1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሀሰተኛ መረጃዎች ትግል

ዓርብ፣ ሚያዝያ 9 2012

የተለያዩ ሀሰተኛ መረጃዎች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት የብዙዎችን ቀልብ ሲስቡ ይስተዋላል። የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን አፍሪቃ ውስጥ አደገኛ የሚያደርገው ደግሞ መረጃውን እንደወረደ የሚቀበለው እና የሚያጣራው ሰው ብዙ ስላልሆነ ነው ይላሉ የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ተሳታፊዎች፤

https://p.dw.com/p/3b1ai
Symbolbild - Fake / Fakt
ምስል Imago Images/S. Steinach

ኮሮናና በአፍሪቃ የሀሰተኛ መረጃዎች ትግል

በተለይ በዚህ በኮሮና ወቅት ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ወሳኝ ነው ምክንያቱም ኢንተርኔት ላይ ብዙ የሚያስገርሙ ታሪኮች እየተሰራጩ ነው ይላል ቪንሰት ንጌቴ ከአፍሪካ ቼክ፤  
«አንድ ምስል አለ ። ይህም እ.ጎ.አ. በ 2014 በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ብዙ ሰዎች መሬት ላይ ተኝተው ቲያትር ሲያሳዩ የተነሳ ነው። ይሄው ምስል ግን ናይጄሪያ ውስጥ በኢንተርኔት አማካኝነት እነዚህ ሁሉ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የሞቱ ናቸው በማለት እንደ ማስረጃ ቀርቧል።”
አፍሪካ-ቼክ የተቋቋመው እ.ጎ.አ. በ 2012 ዓ ም ነው። ተቋሙ በተለይ በኢንተርኔት አማካኝነት የሚለቀቁ መረጃዎች እውነተኛነትን ያጣራል። አፍሪካ-ቼክ በአሁኑ ጊዜ ሌጎስ እና ናይሮቢን ጨምሮ በአህጉሪቱ በርካታ ቢሮዎች አሉት ፡፡ ለንደን ውስጥም ቅርንጫፍ ቢሮ አለው ፡፡ ሰራተኞቹ ትክክል የሆነን እና ያልሆነን መረጃ ያጣራሉ። ተቋሙ ‹ክዌሪ› ተብሎ የሚጠራ የኃትስዓፕ ቻናልም አለው። "ክዌሪ ማለት ስዋሂሊኛ ሲሆን እውነት እንደማለት ነው። ሰዎች አጠራጣሪ ሆኖ ያገኙትን ማንኛውንም መረጃ ኃትስዓፕ ላይ ሊልኩልን ይችላሉ፡፡ እኛ ደግሞ እነዚህን እናጣራ እና ለላከልን ሰው መልስ እንሰጣለን። ምላሹን ስንልክም በቀላሉ በኃትስዓፕ ለሌላ ሰው ማጋራት በሚቻልነት መልኩ አድርገን ነው። »
የኮሮና በሽታን ያድናል ወይም ጨርሶ እንዳይዝ ይከላከላል እየተባለ የሚሰራጨውም የተሳሳተ መረጃ በርካታ ነው። ሮይተርስ ዜና ምንጭ ቃለ መጠይቅ ያደረገለት ይህ ኢትዮጵያ ወጣት ነጋዴ ለምሳሌ አፍንጫው ውስጥ ነጭ ሽንኩርት እና ዝንጅብል ከቶ  እራሱን እየተከላከለ እንደሆነ በሙሉ ልብ ይናገራል። ሲያዩት እና ሲሰሙት የሚያስቀው ነገር ግን በአንድ ጊዜ ሰዎች እውነት አድርገው ሲቀበሉት ይስተዋላል ይላል ቪንሰት ኒጌቴ " ሰዎች ብሊች ኮሮናን ይገላል ሲሉ ሰምተናል ወይም ደግሞ የእንስሳት ሽንት ኮሮናን ያድናል ይላሉ። በርካታ የሀሰት መድሀኒቶች። ከዛ ደግሞ ስለ ክሎሮክዊን ብዙ ክርክር አለ። ብዙ ሰዎች ለኮሮና በሽተኞች ጠቃሚ ነው ይላሉ። ይህን የሚያመላክቱ ነገሮችም አሉ ነገር ግን ሳይንቲስቶች በበቂ ሁኔታ መጠናት ያለበት እንደሆነ ነው የሚናገሩት። »የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም ሳይቀሩ የወባ መድሀኒት የሆነው ክሎሮክዊን ለኮሮና ታማሚዎች መድሀኒት እንደሆነ ተናግረዋል። ኒጌቴ እንደሚለው ይህ ዜና በፍጥነት በተሰራጨበት ናይጄሪያም ሰዎች በብዛት መድሀኒቱን በመግዛታቸው የተነሳ ክሎሮክዊን በአንድ ጊዜ ከገበያ ላይ ጠፍቷል።

