1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወቅታዊዉ ግጭትና የደም ልገሳ

ሰኞ፣ መስከረም 14 2011

በተለያዩ አካባቢዎች  በተፈጠረዉ ግጭት ሳቢያ የደም እጥረት እያጋጠመ መሆኑን ብሄራዊ የደም ባንክ አገልግሎት አስታወቀ። በግጭቱ  ደም የሚያስፈልጋቸዉ ተጎጅዎች  መበራከት እንዲሁም   መደበኛዉ  የደም ልገሳ ተግባር መስተጓጎል  ለእጥረቱ  ምክንያቶች መሆናቸዉ ተጠቅሷል።

https://p.dw.com/p/35Q2o
Frankreich Zentrum für Blutspenden in Paris
ምስል Getty Images/AFP/M. Berard

24 የደም ባንኮች አሉን

በኢትዮጵያ ደም የመለገስ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም አገልግሎቱን ከሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር አንፃር ተመጣጣኝ አለመሆኑን ነዉ የኢትዮጵያ የብሄራዊ የደም ባንክ የለጋሾች አገልግሎት ማስተባበሪያ ሀላፊ ሲስተር አበባ ኃይለ መለኮት ለDW የገለፁት። በተለይ ደግሞ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰተ ባለዉ ግጭት የተጎዱ ሰዎች ደም የሚያስፈልጋቸዉ ቢሆንም ተንቀሳቅሶ ለመስራት ግን ሁኔታዉ አመቺ አለመሆኑን ነዉ ያብራሩት።

በአሁኑ ወቅት በመስሪያ ቤታቸዉ ከአራቱ የደም አይነቶች 1,400 ዩኒት የሚጠጋ የመጠባበቂያ ደምና ወደ 300 የሚሆኑ ለስርጭት ተዘጋጅተዉ የተቀመጡ የደም ከረጢቶች መኖራቸዉን ሲስተር አበባ ገልፀዉ ፤ ቢሆንም ግን አገልግሎቱን ከሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር አንፃር ያለው ተመጣጣኝ አለመሆኑን አስረድተዋል።

Ministerpräsident Abiy Ahmed Äthiopien spendet Blut
ምስል Prime Minister Office/F. Arega

«24 የደም ባንኮች አሉን።አሁን ወደ 40 እያደጉ ነዉ።በጣም ብዙ ማህበረሰብ ነዉ የምናገለግለዉ።ለኢትዮጵያ በሙሉ።ስናስበዉ እያሰባሰብን ያለነዉ ደምና እየደረሰዉ ያለዉ ሰዉ የሚመጣጠን አይደለም።ኢትዮጵያ ዉስጥ በአጠቃላይ በአመት 84 ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰብ አለብን። ያለፈዉ ዓመት ራሱ ያለን «ፐፎርማንስ» 53 ሺህ አካባቢ ነዉ።ስለዚህ አይመጣጠንም።የሚፈለገዉ ደምና እኛ እየቀዳን ያለነዉ ደም አይመጣጠንም»ብለዋል።

እንደ ኃላፊዋ ከ90 በላይ ለሆኑ የጤና ተቋማት በቋሚነት ደም የሚያከፋፍለዉ ብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት፤  ከ250  እስከ 300 ከረጢት ደም በየቀኑ ማቅረብ ይጠበቅበታል። ይህንን የደም አቅርቦት  ለማሟላትም ከማዕከልና ከተንቀሳቃሽ የልገሳ ማዕከሎች፤  ቢያንስ በአመት  ወደ 2500 ከረጢት የመጠባበቂያ ክምችት ያስፈልገዋል። ያምሆኖ ግን በአሁኑ ወቅት ከሚያስፈልገዉ መጠን ሁለት ሶስተኛዉ  ብቻ ነዉ በባንኩ የሚገኘዉ። ለዚህም ከወቅታዊዉ ሁኔታ በተጨማሪ ኅብረተሰቡ ያለዉ የደም ልገሳ ባህልና የመስሪያ ቤቱ  የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ አስተዋፅኦ  ሊኖረዉ እንደሚችል ኃላፊዋ ገልፀዋል። ችግሩን ለመፍታትም እየተሠራ ነዉ ብለዋል።
የደም ልገሳ አርአያነትን የሚፈልግ ተግባር በመሆኑም ታዋቂ ሰዎች በተለይም የጥበብ ሰዎች ሰርተዉ በማሳየት ቀዳሚ እንዲሆኑ አሳስበዋል።  ስራዉ በአንድ ጊዜ ዘመቻ የሚቆም ባለመሆኑም ቀጣይነት ባለዉ መልኩና በየሶስት ወሩ ደም በመለገስ ወገናቸዉን እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል። 
ባለፈዉ ሰኔ 16 ቀን 2010 አ/ም በመስቀል አደባባይ በደረሰው ቦምብ ፍንዳታ ለተጎዱ ሰዎች ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድን ጨምሮ በርካታ የመንግሥትና የግል ተቋማት ሠራተኞችና እንዲሁም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የደም ልገሳ ማድረጋቸዉ ይታወሳል ።

Wissenschaft Medizin Kühlung
ምስል imago/Westend61

 

ፀሐይ ጫኔ

ሽዋዩ ለገሠ