ ምርቱ በወንዙ ላይ በምን መልኩ ጉዳት ያደርሳል የሚለውን የመለየት ሥራ ማከናወኑን ዶ/ር ምህረት ይናገራሉ፡፡
በጉዳቱ ስፋትና በችግሩ መንስኤ ላይ በተካሄደው የክትትል ሥራም ለወንዝ ውሃ መጎዳት ዋነኛው ምክንያት በሳይንሳዊ ሥያሜው ቤክት የተባለው ከእሸት የቡና ፍሬ ውስጥ የሚገኘው ልጋግ መሆኑን ለማረጋገጥ መቻሉን ነው ዶ/ር ምህረት የገለፁት ፡፡
አቶ አመለወርቅ ገብሩ ለበርካታ ዓመታት በአካባቢ ጥበቃ ባለሙያነት ያገለገሉና ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በአካባቢ ጥበቃ ዳይሬክቶሬት በዳይሬክተርነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ አቶ አመለወርቅ አሁን ሳይንሳዊ መፍትሔ እየተገኘለት ነው የተባለው የቡና ተረፈ ምርት እያስከተለ የሚገኘው ጉዳት ከፍተኛ ፣ ችግሩም አሳሳቢ ነው ይላሉ ፡፡
ለወንዞች ብክለት መንስኤ የሆነውን የቡና ገለፈት በሳይንሳዊ መንገድ በማከምና ወደ ጤናማ የውሃ አካላት እንዲቀላቀል በማድረግ የተሠራው ምርምር ውጤት ማስገኘቱን የሀዋሣ ዩኒቨርስቲው ተመራማሪ ዶ/ር ምህረት ይናገራሉ ፡፡
በእርግጥ አንድ የምርምር ቴክኖሎጁ ውጤታማ ፣ ተደራሽና ተገልጋዩ በተመጣጣኝ ወጪ ሊጠቀምበት የሚያስችል መሆን እንዳለበት ይታመናል፡፡ በዚህ ረገድ የቡና ተረፈ ምርትን የማከሙ ቴክኖሎጂ እነኚህን መመዘኛዎች ያሟላ ስለመሆኑ ነው ዶ/ር ምህረት ያረጋገጡት ፡፡
በሀዋሣ ዩኒቨርስቲ የተገኘው ምርምር የቡና ተረፈ ምርት በአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ያስችላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው የአከባቢ ጥበቃ ባለሙያዎ አቶ አመለወርቅ ገብሩ ይናገራሉ፡፡
ይሁንእንጂ ምርምሩ መገኘቱ ብቻ በራሱ ውጤታማ አያደርገውም የሚሉት አቶ አመለወርቅ መደረግ ቴክኖሎጂው ቶሎ ወደ ሥራ የሚገባበት ሁኔታ መመቻቸት እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡
በሀዋሣ ዩኒቨርስቲ ተማራማሪዎች የተገኘው የቡና ተረፈ ምርትን የማከም የምርምር ሥራ በየጊዜው የሚሻሻልና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎችም ሊተገበር የሚችል ነው በማለት ዶ/ር ምህረት መንግሥት ሥራው የጋን ውስጥ መብራት እንዳይሆን ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልበትን መንገድ ጠቁመዋል።

Äthiopien Vermeidung von Umweltverschmutzung durch Kaffee-Nebenprodukte
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW
Äthiopien Vermeidung von Umweltverschmutzung durch Kaffee-Nebenprodukte
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ኂሩት መለሰ