1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ከሰው ልጆች ጋር አብረው ከሚዘልቁ አንዱ ሊሆን ይችላል-የዓለም ጤና ድርጅት

ረቡዕ፣ ግንቦት 12 2012

ዓለም ለኮሮና ክትባት አሊያም መድኃኒት ለማበጀት ሲሯሯጥ የዓለም ጤና ድርጅት ተሕዋሲው እንደ ወባ እና ኤች አይቪ ረዥም ጊዜ ሊቆይ እንደሚችል አስጠንቅቋል። የድርጅቱ የአስቸኳይ የጤና ጉዳዮች ኃላፊ ማይክ ራየን "መቼ መፍትሔ እንደምናገኝለት መናገር ከባድ ነው። ይኸ ተሕዋሲ ከሰው ልጆች ጋር አብረው ከሚዘልቁ አንዱ ሊሆን ይችላል" ብለዋል።

https://p.dw.com/p/3cYE8
Illustration Mikroskop Coronavirus
ምስል picture-alliance/M. Schönherr

ለኮሮና ክትባት ለማግኘት የሚደረገው ጥረት እንደቀጠለ ነው

ባለፈው ሳምንት ዓለማቀፉ የጤና ድርጅት "የኮረና ተሃዋሲ ወረርሽኝ በቀላሉ ላይጠፋ ይችላል" ሲል ስጋቱን ገልጿል:: የድርጅቱ የአደጋ ጊዜ ፕሮግራም ሃላፊ ማይክል ሪያን እንዳሉት "የኮቪድ-19 በሽታ በማኅበረሰባችን ውስጥ ተጨማሪ አደገኛ በሽታ ሆኖ ሊቀጥል ይችላል:: ቫይረሱ መቼ ሊጠፋ እንደሚችል አሁን ላይ መተንበዩ አዳጋች ነው:: በአጭር ጊዜ ውስጥም ፈፅሞ የሚወገድ አይመስልም" በማለት ሀገራት በሽታውን ለመቆጣጠር የጀመሩትን ዘመቻ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል::
"ይህ የኮቪድ-19 ቫይረስ ምናልባትም ፈፅሞ ላይጠፋና ልክ ከአሁን ቀደም እንደተከሰቱት አንዳንድ በሽታዎች በተወሰኑ አካባቢዎች "ኢንደሚክ" በሽታ ሆኖ በማኅበረሰቡ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ከሰዎች ጋር አብሮ ሊኖር ይችላል:: ተመራማሪ ከሆንክ ለአንድ በሽታ ፈውስ የሚሰጥ ክትባት በማይኖርበት በእንዲህ ያለ ወቅት በቀጣይ የምትወስደው እርምጃ ቫይረሱ በርካታ ሰዎችን ካጠቃ በኋላ የሥርጭት አድማሱ እየቀነሰ ከዓለማቀፍ ወረርሽኝነት ወደ አካባቢያዊ "ኢንደሚክ" ደረጃ ዝቅ የሚልበት ከዛም ጨርሶ የሚጠፋበት ሁኔታ ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል በሚለው ስልት ላይ ማተኮር ይሆናል" ሲሉ ሃላፊው ገልፀዋል:: ከመቶ የሚልቁ የኮቪድ-19 በሽታ መከላከያ ክትባቶች በሙከራ ሂደት ላይ መሆናቸውንም ያስታወሱት ዶክተር ሪያን "ለኮቪድ-19 የሚዘጋጅ ክትባትም ወረርሽኙን እስከወዲያኛው ላያጠፋው ይችላል" የሚል ስጋት እንዳላቸው ነው በጄኔቫው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ያስረዱት :: የዓለም የጤና ድርጅት የአውሮጳ ዳይሬክተር ዶክተር ሃንስ ሄንሪ ኩልሽም ተመሳሳይ ስጋት እንዳላቸው ሰሞኑን ይፋ አድርገዋል::
"እኛ በቫይረሶች በተሞላች ፕላኔት ውስጥ እንደምንኖር መገንዘብ ይኖርብናል:: ምንም እንኳ ቫይረሱ መቼ እንደሚጠፋ ዛሬ ላይ ማንም መተንበይ ባይችልም መፍትሄው ግን ይኖራል:: የኮሮና ተሃዋሲ ስርጭት ልክ እንደ ሌሎች ቫይረሶች ሁሉ ኢፒደሚክ ከዛም ኢንደሚክ ብለን ወደምንጠራቸው ደረጃዎች ዝቅ ሊል ይችላል ፣ለዚህም እንዲረዳ በቫይረሱ ባህሪና በኅብረተሰቡ ላይ በሚያሳድረው ተፅዕኖ ላይ ጥልቅ ቅኝትና ምርምር ማድረግ ያስፈልጋል:: እስካሁን የተገኙት ውጤቶች ለመጪው ጊዜ ይበልጥ የምንዘጋጅበት እንጂ በደስታ ተውጠን የምንዘናጋበት አይደለም :: ምክንያቱም ዓለማችን ለወረርሽኞች እንግዳ ባትሆንም አሁን የገጠመን ፈተና በእርግጠኝነት አስከፊ በመሆኑ ነው:: ስለዚህ ምንም እንኳ ያልተቋጩ ጥቂት ጉዳዮች ቢኖሩንም ጠንካራ የጤና ሥርዓትን ከዘረጋን ችግሮችን በአሸናፊነት ለመወጣት እንደሚያስችሉን በቂ ልምድ ቀስመናል:: የጤና ሥርዓት አቅምን መገንባትና የሕዝብን ጤና ክትትልን ማጠናከር አሁን ላይ እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ሆኗል" ነበር ያሉት ዶክተር ኩልሽ::

