1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮሮና በአሜሪካ፦ የዜጎች ጤንነት ወይንስ ምጣኔ ሐብት?

ሐሙስ፣ መጋቢት 17 2012

የዩናይትድ ስቴትስ ገዢ ባለሥልጣናት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተሐዋሲው በብዛት ባልተዛመተባቸው ግዛቶች እና በወጣቶች ላይ በቶሎ እንዲነሳ ይሻሉ። ሀገሪቷም በምጣኔ ሐብት ድቀት እንዳይከሰትባት ይሞግቱ ይዘዋል። የሰው ልጅ ክቡር ሕይወት ሊቀድም ይገባል ሲሉ የሚከራከሩ ባለሥልጣናትም ድምፃቸውን እያሰሙ ነው። 

https://p.dw.com/p/3a3Uo
Washington Abstimmung im US-Senat zu Corona-Hilfspaket
ምስል picture-alliance/AP/Senate Television

«የሰው ልጅ ክቡር ሕይወት ሊቀድም ይገባል»

በመላው ዓለም ስጋት የኾነው የኮሮና ተሐዋሲ ያመጣው ተግዳሮት በዩናይትድ ስቴትስ ለየት ያለ መልክ ይዟል። የዜጎች ደኅንነት ይቅደም የምጣኔ ሐብት ዋስትናው በሚል አንዳች ውዝግብም አስነስቷል። የዩናይትድ ስቴትስ ገዢ ባለሥልጣናት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተሐዋሲው በብዛት ባልተዛመተባቸው ግዛቶች እና በወጣቶች ላይ በቶሎ እንዲነሳ ይሻሉ። ሀገሪቷም በምጣኔ ሐብት ድቀት እንዳይከሰትባት ይሞግቱ ይዘዋል። የሰው ልጅ ክቡር ሕይወት ሊቀድም ይገባል ሲሉ የሚከራከሩ ባለሥልጣናትም ድምፃቸውን እያሰሙ ነው። 

እንደተለመደው በፕሬዚደንቱ የትዊተር መልእክት ነበር የጀመረው። «መፍትኄው ከችግሩ የከፋ እንዲኾን አንተወውም» ሲሉ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ ትዊተር ገጻቸው ላይ ሰኞ እለት ጻፉ። የምጣኔ ሐብት አማካሪያቸውም ላሪ ኩድሎቭ የፕሬዚደንቱን ቃል ፎክስ ኒውስ በተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ቃለ ምልልስ ላይ ደገሙት። ጠንካራ ርምጃ የተወሰደውም ያ በመኾኑ ነው አሉ አማካሪው። 

«ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን ማቋረጥ አንችልም። ኢኮኖሚው ለእያንዳንዱ የሚያስወጣው እጅግ ግዙፍ ነውና።»
ጉዳዩ፦ መቅደም ያለበት የዜጎች ደኅንነት ወይንስ ምጣኔ ሐብቱ የሚለው ነው። ፕሬዚደንቱ በጋዜጣዊ መግለጫ ንግግራቸው በግልጽ ለማስቀመጥ ሞክረዋል። የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ በምጣኔ ሐብቱ ላይ ምን ያኽል ጉዳት ተቀባይነት አለው? በተቃራኒው ምጣኔ ሐብቱን ለመታደግስ ምን ያኽል ሰው እስኪሞት ነው የሚጠበቀው? 

Illustration Coronavirus Sars-CoV-2
ምስል AFP/US Food and Drug Administration

«በተመሳሳይ የኾነ ጊዜ ላይ መክፈት እና መቀጠል ይኖርብናል። እነዚህን ኩባንያዎች እና ሠራተኞች ማጣት የለብንም።»
በምንም አይነት መልኩ በኮሮና ተሐዋሲ የተነሳ ሃገራቸው ለወራት እጅ መስጠት እንደሌለባት ፕሬዚዳንቱ የቆረጡ ይመስላል። የተቀመጠው የ15 ቀን ገደብ ሲጠናቀቅ አንዳች ውሳኔ ማሳለፍ ይሻሉ። ጉዳዩ  የመላ ሀገሪቱ ነዋሪዎች ጤና እና የሥራ ዋስትና ነው። 
ዶናልድ ትራምፕ ሃገራቸው የዜጎቿን ደኅንነት አስጠብቃ ምጣኔ ሐብቷንም መታደግ እንደምትችል በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል። ያም በመኾኑ ሀገሪቷን ዘግቶ መቀመጡ እንደሳቸው አባባል የሚያስከፍለው መስዋእትነት ከተሐዋሲውም የከፋ ነው።

«ሰዉ ብርቱ ስጋት ነው የሚገባው ምጣኔ ሐብትህ ሲናጋ፤ ያኔም መደበት እና መጨነቅ በርትቶበት ራስ ወደ ማጥፋትም ሊሻገር ይችላል። ሞት ሊከሰት ይችላል፤ ምናልባትም በተሐዋሲው ከሚሞተው በከፋ መልኩ።» 