DW Sendung The 77 Percent
አፍሪቃ ውስጥ ከጨርቅ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ እየሰፉ የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር ተበራክቷል።ምስል DW

ይህንኑ የሀሰት መረጃዎች ጉዳይ በተመለከተ የዶይቸ ቬለ የ 77 ከመቶው የወጣቶች ፕሮግራም ሌጎስ ናይጄሪያ ውስጥ አንድ ውይይት አካሂዶ ነበር። በዚህ ውይይት ላይ የተሳተፈችው ሎላ ዴዋንሲ ጋርዲያን ለተጋለው ጋዜጣ ናይጄሪያ ውስጥ ትሰራለች። የኮሮና ተህዋሲ ናይጄሪያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ጣሊያናዊ ላይ መረጋገጡ ይፋ እንደሆነ ወጣቷ ጋዜጠኛ እና ባልደረቦቿ ዜናውን በትዊተር አሰራጭተው ነበር። ብዙም ሳይቆይ አንድ ሰው እኔ ነኝ ሀጢያተኛው ሹፌር ጣሊያናዊውን ከአይሮፕላን ማረፊያ የተቀበልኩት የሚል መልዕክት ይልክላቸዋል። ይህም ዜና በአንዴ ይሰራጫል።  « ሁሉም ሰው ታድያ፤ አንተ ነህ እንዴ? በል ቶሎ እጅህን ስጥ የሚል አስተያየት ሰጡ። ወሬውንም ሁሉም ተቀባበሉት። የሰውየው ማንነት ፣ ፎቶው ይኼው እየተባለ ተሰራጨ። እኛም ትዊቱን እንዳየን ወደ ስራ ነው የገባነው። ለሰውየው ደወልንለት። ሰውየው ግን ስለምን እንኳን እንደምናወራ ሊገባው አልቻለም ነበር። እኛም ነገሩን እንዳጣራን መረጃን መልሰን ለጠፍን »ሎላ ይህን የፈጠረው የመረጃ ክፍተት ነው ትላለች። መንግስታ የታማሚውን ማንነት ይፋ ስላላደረገ ነጭ ሰው ከኤርፖርት የተቀበለ ሁሉ እኔ ልሆን እንዴ ማለት ይጀምራል። 
ሌላኛው የውይይት ተሳታፊ የሆነው ሼኩን አዋሳኛም በዚህ ይስማማል።  ጥርጣሬ እና እምነት በሌለበት ማህበረሰብ ውስጥ አንዳንድ ራሳቸውን አጉልተው ለማውጣት ለሚፈልጉ ሰዎች በቂ ቦታ አለ ባይ ነው። ሌሎችም ይህንን ስለማይፈትሹ ነገሮች በቀላሉ ይሰራጫሉ ወይም ይጋራሉ።« እንደዚህ አይነት ቀውስ በአንድ ሀገር ላይ በሚከሰትበት ጊዜ እያንዳንዱ ሰው ማድረግ ያለበት ኃላፊነት ማሳየት ነው። ከሚመለከታቸው ሰዎች ጎን በመቆም፤ መንግስት ፣ የአለም የጤና ድርጅት ሌሎች ተቋማት የሚያወጧቸውን መመሪያዎች እና ምክሮች መከተል ነው። የሚገባው። በዚህ አይነት መንገድ ብቻ ነው ይህንን መታገል የምንችለው እንጂ ሽብር በመፍጠር አይደለም።» የውይይቱ ተሳታፊ ሎላ ከኮሮና ጋር በተያያዘ የተሰራጨ ሌላ ምሳሌም አላት።

