1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኬንያውያን የበቆሎ መጠባበቂያ ተመዝብሯል ብለው ያምናሉ

ዓርብ፣ ጥቅምት 10 2010

በአፍሪካ በድርቅ ምክንያት የተከሰተው ቀውስ ኬንያንም ነክቷል፡፡ ለተማሪዎች ምግብ በነጻ ያድሉ የነበሩ በርካታ ትምህርት ቤቶች ይህንን አገልግሎታቸውን አቁመዋል፡፡ “ይህ የሆነው ግን በዝናብ እጥረት ምክንያት ሊደርስ ባልቻለው የሰብል ምርት ብቻ ሳይሆን በስግብግብ አትራፊዎች ጭምር ነው” ይላል የዣን ፊሊፕ ሾልዝ ዘገባ፡፡

https://p.dw.com/p/2mGjv
Kenia Nairobi Slum
ምስል DW/J. Scholz

ኬንያውያን የበቆሎ መጠባበቂያ ተመዝብሯል ብለው ያምናሉ

ከክበቡ ኩሽና ፊት ለፊት ያለው ሰልፍ እየረዘመ መጥቷል፡፡ በቀለም የደመቁ የፕላስቲክ ሳህኖችን የያዙ ህጻናት በስጋት መቁነጥነጥ ጀምረዋል፡፡ ሰዓቱ ከምሽቱ 12 ሰዓት እንዳለፈ ያሳያል፡፡ ኩዋ ዋቶቶ በተሰኘው በዚህ ትምህርት ቤት በአብዛኛው የቀድሞ ጎዳና ተዳዳሪዎች ለሆኑት ተማሪዎች እራት የሚቀርበው በዚህ ሰዓት ነው፡፡ በኬንያ መዲና ናይሮቢ በሶዌቶ ጭርንቁስ ሰፈር ባለው በዚህ ትምህርት ቤት የሚማሩ ህጻናት ትምህርት ብቻ አይደለም የሚያገኙት፡፡ ይልቁንም ትኩስ ምግብ እና ማደሪያ ስፍራም እንጂ፡፡ 

Kenia Nairobi Kwa Watoto Schule
ምስል DW/J. Scholz

ህጻናቱ በጉጉት ሲጠብቁት የነበረው የክበቡ ኩሽና በር በስተመጨረሻ ተከፈተ፡፡ ሆኖም በሹክሹክታ ወዲያው የተዳረሰው መረጃ ለእራት የሚሰጣቸው ከምሳ የተረፈ እንደሆነ የሚያረዳ ነበር፡፡ እንዲህ አይነቱ ነገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ ተከስቷል፡፡ የትምህርቱ ቤቱ ዳይሬክተር ኔህሚያ ንዴታ እንደሚያስረዱት በአሁኑ ጊዜ ለልጆቹ የሚቀርብ ነገር የለም፡፡ ንዴታ ትምህርት ቤቱን የዛሬ 20 ዓመት ግድም ሲመሰርቱት ረዳት የለሽ እና የተጎዱ ልጆችን ለማስተማር በሚል ነበር፡፡ እንደአሁኑ አስቸጋሪ የሆነ ጊዜ ግን እምብዛም አልገጠማቸውም፡፡ 

በኬንያ ላለፉት ሶስት ዓመታት የዝናብ ወቅት ተስተጓጉሏል፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የሰብል ምርት እጥረት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል፡፡ በመላው ሀገሪቱ የዋና ዋና የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ጣራ ነክቷል፡፡ ለሀገሬው ሰው ሁነኛ ምግብ ኡጋሊ(የበቆሎ ገንፎ) ዋና ግብዓት የሆነው የበቆሎ ዱቄት ዋጋ በግማሽ ጨምሯል፡፡ ንዴታ እንደሚነገሩት በዚህ ሰሞን ዱቄት ፍለጋ ወደ ወፍጮ ቤት መመላለስ ዋነኛ ስራቸው ሆኗል፡፡ “አንድ ሺህ ህጻናት መመገብ እንዳለብህ እንኳ ብትነግራቸው የሚመልሱህ ያ የእነርሱ ችግር እንዳልሆነ ነው፡፡ በር በላይህ ላይ ሲጠረቀምብህ ምን ማድረግ ትችላለህ?” ሲሉ ዳይሬክተሩ ይጠይቃሉ፡፡

