1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮቪድ19ኝ የመከላከሉ ዘመቻ ጥቀመ ወይስ ጎዳ

እሑድ፣ ሚያዝያ 25 2012

የኮቪድ 19ኝ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት በተለይ በሕዝቡ ኑሮ ላይ ያሳደረዉ ኪሳራ ወይም ተፅዕኖ በዉል አልተጠናም።ከሐዋሳ ሐይቅ ዳርቻ እስከ አክስም ታሪካዊ ስፍራዎች ኦና ከቀሩ ግን ሁለት ወር ሊሆናቸዉ ነዉ።ሆቴሎች፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ መድብሮች፣ ተከርችመዋል።

https://p.dw.com/p/3bfG5
Äthiopien Jahrestag Absturz Boeing 737 max 8
ምስል DW/S. Muchieu

ኮቪድ 19 የመከላከሉ እርምጃ ጥቅምና ጉዳቱ

የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት በኢትዮጵያዉያን ላይ ያደረሰዉ የኑሮ ቀዉስ የዛሬ ዉይይታችን ትኩረት ነዉ።የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት  ወይም የኮቪድ 19 ወረርሺኝ ሚሊዮኖችን ከማሳመም፣ መቶ ሺዎችን ከመግደሉ ሌላ የዓለምን ሁለንተናዊ ሥርዓት አናግቶ የቢሊዮነ ቢሊዮንትን ኑሮ እና አኗኗር አሳክሮታል።

ገበሬዉ የእርሻ ምርቱን ባለኢንዱስትሪዉ የፋብሪካ ዉጤቱን፣ ነጋዴዉ ሸቀጡን፣ ወይም አገልግሎቱን ለየተጠቃሚዉ ማቅረብ፣ ተጠቃሚዉም የሚፈልገዉን ማግኘት አልቻሉም።የዓለም አቀፍ የገንዘብና የስራ ተቋማት ዘገቦች እንደሚጠቁሙት ዓለም በትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢ እያጣች ነዉ።የዓለም የሰራተኞች ድርጅት (ILO) እንዳለዉ ደግሞ ከዓለም ሠራተኛ ኃይል ግማሽ ያሕሉ ወይም መደበኛ ባልሆነ ሥራ ላይ የተሠማራዉ  1.6 ቢሊዮኑ ሠራተኛ ኑሮዉ ክፉኛ ተናግቷል።

አፍሪቃ እስካሁን በተሕዋሲዉ የተለከፈ ወይም በበሽታዉ የሞተባት ሰዉ ቁጥር ከአብዛኛዉ ክፍለ-ዓለም ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነዉ።ይሁን እንጂ ወትሮም በእርሻ ምርት፣ በዕለት ሽቀላ፣ በአገልግሎት፣ በብድርና ርዳታ ላይ የተመሰረተዉ ምጣኔ ሐብቷ ክፉኛ እየተንኮታኮተ ነዉ።

ኢትዮጵያ ክፉኛ ከተጎዱና ከሚጎዱ ሐገራት አንዷ ናት። የዓለም ምግብ ድርጅት WFP የበላይ ኃላፊ ዴቪድ ቤስሌይ ባለፈዉ ሳምንት ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት እንደነገሩት ወትሮም ግጭት፣ ድርቅ፣የአንበጣ መንጋ ሚሊዮኖችን ለረሐብ ያጋለጠባት ኢትዮጵያ አሁን ደግሞ በኮቪድ19 ወረርሽኝ ምክንያት የሰዎች እንቅስቃሴ በመታገዱ፣ ሥራ በመቆሙ፣ ከዉጪ የሚላከዉ ገንዘብ (ሪሚታንስ) በመቀነሱ እና ሐገር ጎብኚ ባለመኖሩ ሚሊዮኖች ለከፋ ችግር ተጋልጠዉባታል።

የኮቪድ 19ኝ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት በተለይ በሕዝቡ ኑሮ ላይ ያሳደረዉ ኪሳራ ወይም ተፅዕኖ በዉል አልተጠናም።ከሐዋሳ ሐይቅ ዳርቻ እስከ አክስም ታሪካዊ ስፍራዎች ኦና ከቀሩ ግን ሁለት ወር ሊሆናቸዉ ነዉ።ሆቴሎች፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ መድብሮች፣ ተከርችመዋል።

የአዲስ አበባ የሆቴል ባለቤቶች ማሕበር ያደረገዉ ቅኝት እንዳመለከተዉ የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭትን ለመከላከል በተወሰደዉ እርምጃ ምክንያት 88 ከመቶ የሚሆኑት የከተማይቱ ሆቴሎች አንድም በከፊል አለያም ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል።ወይም ለመዝጋት ወስነዋል።ኮቪድ 19 ወረርሺኝን ለመከላከል የተወሰደዉ እርምጃ ጥቅምና ጉዳቱ፣ ወረሽኙ ያስከተለዉ ቀዉስና መዉጪያ መንገድ ካለ ለመቃኘት እንሞክራለን።(ሙሉዉን ያድምጡ)

ነጋሽ መሐመድ