በዚህም አለ በዚያ ማኅበረሰቡ ቀድሞውኑም ቢኾን ሌሎች አደጋዎች እና ጋሬጣዎችን ሲጋፈጥ ነው የኖረው እንደ ፕሬዚደንቱ። 
«በተሽከርካሪ አደጋ የሚደርሰውን ጥፋት ብትመለከቱ ከየትኛውም ከምንነጋገርበት ጉዳይ የበዛ ቊጥር ነው ያለው። ያ ማለት ታዲያ ከእንግዲህ ማንኛውም ሰው መኪናዎችን እንዳያሽከረክር ብለን እንነግራለን ማለት አይደለም።»

በኋይት ሐውስ የኮሮና ቀውስ አሰተባባሪዋ ዴቦራህ ቢርክስ እያንዳንዱ ግዛት በተሐዋሲው የተጠቃበት ነዋሪ መጠን ስለሚለያይ ውሳኔውን በዚያ መቃኘት አለበት ባይ ናቸው። በተሐዋሲው የተነሳ ወጣቶች ቢታመሙም እንኳ ከሟቾቹ 99 በመቶዎቹ ቀደም ሲል ኅመም የነበረባቸው ናቸው እንደ ዴቦራህ ገለጣ። 

«በየግዛቱ በዚህ መልኩ በደንብ መቃኘት ይገባዋል። ምናልባትም የእድሜ ጉዳይንም ማጤን ያሻል።» 
ይኽ ማለት የመንቀሳቀስ እገዳው ለወጣቶች እና ብዙም ተሐዋሲው ባልተዛመተባቸው የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች ሊነሳ ይገባል ነው ዕቅዱ የሚለው። 

USA New York Citiy | Coronavirus
ምስል Reuters/M. Segar

ተሐዋሲው በብዛት ከተዛመተባቸው ግዛቶች አንዷ የኾነችው ኒው ዩርክ ከተማ ገዢ አንድሪው ኩሞ ግን ሐሳቡን ይቃወማሉ። ለእሳቸው የቀረበው አማራጭ የተሳሳተ ነው። ውሳኔ ማሳለፍ ቢያስፈልግ እንኳን ምን ጊዜም የጤና ኹኔታን ማስቀደም ተገቢ ነው ሲሉ ይከራከራሉ።  የሰው ልጅ ክቡር ሕይወት በምንም መልኩ ለድርድር መቅረብ የለበትም ሲሉም ይሞግታሉ። 

«በነገራችን ላይ ያን ውሳኔ የምታስተላልፉ ከኾነ ነገሩ የኅብረተሰቡ የጤና ጉዳይ መኾኑን ማስገንዘብ ያሻል። የሰው ልጅ ሕይወትን እንደ ሸቀጥ ልትመዝኑት አትችሉም።»

የቴክሳስ ምክትል ሀገረ ገዢ ዳን ፓትሪክ ግን ፍጹም ለየት ባለ መልኩ ነው ነገሩን የቃኙት።  «ወደ ሥራችን እንመለስ፤ ወደ ሕይወታችን እንመለስ። ጉዳዩን በብልሃት እንያዘው። እኛ ከ70 ዓመት በላይ የኾነን ራሳችንን በሚገባ እንከባከባለን።»

እናም የ70 ዓመቱ አዛውንት አስፈላጊ ከኾነ ለልጆቻቸው እና ለልጅ ልጆቻቸው ሲሉ ሕይወታቸውን ለመስጠት ዝግጁ መኾናቸውን በአጽንዖት ዐስታውቀዋል።  የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕም ወደ ሥራ መመለሱ ላይ ቁርጠኛ የኾኑ ይመስላል። ልክ ከ15ኛው ቀን በኋላ በየትኛው መንገድ መሔድ እንዳለባቸው ውሳኔ እንደሚሳልፉ በተለመደው የትዊተር መ ልእክታቸው አስገንዝበዋል። 

USA Vizepräsident Mike Pence
ምስል picture-alliance/CNP/AdMedia/A. Drago

ይኽ በእንዲህ እንዳለ፦ የሀገሪቱ ምክር ቤት እና የሕግ መወሰኛ የኮሮና ተሐዋሲ የሚያስከትለውን የምጣኔ ሐብት ድቀት ለመደጎም የሚያግዝ ያለውን አስቸኳይ የ2 ትሪሊዮን ዶላር ገንዘብ ለማውጣት ረቡዕ ዕለት ስምምነት ላይ መድረሱን ዐስታውቋል። ከአጠቃላይ ገንዘቡ 367 ቢሊዮን ዶላር አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ሠራተኞቻቸውን ቤታቸው እንዲቆዩ ባደረጉበት ወቅት ደሞዛቸውን ለመክፈል የሚያስችል መርሐ ግብር ነው ተብሏል።

500 ቢሊዮን ዶላሩ ደግሞ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችን ለመደጎም የሚውል እንደኾነ ተገልጧል። ዲሞክራቶች ገንዘቡ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች እና ከበርቴዎችን ለመጥቀም የታሰበ ነው ሲሉ የምጣኔ ሐብት እፎይታ መርሐ ግብሩን ሲቃወሙት ነበር። በጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር በእለተ-ትንሣኤ አሜሪካውያን ዳግም ወደ ሥራ እንዲሰማሩ እና መደበኛ ሕይወት እንዲቀጥል ለማድረግ ማቀዳቸውን የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ለፎክስ ጣቢያ ተናግረዋል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