ከንዴታ ትምህርት ቤት ተሁኖ በኬንያ ብሔራዊ የእህል እና የግብርና ምርቶች ባለስልጣን ስር የሚተዳደሩ የእህል ማከማቻ ጎተራዎች ይታያሉ፡፡ ድርቅ ከመከሰቱ በፊት የኬንያ መንግስት ጎተራዎቹ በሁለት ሚሊዮን ኩንታል በቆሎ እስከ አፍ ገደፋቸው እንደሚሞሉ ለዜጎቹ ቃል ገብቶ ነበር፡፡ የግብርና ሚኒስትሩ ዊሊ ቤት ያን ጊዜ እንዳስታወቁት በችግር ጊዜ ከእንዲህ አይነቱ የአስቸኳይ ጊዜ መጠባበቂያ “በትንሹ ለአምስት ወር ያህል” የሚያስጉዝ አቅርቦት እንደሚኖር ተናግረው ነበር፡፡ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ግን ድርቅ ከተከሰተ በኋላ ጎተራዎቹ በጥቂት ሳምንታት ባዶ መሆናቸው ያበሳጫቸዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ሁሉ በርካታ ኬንያውያን ቀሪው የበቆሎ መጠባበቂያ የት እንደገባ ማብራሪያ ይሻሉ፡፡ አንዳንዶች የተወሰነውን ክምችት “ፖለቲከኞች ዘርፈው ሸጠውታል” ሲሉ ይወነጅላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ መጠባበቂያ የሚባለው ጭርሱኑ አልነበረም ይላሉ፡፡ እነዚህን ውንጀላዎች የሚያረጋግጥ ማስረጃ ግን አልቀረበም፡፡ የትምህርት ቤት ዳይሬክተሩ ንዴታ የምግብ ክምችቱ በጎተራዎቹ ውስጥ እንዳለ ከጥቅም ውጭ ሆኗል ብለው ያምናሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ በጎተራዎቹ ያለውን መጥፎ አያያዝ ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ “በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ ሰዎች በረሃብ ሞት አፋፍ ደርሰው ከጎን ባለው ክፍል በቆሎ ተከማችቶ ይበሰብሳል” ይላሉ ዳይሬክተሩ፡፡ 

Kenia Nairobi Nehemiah Ndeta
ምስል DW/J. Scholz

በኬንያ የድርቅ ቀውስ ከተከሰተ ወዲህ የኬንያ መንግስት በርካታ ጥፋቶችን ከመፈጸሙ የተነሳ ባለሙያዎች የችግሩ ምክንያት “ግድ የለሽነት እና ብልሹ አስተዳደር ነው” የሚል እምነታቸውን ቀይረዋል፡፡ በኬንያ መንግስት በኩል የምግብ እጥረት እና የዋጋ ንረትን ለመቋቋም እርምጃዎች መወሰድ የጀመሩት በጣም ዘግይተው ነው፡፡ ከእርምጃዎቹ ውስጥ የገቢ ቀረጥን ማንሳት፣ ከአስቸኳይ ጊዜ መጠባበቂያ እህል ማሰራጨት እና መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችን መደጎም ይገኝበታል፡፡ 

የፋይናንስ ባለሙያው አልይካህን ሳቹ “ቀውሱ ከመከሰቱ አስቀድሞ በቂ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል”  ይላሉ፡፡ ሆኖም አብዛኞቹ ችላ ተብለዋል፡፡ እንደሳቹ እምነት ይህ የሚያሳየው በመንግስትም ውስጥ ቢሆን ከሁኔታው የሚጠቀሙ ውስጥ አወቆች እንዳሉ ነው፡፡  በርካታ ታዛቢዎች እንደሚያምኑት ከመንግስት በቂ ምላሽ ካለመስጠቱ ጀርባ የበቆሎ እና ሌሎች እህሎች ዋና ዋና አስመጪዎች እጅ አለበት፡፡ አስመጪዎች አሁን ባለው የዋጋ ግሽበት ዋነኛ ተጠቃሚዎች መሆናቸው እና ከኬንያ የፖለቲካ ሰዎች ጋር ያላቸው ቅርበት የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በበይነ አካባቢያዊ የምጣኔ ሀብት ትብብር ውስጥ የሚሰሩት ጄምስ ሺኪዋቲ ከፋይናንስ ባለሙያው ሳቹ ጋር ይስማማሉ፡፡  