Nigeria Lagos | Coronavirus | Presse, Medien
ምስል DW/A. Dada

« አንብባችሁት እንደው ጥቁሮች በኮሮና ተህዋሲ ሊያዙ አይችልም የሚል መረጃ ተሰራጭቶ ነበር። ያኔም ሰው ብዙም ጥያቄ አላነሳም። ተመልከቱ እኛ ጥቁሮችን ተህዋሲው አይነካም ፤ ተህዋሲው ይህን አይነት የአየር ንብረት ሊቋቋም አይችልም ማለት ጀመሩ። ይህን መሠል አባባሎች ስንታዘብ የባለሙያዎችን እና የአለም ጤና ድርጅት ምላሽን በማካተት ለህዝቡ እውነታውን ይፋ አደረገን። ሌላው ሳላነሳው ማለፍ የማልፈልገው ነገር ደግሞ ነጭ ሽንኩርት ነው። መረጃው በምን አይነት ፍጥነት መሰላችሁ የተሰራጨው። ሰው መልዕክት ይልክልኝ ነበር ለማንኛውም ኮሮና ወደ ሰፈሬ ቢገባ እንኳን ነጭ ሽንኩርት ገዝቼ ማስቀበጥ አለብኝ የሚል። ይህን አይነት አባባል ስሰማ ፍፁም ስህተት የሆነ ነገር ነው ያልኩት።»
ዎሮንታዩ ጁዌል ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ነው። ናይጄሪያ ውስጥ አፍሪካ ቼክ ለተባለው ተቋም ያገለግላል። ያልተጣሩ መረጃዎች በኤቦላ ወረርሽኝ ጊዜም እንዴት ለሰው ህይወት መጥፋት እንደዳረጉ ያስረዳል።  « ኤቦላ የተከሰተ ጊዜ የወጡ አንዳንድ ታሪኮች ነበሩ። የተወሰነ ውኃ በጨው ቀላቅሎ ከጠጡት ኤቦላን መከላከል እንደሚቻል። በነገራችን ላይ ሁለት ሰዎች  እንደውም ብዙ ጨው በመጠጣታቸው ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል። »
ታድያ ሀሰተኛ መረጃዎች እንዳይሰራጩ ወጣቶቹ መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ? ሼኩን መንግሥት ማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎችን ይቆጣጠር በሚለው ፈፅሞ አይስማማም። እሱ እንደሚለው መንግስት እንደውም ለሰዎች ለመወሰን ሲሞክር በርካታ ጊዜ ተስተውሏል።« ነገሮችን በምን መልኩ መረዳት እንዳለን ለማያየት እንዲያመቻቸው ሲሉ ለዚህም ነው ፖለቲከኞች የሚዲያ ተቋማትን ለመግዛት የሚሞክሩት። የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ተፈጥሮው ራሱ ዲጂታል፣ ዲሞክራሲያዊ እና አሳታፊ መድረክ ነው። ስለዚህ መንግስት ሀሰተኛ መረጃን ከመታገል ይልቅ ፣ ግልፅ እና ተጠያቂ መሆን አለበት። የተሸሸገ እና ሚስጥር የሆነ ነገር ሰዎች እንዳለ ሲረዱ ራሳቸው እውነታውን የሚያፈላልግ ጋዜጠኛ ለመሆን ይሞክራሉ። ስለዚህ መንግስት ሀቀኛ ይሁን። የማህበራዊ መገናኛ ዘደዎች ኃላፊነት እንዲወስዱ ከፈለገ ራሱ ኃላፊነት ያሳል።»
በዚህ ግን ሌላዋ ተወያይ አትስማማም። « የመሰላችሁን የመናገር እና ማህበራዊ መገናኛ ላይ የመጫኝ ነፃነት አላችሁ ። ይህ ግን ሌላውን አካል መጉዳት የለበትም ። ለምሳሌ ፕሬዚዳንት ሙሀሙዱ ቡሃሪ ሞቱ ብሎ መለጠፍ ሌሎችን ጭንቀት ውስጥ ሊከት ይችላል። ይህ እንዳይሆን ክትትል ቢደረግ ጥሩ ስሜት ይሰማኛል።]
ሀሰተኛ መረጃዎች እንዳይሰራጩ ሁሉም ተወያዮች የሚስማሙበት ጉዳይ የሚዲያ ተቋሟት መረጃ በፍጥነት ማድረስ አለባቸው የሚለው ላይ ነው። ይህ ብቻ አይደለም « ከ70 በመቶ በላይ ወጣቶች ያሉባቸው ሀገራት አሉ። ጋዜጣ የማያነቡ እና ቴሌቪዥን የማያዩ። ናይጄሪያ ውስጥ ሰዎች በአመኔታ እየተከታተሉት ያለው ለምሳሌ ትዊተርን ነው እንጂ ጋዜጣን አይደለም።
« መደበኛ የመገናኛ ብዙኃን ከጊዜው ጋር መሄድ አለባቸው። ተከታታዮቻቸው የት ነው ያሉት? ፌስ ቡክ ላይ ነው። ከሆነ ወደዛ መሄድ ያስፈልጋል። ይፋ ማድረግ የምትፈልጉትን መረጃዎች ትዊት ማድረግ እንዳትዘነጉ። ሰዎቹ ኢንስታግራም ላይ ከሆኑ ኢንስታግራም እንዴት እንደሚሰራ ተረዱ። ወይም ስለዚህ የሚረዱ ሰዎች ቅጠሩ እና መረጃዎቹን ያጋሩላችሁ። »

Infografik BG Mythen und Fakten Coronavirus - Knoblauch EN

ልደት አበበ 

ሂሩት መለሰ