1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮሮና፦ የጎረቤት ኬንያ ቆራጥ ርምጃ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 12 2012

የዓለም ጤና ድርጅት ለአፍሪቃ አንዳች ምክር አለው። «ወደፊት የከፋውን ጠብቃችሁ ለዚያ ከወዲሁ ተዘጋጁ» ብሏል። ምክሩን የኬንያ መንግስት ከልብ የወሰደው ይመስላል።

https://p.dw.com/p/3ZobU
Symbolbild Corona-Virus
ምስል Reuters/D. Ruvic

ድንበሯንም ለውጭ ሀገር ተጓዦች ጥርቅም አድርጋ ከርችማለች

ኬንያ ውስጥ እስከ ሐሙስ መጋቢት 10 ቀን፤ 2012 ዓ.ም ድረስ በኮሮና ተሐዋሲ የተያዘው ሰው ብዛት ሰባት ነበር። እንዲያም ኾኖ ግን ኬንያ ትምህርት ቤቶቿን በአጠቃላይ ዘግታ ድንበሯንም ለውጭ ሀገር ተጓዦች ጥርቅም አድርጋ ከርችማለች። ከለንደን ወደ ኬንያ ያቀኑ አንድ የምክር ቤት አባል በአባላቱ ተዋክበው ከምክር ቤቱ ተባረዋል። አንዳንድ ድርጊቶች በዘፈቀደ ሲፈጸሙ ይስተዋላል። አንድ ሰው የኬንያ መዲና ናይሮቢ እምብርት ላይ ተሐዋሲውን ይገላል የተባለ ነገር ሲረጭ ይታያል።

መላ አካሉን የተሸፋፈነ ሰው ናይሮቢ ባቡር ጣቢያ ውስጥ አንድ ባቡር ላይ አንዳች ነገር እየረጨ ነው። ባቡሩ ጋር ግን ብዙም መቆየት አላፈለገውም።

«ውኃ ውስጥ በቀላሉ የሚቀየጠውን ክሎሪን ነው የምንጠቀመው። ሙሉ ለሙሉ አስተማማኝ ነው። ብትፈልግ ልትጠጣው ትችላለህ፤ ምንም ጉዳት አያደርስብህም።»

የኬንያ ጤና ጥበቃ ባለሞያ ፔተር ንጄንጋ የኮሮና ተሐዋሲውን ይገድላል በሚል ነው የክሎሪኑን ቅይጥ የሚረጩት። ራሳቸውን በጭምብል እና መከላከያ ልብስ የሸፈኑ ወታደሮች በናይሮቢ ጎዳናዎች ወዲህ ወዲያ ይላሉ።   

«በርካቶች በጋራ የሚጠቀሟቸው ነገሮች ላይ እናተኩራለን። ከምንም በላይ በርካታ ሰዎች የሚነኳቸው ነገሮችን። ከላይ የሚታዩትን ነገሮች በአጠቃላይ ተሐዋሲ ማምከኛውን እንረጫለን።»

Afrika Coronavirus Pandemie / Kenia
ምስል Reuters/B. Ratner

የማጽዳት ዘመቻው ቢያንስ ሰዉን ለማንቃት አንዳች ርምጃ ነው። ምናልባትም ዜጎች ደኅንነት እንዲሰማቸውም ሊያደርግ ይችላል። አብዛኞቹ ኬንያውያን በሀገራቸው የኮሮና ተሐዋሲ ሊዛመት ይችላል በሚል ስጋት ገብቷቸዋል። የኬንያ መንግስት በበኩሉ የዓለም ጤና ድርጅት ማስጠንቀቂያን ከምር ነው የወሰደው።

«በሌሎች ሃገራት ተሐዋሲው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ምን ያህል በፍጥነት እንደተዛመተ ተመክተናል። ስለዚህ አፍሪቃ ውላ ሳታድር ከወዲሁ ለከፋው ነገር ብትዘጋጅ ነው የሚበጀው።»

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም አፍሪቃውያን መዘናጋት እንደሌለባቸው በአጽንዖት ተናግረዋል። ኬንያ ውስጥ የመጀመሪያው በኮሮና ተሐዋሲ የተጠቃ ሰው መኖሩ እንደተነገረ ነው ማንኛውም የውጭ ዜጋ ወደ ኬንያ መጓዝ እንደማይችል የሀገሪቱ መንግሥት የወሰነው። ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። ከውጭ የሚገቡ ኬንያውያን በአጠቃላይ ለሁለት ሳምንት ሙሉ ራሳቸውን ከሰው ለይተው እንዲቆዩ የኬንያ መንግስት ጥብቅ ውሳኔ አስተላልፏል። አንድ የምክር ቤት አባል ከለንደን መልስ ምክር ቤቱ ውስጥ ብቅ ማለታቸው በምክር ቤቴቱ ብጥብጥ ነው ያስከተለው።  

