1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወልድያ በመድፍ ተመታች

ሰኞ፣ ነሐሴ 3 2013

የአማራ ክልል መንግስት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ እንዳሉት ህወሓት ትናንት ምሽት በወልዲያ ከተማ ላይ ሁለት መድፎችን ተኩሶ በንፁሐን ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ የተናጠል ተኩስ አቁም ከታወጀ በኃላ በአማራ ክልል ሰሜናዊ አካባቢዎች ውጊያ በመቀጠሉ 250ሺህ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

https://p.dw.com/p/3ylOT
Äthiopien Gizachew Muluneh General Director Amhara Communication Office Bahar Dar
ምስል Alemenew Mekonnen/DW

«ከተኩስ አቁም ወዲህ 250 ሺህ ሰዎች ተፈናቀሉ»የአማራ ክልል

ህወሓት በወልዲያ ከተማ ላይ ትናንት ምሽት መድፍ መተኮሱን የአማራ ክልል አስታውቋልግጭት በሚካሄድባቸው የአማራ ክልል ሰሜናዊ አካባቢዎች የተፈናቃዮች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱን የአማራ ክልል መንግስት አስታውቋል። ተፈናቃዮቹ ዘመዶቻቸውጋና በመጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙና የእለት እርዳታ እየቀረበላቸው እንደሆነም ገልጿል፡፡ በደሴ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች የእለት እርዳታ ሊሰጣቸው መሆኑን ገልፀዋል። የአማራ ክልል መንግስት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ እንዳሉት ህወሓት ትናንት ምሽት በወልዲያ ከተማ ላይ ሁለት መድፎችን ተኩሶ በንፁሐን ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ መንግስት የተጠናጠል ተኩስ አቁም አድርጌያለሁ ካለ ጊዜ ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜናዊ አካባቢዎች ውጊያ በመቀጠሉ በርካታ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የክልሉ መንግስት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡ የጽ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ እንደገለፁት ባለፉት ሶስት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች በነበሩ ግጭቶች 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የክልሉ ተወላጅ ዜጎች መፈናቀላቸውን አስታውሰው የተናጠል ተኩስ አቁም ከታወጀ በኃላ ብቻ 250ሺህ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና፣ ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ማስተባበሪያ ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ እታገኘሁ አደመ በበኩላቸው በጦርነቱ ምክንያት በላሊበላ፣ በግዳን፣ በአላማጣ፣ በዋጃ፣ በባላ፣ በቆቦ፣ በወልዲያ፣ በሀብሩ፣ በአበርገሌ፣ በኦፍላ፣በኮረምና ጠለምት አካባቢዎች በርካታ ነዋሪዎች መፈናቀለቸውን ለዶይቼ ቬለ አብራርተዋል፡፡ አብዛኛው ተፈናቃይ በየዘመዱ መጠጋቱን የጠቀሱት ወ/ሮ እታገኘሁ፣ ዘመድና መጠጊያ የሌላቸው ደግሞ በመጠለያ ውስጥ እንዲገቡ መደረጉንና ርሳቸውን ጨምሮ ከፌደራልና ከክልል ጉዳዩን የሚከታተል ቡድን መቋቋሙንና ተፈናቃዮችን ለማገዝ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ምክትል ኮሚሸነሯ አስረድተዋል፡፡ የመርሳና የወልዲያን ተፈናቃዮች አስተያየት ለማካተት ስልክ መስራት ባለመቻሉ ዶይቼ ቬለ ባይሳካለትም  ደሴ ከተማ ከደረሱት ተፈናቃዮች መካከል ሁለቱ እርዳታ ለማግኘት ምዝገባ ማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡

 ዓለምነው መኮንን

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