Kenia Mutomo Dürre
ምስል DW/J. Scholz

“ነገርየው ትንሽ ጠለቅ ብለህ ከመረመርከው እነዚህ ነጋዴዎች በጣም ኃይለኛ የፖለቲካ የበላይ ጠባቂዎች እንደሏቸው ትረዳለህ፡፡ በሰጥቶ መቀበል ቀላል መርህ ላይ የተመሰረተ ንግድ ነው፡፡ ፖለቲከኞቹ በጥብቅ የሚፈለገውን የአስመጪነት ፍቃድ ይሰጣሉ፡፡ አስመጪዎቹ የሚያልሙትን ትርፍ ያገኛሉ፡፡ ከዚያ ከትርፉ የተወሰነው በድብቅ ለፖለቲካ ስርዓቱ ፈሰስ ይደረጋል” ይላሉ ጄምስ ሺኪዋቲ፡፡   

በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ስለእንደዚህ አይነት ውንጀላዎች ሲነሳባቸው በቁጣ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ ጄምስ ኦዶር የብሔራዊ የድርቅ ቦርድ ኃላፊ ናቸው፡፡ በድርቅ ምክንያት የተከሰተው ቀውስ በጋራ ጥረት በተደረገ ርብርብ እንደተረጋጋ የሚናገሩት ኃላፊው ኬንያውያን የተከሰተውን ቀውስ ከኋላቸው አድርገዋል ይላሉ፡፡ “ከድርቅ ጋር በተያያዘ ላጋጠመ የሰብል መታጣት በሚሰጥ ካሳ ላይ በመጀመሪያዎቹ አካባቢ የተወሰኑ ችግሮች ነበሩ፡፡ ፍላጎት የሌላቸው ማድረግ ያለባቸው ቀላሉ ነገር እንዲህ አይነት ተአማኒነት የሌላቸው ታሪኮች ከማሰራጭት መቆጠብ ነው” ሲሉ ኃላፊው ተቺዎች ይኮንናሉ፡፡  

የግብርና ሚኒስትሩ ዊሊ ቤት በነሐሴ ከተካሄደው ምርጫ ጥቂት ቀደም ብሎ ሲናገሩ ከአምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ከውጭ ሀገር ማስመጣታቸውን ተናግረው ነበር፡፡ የኬንያ መንግስት በእህል መሸጫዎች ላይ ድጎማ እንደሚያደርግ እና “በወር ውስጥ የተፈጠረው እጥረት ይቃለላል” ሲሉ ቃል ገብተው ነበር፡፡

የትምህርት ቤት ዳይሬክተሩ ንዴታ እንዲህ አይነት ተስፋ ያዘሉ ቃላት አይዋጡላቸውም፡፡ እርሳቸው የሚፈልጉት ብቸኛ ነገር ለተማሪዎች የሚያቀርቡት በቂ ምግብ ነው፡፡ የመጨረሻ ተስፋቸው በተባበሩት መንግስታት እና በኬንያ መንግስት የሚተገበረው የትምህርት ቤት የምግብ መርኃ ግብር ነው፡፡ ትምህርት ቤታቸው ባቀፋቸው በርካታ የጭርንቁስ መንደር ህጻናት ምክንያት በዚህ መርኃ ግብር ለመካተት መስፈርቱን ያሟላል፡፡ ነገር ግን እስከሁን ያገኘው በተጠባባቂ ዝርዝር ውስጥ መስፈር ነው፡፡ 

Kenia Nairobi Skyline
ምስል DW/J. Scholz

የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ኃላፊዎች ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በዚህ ወቅት በምግብ ዋጋ ንረት ምክንያት “መዘግየቶች” አሉ፡፡ ድርቅ ያስከተለውን ቀውስ ለመዋጋት የሚሰጡ እርዳታዎች ከምንጊዜውም ያነሰ ሆነዋል፡፡ እንደተባበሩት መንግስታት ገለጻ ከሆነ ለሰብዓዊ ስራዎች ከሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ውስጥ የተገኘው ከ20 በመቶ ያነሰ ነው፡፡ 

ንዴታ ስለ ብልሹ አስተዳደር እና የግለሰቦች ሀብት ማጋበሻነት በሚነገርበት በዚህ ወቅት ሰዎች ቀውሱን ለመፍታት ገንዘብ ባይለግሱ ሊጠየቁ አይገባም ባይ ናቸው፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን የሚሰቃዩት እንደ እርሳቸው ተማሪዎች አይነት ምንም ውስጥ የሌሉበት ንጹሃን መሆናቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ዳይሬክተሩ ስለተማሪዎቻቸው ሁኔታ እንዲህ ያጠቃልላሉ፡፡ “እነርሱ በቃ ተርበዋል”፡፡ 

ያን ፊሊፕ ሾልዝ / ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