የኹሉም ፓርቲዎች አባላት የምክር ቤቱ አባል ከምክር ቤቱ በአስቸኳይ ተገፍትረው እንዲወጣ ጠይቀዋል። የምክር ቤቱ ሊቀመንበርም አባላቱ የጠየቊትን አድርገዋል።

«ምናልባት በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት የገባ ሌላ አባልም ካለ፤ ለኹለት ሳምንታት በለይቶ ማቆያ ውስጥ መኾናችሁን ርግጠኛ እንድትኾኑ ትጠየቃላችሁ።»

የኬንያ የጤና ስርዓት ከፍተኛ ቊጥር ላለው የኮሮና ተሐዋሲ ፈጽሞ ዝግጁ አይደለም። በኬንያ ወደ 50 ሚሊዮን ግድም ሰዎች ይኖራሉ። እናም ታዲያ ከፍተኛ ክትትል ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በተዘጋጁ ክፍሎች ውስጥ 200 አልጋዎች እንኳን የሉም።            

ብዙዎችን እጅግ ያስጨነቀው፦ ተሐዋሲው በትልልቅ ከተሞች የተጨናነቊ ጎስቋላ መንደሮች ከገባ ሥርጭቱን ለማስቆም እጅግ አዳጋች መኾኑ ነው። ናይሮቢ በሚገኘው ትልቊ የድኾች መኖሪያ ኪቤራ የተሰኘው መንደር ውስጥ አንድ የእርዳታ ድርጅት የእጅ መታጠቢያ ቦታዎችን አመቻችተል።  በተዘጋጁት ቦታዎች ውኃና ሳሙና አስፈላጊ መኾናቸውን አንድ የድርጅቱ ባልደረባ ይናገራሉ።  

«አኹን ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው እጅ መታጠብ ነው። ተሐዋሲው እንዳይዛመት ብቸኛው መንገድ ያ ነው። እዚህ ኪቤራ እና ኬሎች ስምንት የጎስቋላ መንደሮች ውስጥ አለን። ወደፊት ወደ ሌሎች መንደሮች ለመዝለቅም እንሻለን።»

Kenia Jama Wolde
ምስል DW/M. Kwena

ኮሮና ተሐዋሲን ባለበት ለማቆም ብሎም ለማጥፋት ኬንያውያን የቆረጡ ይመስላል። ብዙዎች ተሐዋሲው ተሰራጭቶ ወደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማምራቱን ፈጽሞ አይፈልጉም። ያ መጣ ማለት በተለይ በድህነት አረንቋ ውስጥ ለሚገኙ የመንገድ ዳር ቸርቻሪዎች፤ አውቶቡስ አሽከርካሪዎች፤ የዕደ ጥበብ ባለሞያዎች ለመሳሰሉት ገቢያቸው ደርቆ ጉሮሯቸው ተዘጋ ማለት ነው።

ያም በመኾኑ መንግስት ከወሰዳቸው ፈጣን ርምጃዎች ባሻገር ነዋሪውም የተባለውን ለማድረግ በመረባረብ ላይ ነው። ምናልባትም ኢትዮጵያን ጨምሮ የኬንያ ጎረቤት የኾኑ ሃገራትም፦ በርካታ ሰዎች በአንድ ላይ የሚከማቹባቸውን ስብሰባዎችን በማስቀረት፤ ኅብረተሰቡም የዓለም ጤና ድርጅት የሚመክረውን ከልብ ወስዶ ቢተገብር ነገሮች ሳይቃጠል በቅጠል ይኾኑለታል።

በዓለማችን ጠንካራ ምጣኔ ሐብትና ድንቅ የጤና ስርዓት ላላቸው እንደ ጀርመን ላሉ ሃገራት ሳይቀር ተሐዋሲው ብርቱ ፈተናን ደቅኗልና ከቊጥጥር ውጪ ከመውጣቱ በፊት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል።     

ማንተጋፍቶት ስለሺ/አንትየ ዲክሐንስ