Schweiz PK Michael Ryan WHO
ምስል picture-alliance/Keystone/S. Di Nolfi

ዶክተር ስንታየሁ አሰፋ በጀርመን ሀገር ከ 30 ዓመታት በላይ በተለያዩ ሆስፒታሎች በህክምና ሙያ አገልግለዋል:: በአሁኑ ወቅት ላይፕሲግ በሚገኘው በቱሪንጂያ የሂሊዮስ የዩኒቨርሲቲ ክሊኒክ የማይክሮ ባዮሎጂ፣ የውስጥ ደዌና የተላላፊ በሽታዎች ህክምና ክፍል ሃላፊና ስፔሻሊስት ናቸው:: በዛሬው ዝግጅታችን ስለኮሮና ተሃዋሲ የተለያዩ ሙያዊ ማብራሪያዎችን እንዲሰጡን ጠይቀናቸዋል:: በቅድሚያ አንድን በሽታ ወይም ቫይረስ "ኢንደሚክ"፣ "ኢፒደሚክ" እና "ፓንዴሚክ" ነው የምንልባቸውን መስፈርቶች እንዲሁም የፅንሰ ሃሳቦቹን ልዩነት በምሳሌ አብራርተዋል:: " አንድ በሽታ ከእንስ ሳትም ሆነ ከቫይረስ ከአንድ አካባቢ ሲነሳና በዛ ሕዝብ ውስጥ ተወስኖ እስካለ ድረስ ኢፒደሚክ ነው የሚባለው:: ቫይረሱ ወደ ሌላ ሃገር ከተዛመተና የተለያዩ ሀገራት ሕዝቦችን ማጥቃት ከጀመረ ማለትም ወደ ጎረቤት ሀገራት አልያም አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ የሥርጭት አድማሱን የማስፋት ይዘት እየያዘ ሲመጣ ፓንዴሚክ ወረርሽኝ ሆነ ይባላል:: ´ፓንዴሚክ´ የግሪክ ቃል ነው:: ´ፓን´ ማለት ብዙ ወይም ሁሉም ማለት ሲሆን ´ዴሚክ´ ማለት ደግሞ ሕዝብ የሚል ትርጉም አለው:: ስለዚህ በሽታው ልክ እንደ ኮቪድ-19 ወይም ኤድስ ፓንዴሚክ ከሆነ ብዙ ሀገሮች በወረርሽኙ ተጠቅተዋል ማለት ነው:: በሌላ በኩል እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 2012 ዓ.ም አካባቢ በመካከለኛው ምስራቅ በተለይም ሳውድ አረቢያ የተከሰተው የመተንፈሻ አካል በሽታ ሜርስ በዛው አካባቢ ብቻ ተወስኖ ስለቀረ ኢንደሚክ በሽታ ነው ማለት ይቻላል:: በኢትዮጵያም እንደ ወባ እና የማጅራት ገትርን የመሳሰሉ በኢትዮጵያና በጥቂት የአፍሪቃ ሀገራት ብቻ ለረጅም ጊዜያት ተወስነው የሚገኙና ተለይተው የሚታወቁ በሽታዎች ለዛ አካባቢ ኢንደሚክ በሽታ ናቸው:: አንድ በሽታ በአንድ አገር ወይም አካባቢ ብቻ ተወስኖ ማለትም ኢንደሚክ ሆኖ በየጊዜው እያገረሸ ለረጅም ጊዜ ሲቀጥል በማህበረሰቡ ኑሮ በቱሪዝም ኢንዱስትሪውና በምጣኔ ሃብት ላይ ከፍተኛ ቀውስ ማሳደሩ አይቀርም:: ዓለም በሂደት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ኢንደሚክ ሆኖ እንዳይቀር አሁን ላይ ከፍተኛ ምርምርና ጥረት የሚያደርገውም ለዚህ ነው " በማለት አብራርተዋል::
 

እንዳልካቸው ፈቃደ

ጸሀይ ጫኔ

እሸቴ በቀለ